የበይነ መረብ ጥቃት አድራሹ ቡድን በቢትኮይን 70 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፈለው ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
'ኮሎሳል' በሚል ከሚታወቀው የኮምፒውተር መረጃ ጥቃት ጀርባ ያለ ቡድን በቢትኮይን (ዲጂታል መገበያያ) 70 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፈለው ጠየቀ።
'ዘ ሬቭል' የተባለው ይህ ቡድን የኮምፒውተር መረጃ ጥቃት መጀመሪያ ላይ የሰነዘረው አሜሪካ ውስጥ ባለ 'ካስያ' የተባለ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተቋም ላይ ነበር። ከዚያ ግን ከአንድ ሚሊዮን በላይ የኮምፒውተር ሥርዓቶችን ማጥቃቱን ቡድኑ አስታውቋል።
ቡድኑ የጠየቀው ገንዘብ ሲከፈለው፤ የግል መረጃቸውን ያገደባቸው ሰዎች መረጃቸውን እንዲያገኙ እንደሚፈቅድ ገልጿል።
ቡድኑ የኮምፒውተር መረጃ ጥቃት ያደረሰው በምን ያህል ሰዎች እንደሆነ በግልጽ አይታወቅም። ሆኖም ግን ስዊድን ውስጥ የሚገኙ 500 መደብሮች እና 11 የኒው ዚላንድ ትምህርት ቤቶች የመረጃ ምዝበራ ከተደረገባቸው መካከል ይገኙበታል።
'ሀንትረስ' የተባለው የበይነ መረብ ደኅንነት ተቋም ወደ 200 ድርጅቶች ጥቃት እንደደረሰባቸው ገምቷል።
የመጀመሪያው ጥቃት ሰለባ የሆነው ካስያ የተባለው ተቋም ወደ 40 የሚጠጉ ደንበኞቹ ጥቃት እንደተሰነዘረባቸው አረጋግጧል።
ካስያ ሶፍትዌር የሚያቀርብላቸውና ሌሎች የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ድርጅቶች አገልግሎት የሚሰጡ ተቋሞች ስላሉ ጥቃቱ መጠነ ሰፊ ነው ተብሎ ይገመታል።
የካስያ ዋና ኃላፊ ፍሬድ ቮካላ ለኤሶሺየትድ ፕሬስ ዜና ወኪል እንደተናገሩት፤ የበይነ መረብ ጥቃት የደረሰባቸው ግለሰቦች እና ድርጅቶች ወደ 1 ሺህ ሊጠጉ ይችላሉ። ይህም ቤተ መጻሕፍት እና የጥርስ ሐኪም ቤቶችን ጨምሮ ነው።
በሺዎች የሚቆጠሩ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተቋሞች ይህ ጥቃት ከባድ ራስ ምታት ሆኖባቸው ነበር። አሁንም ስጋቱ አልተወገደም።
የግል እንዲሁም የሕዝብ የበይነ መረብ ደኅንነት ተሟጋቾች እንዴት ጥቃቱን መከላከል እንደሚቻል መረጃ ሲሰጡ ነበር።
ይህም ተጨማሪ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች የጥቃቱ ሰለባ እንዳይሆኑ ተከላክሏል።
ጥቃቱን ለማስቆም አንድ የኔዘርላንድ ተቋም ጥረት ቢያደርግም የበይነ መረብ ጥቃት አድራሹ ቡድኑ ሬቭልን ማስቆም ሳይችሉ ቀርተዋል።
ፕሮፌሰር ሲራን ማርቲን የተባሉ የበይነ መረብ ደኅንነት ጥበቃ ባለሙያ "ይህ ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ ጥቃት ያልተጠበቀና ውስብስብ ነው" ብለዋል።
















