በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቻይናውያን ግላዊ መረጃ ተሰርቆ ለሽያጭ መቅረቡ አነጋጋሪ ሆኗል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አንድ የበይነ መረብ መረጃ ሰርሳሪ ከቻይና የፖሊስ ተቋም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን መረጃ መዝብሮ ለሽያጭ ማቅረቡን ተከትሎ ጉዳዩ መነጋገሪያ ሆኗል።
ይህ አንድ ቢሊየን ይደርሳሉ የተባሉ የቻይናውያን ግላዊ መረጃ ስርቆት ዜና ይፋ ከሆነ በኋላም የአገሪቱ ፕሬዝዳንት የሕዝቡ መረጃ ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግለት አሳስበዋል።
የበይነ መረብ መረጃ ሰርሳሪዎች (ሃከርስ) ሰርቀነዋል ያሉትን የቻይናውያንን መረጃ የሚገዛቸው ካለ ለመሸጥ ማስታወቂያ ካወጡ በኋላ ነው፣ ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ሕዝባዊ ተቋማት “የመረጃ ደኅንነታቸውን እንዲያጠናክሩ” ጥሪ ያቀረቡት።
ኋላ ላይ በተነሳ እና በሕገወጥ የበይነ መረብ መድረክ ላይ በወጣው ማስታወቂያ እንደተጠቀሰው ለሽያጭ የቀረቡት ግላዊ መረጃዎች ከሻንግሃይ ብሔራዊ ፖሊስ የተሰረቁ መሆናቸው ተገልጿል።
የበይነ መረብ መረጃውን የሰረቀውና ለሽያጭ ያቀረበው ግለሰብ በእጁ ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቻይናውያን ስም፣ አድራሻ፣ የብሔራዊ መታወቂያ ቁጥር እና የሞባይል ቁጥራቸውን ጨምሮ ሌሎች መረጃዎች እንዳሉት አመልክቷል።
የበይነ መረብ መረጃ ደኅንነት ባለሙያዎችም ተሰርቀዋል ከተባሉት ግላዊ መረጃዎች ውስጥ ናሙናዎችን በመውሰድ ባደረጉት ማጣራት ስርቆቱ መፈጸሙን አረጋግጠዋል።
ከፍተኛ መጠን ያለው ይህ መረጃ 23 ቴራባይት ይሆናል ተብሎ የሚገመት ሲሆን፣ ይህም በ200 ሺህ ዶላር ለሽያጭ የቀረበ ትልቁ መረጃ ነው ተብሏል።
ድርጊቱ ወንጀል በመሆኑ ማስታወቂያው ከተለጠፈበት ድረ ገጽ ላይ እንዲነሳ ተደርጓል።
ነገር ግን ይህ ተሰረቀ ስለተባለው ግዙፍ ግላዊ መረጃ ክምችትን በተመለከተ የትኛውም የቻይና ባለሥልጣን አስካሁን በይፋ ያለው ነገር የለም። ፕሬዝዳንቱም ቢሆኑ ጉዳዩን በሚመለከት በቀጥታ ምንም አላሉም።
‘ሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት’ የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው ፕሬዝዳንት ዢ፣ ዜጎች ለሕዝባዊ አገልግሎቶች ግላዊ መረጃዎችን ሲሰጡ ደኅንት እንዲሰማቸው ለማድረግ ተቋማት “ለግላዊ መረጃዎች እና ለምስጢራዊ የተቋማት መረጃዎች ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደረጉ” አሳስበዋል።

ተሰረቀ ስለተባለው ግዝፍ መረጃ ሽያጭን በተመለከተ የወጣውን የበይነ መረብ ማስታወቂያ ተከትሎ የገጹ ተቆጣጣሪዎች የሚከተለውን ጽሁፍ አስፍረው በኋላም ማስታወቂያውን አንስተውታል።
“የተወደዳችሁ ቻይናውያን ተጠቃሚዎች፣ እንኳን ወደ መድረካችን በደህና መጣችሁ። ብዙዎቻችሁ ወደ እዚህ ገጽ የመጣችሁት ከሻንግሃይ ፖሊስ ባፈተለኩ መረጃዎች ምክንያት ነው። መረጃው ከዚህ በኋላ ለሽያጭ አይውልም፣ በተጨማሪም ከዚሁ ጉዳይ ጋር የሚያያዙ ርዕሶች በሙሉ ከገጹ ላይ እንዲሰረዙ ተደርገዋል” ብሏል።
