ሶማሊያውያን በጉንዳን ‘ሱስ መጠመዳቸው’ እንዳሳሰበው የአገሪቱ ፖሊስ ገለጸ

ጉንዳኖች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሶማሊያ ፖሊስ በርካታ ሰዎች እንደ እጽ እየተጠቀሙበት ነው ያለውን በአገሪቱ ያለ አንድ የጉንዳን ዝርያን አደንዛዥ እጽ ነው ሲል በመለየት አስጠነቀቀ።

ይህ በሳይንሳዊ ስሙ ‘ታፒኖማ ሴሲሌ’ የተባለው ሽታ ያለው የጉንዳን አይነት፣ በአገሪቱ በበርካታ መኖሪያዎች አካባቢ የሚገኝ ሲሆን ፎርሚክ የተባለ አሲድን የሚያመነጭ ነው።

የሶማሊያ ፖሊስ እንደደረሰበት ሰዎች ይህንን የጉንዳን አይነት ሰብስበው በመቀቀል የሚወጣውን እንፋሎት እየታጠኑ እንደ አደንዛዥ እጾች የሚፈጥሩት አይነት ለየት ያለ ስሜት ለማግኘት እንደሚሞክሩ ገልጿል።

በዚህም ሳቢያ ፖሊስ ይህንን ጉንዳኖችን በመጠቀም የተለየ የስካር ወይም ‘የመመርቀን’ ስሜትን ለማግኘት የሚፈጸመውን ድርጊት አደንዛዥ እጽ እንደመጠቀም እንደሚቆጥረው አመልክቷል።

ይህ ከጉንዳኖቹ የሚመነጨው ፎርሚክ የተባለው አሲድ አደገኛ መሆኑን የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ለዚህ አሲድ መጋለጥ ብዥ የማለት ስሜት፣ መቅለሽለሽና ማስመለስን ከማስከተሉም በተጨማሪ በአካል ላይ ጉዳትን ሊያደርስ ይችላል።

ስለዚህም ሰዎች ለዚህ አሲድ እንዳይጋለጡ ዶክተሮች ይመክራሉ።

ከፍተኛ መጠን ያላቸውን እነዚህ ጉንዳን ዝርያዎች የበሉ ወፎች ‘ስካርን’ የመሰለ የተለየ ባህሪይ እንደታየባቸው በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል።

አንድ የሶማሊያ የደኅንነት መኮንን ‘ሶማሊ ኬብል’ ለተባለ የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደተናገሩት ሰዎችም ተመሳሳይ ስሜት ለማግኘት ሲሉ ነፍሳቱን በተለየ መንገድ እየተጠቀሙ ነው ብለዋል።

“ጉንዳኖቹን ሰብስበው ክዳን ባለው ድስት ውስጥ በማድረግ ውሃው ለተወሰነ ጊዜ እንዲፈላ ካደረጉ በኋላ፣ ሰዎች በድስቱ ዙሪያ ተሰብስበው እንፋሎቱን ይታጠኑታል። ከዚያ በኋላ የተለየ ስሜት ውስጥ ይገባሉ” ሲሉ የፖሊስ መኮንኑ ለቴሌቪዥን ጣቢያው ገልጸዋል።

በዚህም አደንዛዥ እጾች በሚጠቀሙ ሰዎች ላይ የሚፈጠረው አይነት ስሜት ውስጥ እንደሚገቡ አስረድተዋል።

ጨምረውም በርካታ ሰዎች ነፍሳቱን ከያሉበት እየሰበሰቡ በዚህ ሁኔታ እየተጠቀሙባቸው በመሆኑ የጉንዳን “እጥረት” መከሰቱን ገልጸዋል።

ፖሊስ ይህንን የጉንዳን አይነት ቁጥጥር ከሚደረግባቸው የአደንዛዥ እጽ አይነቶች ዝርዝር ውስጥ ለማስገባት መገደዱም ተነግሯል።