በአሜሪካ በተፈጸመ የመረጃ መረብ ጥቃት 50 ድርጅቶች ተጎድተዋል

የፎቶው ባለመብት, EPA
በአሜሪካ መንግሥት ተቋማት ላይ የደረሰውን ከፍተኛ የሆነ የሳይበር ጥቃት ወደ 50 የሚጠጉ መሥሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት አድርሷል ተባለ።
የፋየር አይ ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑት ኬቨን ማንዲያ፣ ይህንን የሳይበር ጥቃት ያደረሱ አካላት 18 ሺህ ተቋማት ላይ ቫይረሶችን የላኩ ቢሆንም 50ዎቹ ግን ከፍተኛ የሆነ ጉዳት አስተናግደዋል ብለዋል።
በዚህ የሳይበር ጥቃት ኢላማ ከሆኑ የአሜሪካ ተቋማት መካከል፣ የአሜሪካ ግምጃ ቤትና የንግድ ሚኒስቴር፣ መከላከያ እንዲሁም የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ይገኙበታል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ከጥቃቱ ጀርባ ሩሲያ አለች ሲሉ መክሰሳቸው ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሩሲያ እጇ አለበት መባሉን ጥያቄ ውስጥ የሚከትና ቻይናን ተጠያቂ የሚያደርግ የትዊተር መልዕክት በሰሌዳቸው ላይ ቅዳሜ ዕለት ለጥፈዋል።
ማንዲያ ግን ለአሜሪካው ሲቢኤስ የዜና ተቋም ይህ የሳይበር ጥቃት "በተከታታይ የደረሰ" እንደነበር በመግለጽ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ስለሩሲያ የውጭ ደኅንነት ተቋም ኤስቪአር እውቀት እንዳላቸው ገልፀዋል።
"እነዚህ በ1990ዎቹ እንዲሁም በ2000 የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ምላሽ የሰጠናቸው ቡድኖች ናቸው። በሳይበሩ ዓለም ያለ ቀጣይ ጨዋታ ነው" ብለዋል።
መቀመጫውን ቴክሳስ ግዛት ውስጥ ባደረገውና በአሜሪካ ሶፍትዌር አምራች ድርጅት ሶላርዊንድስ የተሰራ ሶፍትዌር ላይ ያነጣጠረው ይኸው ጥቃት ለዚህ አንድ ማሳያ ነው ብለዋል።
የጥቃቱ ኢላማ ከሆኑ የአሜሪካ ድርጅቶች የኒውዩክሊር መሳሪያዎችን የሚያስተዳድረው መሥሪያ ቤት ይገኝበታል። የመንግሥት ተቋም የሆነው የአሜሪካ ኢነርጂ ቢሮ በጥቃቱ "የጦር መሳሪያ ደኅንነቱ አልተደፈረም" ብሏል።
ከጥቃቱ ጀርባ ያሉ ጠላፊዎች የብሔራዊ ደኅንነት፣ የመከላከያ እና ሌሎች ተዛማጅ መረጃዎችን ለመስረቅ ሲሉ የተወሰኑ ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ ናቸው ተብሎ ይታሰባል።
ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በርካታ በዓለም ላይ የሚገኙ ድርጅቶችም ተመሳሳይ የኔትወርክ አስተዳዳር ሶፍትዌር በመጠቀም በመረጃ ጠላፊዎች ዒላማ መሆናቸው ተሰምቷል።
የጠለፋውን ስያሜ 'ሰንበርስት' ሲሉ ስያሜ የሰጡት ተመራማሪዎች፤ ከመቼውም ጊዜ በላይ አስከፊ የተባለውን የሳይበር ጥቃት ሙሉ ለሙሉ ለመረዳት ዓመታት ሊወስድ ይችላል ብለዋል።
የአሜሪካ የበይነ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (Cisa) የመረጃ መረብ ሰርሳሪዎቹ የኮምፒውተር ኔትዎርኮችን ሰብረው መግባት የቻሉት መቀመጫውን ቴክሳስ ባደረገ የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ኩባንያ በሆነው ሶላርዊንድስ ሶፍትዌር ተጠቅመው መሆኑን ገልጿል።
ከ300 ሺህ የሶላርዊንድስ ኦሪዮን ሶፍትዌር ተጠቃሚዎች መካከል 18ሺ የሚሆኑት ጥቃት ሳይደርስባቸው እንዳልቀረም ተነግሯል። ይሁን እንጂ የተወሰደ የግለሰብም ሆነ የደንበኞች መረጃ ስለመኖሩ የሚያመላክት ነገር የለም።
ተመራማሪዎች በሶላርዊንድስ አማካኝነት ወራትን የፈጀው ጥቃት የጀመረው ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ከሞስኮ ጋር የተገናኙ ጠላፊዎች የአሜሪካን ምስጢሮች ለመስረቅ እንደሞከሩ ይታመናል።
ከአንድ ወር በኋላ ወደ ዋይት ሐውስ የሚገቡት ተመራጩ ፕሬዚደንት ጆ ባይደንም የሳይበር ደኅንነት ጉዳይ "መንግሥቴ እጅግ አንገብጋቢ ከሚላቸው አጀንዳዎች አንዱ ነው" ብለዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ በአሜሪካ መንግሥት ላይ ለተፈፀመው "አደገኛ" የሳይበር ጥቃት ሩሲያን ተጠያቂ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ሚኒስትሩ "በዚህ ድርጊት ላይ የተሳተፉት ሩሲያዊያን መሆናቸውን መናገር እንችላለን" ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለአንድ ራዲዮ በሰጡት በዚሁ ቃለመጠይቃቸው "ሩሲያ ለወራቶች በመላው ዓለም ያሉ ድርጅቶችን ጨምሮ በርካታ የአሜሪካ መንግሥት ተቋማት እና የግል ድርጅቶችን ዘልቃ እንደገባች አምናለሁ" ብለዋል።
አክለውም በአሜሪካ የመንግሥት ሥርዓት ውስጥ ኮድ ለማስገባት የሦስተኛ ወገን ሶፍትዌርን ለመጠቀም ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ እንደነበርም ተናግረዋል።
