የድረ ገጹ ተቆጣጣሪዎች ጨምረውም ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸው ሌሎች የቻይና መረጃዎች እጃቸው ላይ እንዳሉና ለሽያጭም ሊያቀርቧቸው እንደሚችሉ አሳውቀዋል።
“ያለነው ቻይና ውስጥ አይደለም፣ ቻይናውያንም አይደለንም። ስለዚህም ለቻይና ሕጎች ተገዢ መሆን የለብንም” ሲሉ ስለማንነታቸው ድፍን ያለ ምላሽ ሰጥተዋል።
በበይነ መረብ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የሚከታተለው ‘ዳርክትሬሰር’ የተባለው ቡድን እንዳለው ይህ የመረጃ ምዝበራ ከፍተኛ ትኩረትን ስቧል።
ይህም ምናልባት በቻይናውያን መረጃ ላይ ተፈጽሟል በተባለው ስርቆት አማካይነት በተፈጠረው ትኩረት የተነሳሳ ነው የተባለ ሌላ የበይነ መረብ መረጃ መዝባሪ ተመሳሳይ የሽያጭ ማስታወቂያ አውጥቷል።
በዚህም የበይነ መረብ መረጃ ሰርሳሪው እዚያው ቻይና ውስጥ ከሚገኘው የሄናን ግዛት ብሔራዊ ፖሊስ የመረጃ ቋት የመዘበረው የ90 ሚሊዮን ሰዎች መረጃዎች እጁ ላይ እንዳለ ገልጿል።
ነገር ግን ይህ ምን ያህል እውነት እንደሆነ በበይነ መረብ ደኅንነት ባለሙያዎች አልተረጋገጠም።
ባለሙያዎች ይህ ተሰረቀ የተባለው ከፍተኛ መጠን ያለው መረጃ ጉዳይ ለቻይና ባለሥልጣናት ዋነኛ አሳሳቢ ጉዳይ እንደሆነ፣ የሽያጭ ማስታወቂያውን በተመለከተ በአገሪቱ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ የሚደረጉ ውይይቶች ማገዳቸውን በመጥቀስ ተናግረዋል።
በዘርፉ ደኅንት ጉዳዮች ላይ የሚሰራው የ‘ፎሬንሲክ ፓዝዌይ’ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዴብ ሌሪ እንደሚያምኑት፣ መረጃው ከፍተኛውን ክፍያ ላቀረበ ወገን ተሽጧል ወይም የበይነ መረብ ሰርሳሪዎቹ እንዲህ አይነት ግላዊ መረጃን የሚፈልጉ ወደ እነሱ እንዲመጡ ለማስተዋወቅ ተጠቀሙበት ዘዴ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
ምክንያቱም “ድርጊታቸው የቻይና መንግሥት ባለሥልጣናትን ሊያስቆጣ እንሚችል ብዙም አላሳሰባቸውም” ብለዋል።
ባለፈው ሚያዝያ ወር በይነ መረቦችን ሰብሮ በመግባት መረጃዎችን የሚመዘብረው ‘ራይድ ፎረምስ’ የተባለው ድረ ገጽ በአሜሪካው የፌደራል ደኅንነት መሥሪያ ቤት መሪነት በተካሄደ ዓለም አቀፍ የፖሊስ ዘመቻ በቁጥጥር ስር ውሎ እንዲዘጋ ተደርጓል።
በዚህም ፖርቱጋላዊው የድረ ገጹ መስራች እና አንድ ብሪታኒያዊ ግለሰብ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል።
አሁን ቻይና ውስጥ ተሰርቋል የተባለው አይነት ከፍተኛ መጠን ያለው የግሰቦች ግላዊ መረጃዎች፣ ትክክለኛ ባለቤቶቹን አስመስሎ መልዕክት ለመላክ እና ሌሎች መጥፎ ድርጊቶችን በመፈጸም ወንጀለኞች ገንዘብ ለማግኘት ጥቅም ላይ ሊያውሉት ይችላል።
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የቻይናውያን ግላዊ መረጃ መሰረቁን በተመለከተ የተለያዩ መላምቶች እየቀረቡ ሲሆን፣ በትክክል ይህን ያህል ግዙፍ መረጃ በሰርሳሪዎች እጅ ከገባ አስካሁን ካጋጠሙ የመረጃ ምዝበራዎች ሁሉ የላቀው ነው ተብሏል።
















