የሰሜን ኮሪያና የሩሲያ የመረጃ መዝባሪዎች ጥቃት በክትባት ምርምሮች ላይ

የፎቶው ባለመብት, BBC/GETTY IMAGES
በሰሜን ኮሮያና በሩሲያ መንግሥታት የሚደገፉ የመረጃ መረብ መዝባሪዎች (ሃከርስ) ለኮሮናቫይረስ ክትባት ለማግኘት የሚሰሩ ተቋማትን ኢላማ እንዳደረጉ ማይክሮሶፍት ገለጸ።
ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ማይክሮሶፍት እንዳለው በቅጽል ስም "ፋንሲ ቤር" የተባለው የሩሲያ ቡድንና "ዚንክ" እንዲሁም "ሲሪየም" የተባሉት ሁለት የሰሜን ኮሪያ የመረጃ መረብ ሰርሳሪ ቡድኖች በቅርቡ ከተደረሰባቸው ጥቃቶች ጀርባ እንዳሉ ተጠቁሟል።
የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የመረጃ ደኅንነት ማዕከል ቀደም ሲል የሩሲያ የመረጃ መረብ መዝባሪዎች በክትባት ላይ በሚደረጉ ምርምሮች ላይ ትኩረት አድርገው ጥቃት ለመፈጸም እየሞከሩ መሆኑን አስታውቆ ነበር።
ነገር ግን ሩሲያ በወቅቱ በድርጊቱ ውስጥ እጇ እንደሌለበት አሳውቃ ነበር።
የመረጃ መረብ ደኅንነትን ለመጠበቅ የሚረዱ ሶፍትዌሮችን የሚሰራው ማይክሮሶፍት እንደገለጸው፤ የሰባት መድኃኒት አምራች ኩባንያዎችን የኮምፒውተር ሥርዓት ሰብሮ ለመግባት የተደረጉ ሙከራዎችን ተከላክሏል።
በተጨማሪም ክትባት ለማግኘት በካናዳ፣ በፈረንሳይ፣ በህንድ፣ በደቡብ ኮሪያ እና በአሜሪካ ጥረት የሚያደርጉ የምርምር ተቋማትም ኢላማ መደረጋቸው ተጠቁሟል።
ማይክሮሶፍት ጨምሮም መረጃዎችን ለመመዝበር እየጣረ ያለው የሩሲያው ቡድን ኢላማ የተደረጉትን ተቋማት አካውንቶች ሰብሮ ለመግባት በሚያደርገው ሙከራ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የይለፍ ቃሎችን በመጠቀም ከባድ የተባለውን ዘዴ እንደተጠቀመ ገልጿል።
ከሰሜን ኮሪያ ናቸው ከተባሉት ሰርሳሪ ቡድኖች አንደኛው ከዓለም የጤና ድርጅት ባለስልጣናት ከአንዱ የተላከ የሚመስል ኢሜል በመላክ ኢላማ የተደረጉትን ተቋማት የኮምፒውተር ሥርዓት ሰብሮ ለመግባት የሚያስችል መረጃን ለማግኘት ሙከራ ማድረጉም ተደርሶበታል።
ማይክሮሶፍት እንዳለው የተቋማት የኮምፒውተር ሥርዓት ሰብሮ ለመግባት ከተደረጉት ሙከራዎች መካከል አንዳንዶቹ ሳይሳኩ የቀሩ ቢሆንም፤ አንዳንዶቹ ግን ተሳክተዋል ብሎ አስጠንቅቋል።
ሩሲያ ቀደም ሲል የክትባት ምርምሮችን ኢላማ አድርጋለች የተባለውን ክስ ማስተባበሏ ይታወሳል። በአሜሪካ ዋሽንግተን የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ለሮይተርስ በአሁኑ ወቅት በጉዳዩ ላይ ከቀደመው የተለየ መረጃ እንደማይሰጥ ገልጿል።
















