ሳይበር ጥቃት፡ በአሜሪካ ከተፈፀመው የሳይበር ጥቃት ጀርባ ሩሲያ እንዳለች ማይክ ፖምፒዮ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ በአሜሪካ መንግሥት ላይ ለተፈፀመው 'አደገኛ' የሳይበር ጥቃት ሩሲያን ተጠያቂ አደረጉ።
ሚኒስትሩ አርብ ዕለት በሰጡት ቃለ ምልልስ "በዚህ ድርጊት ላይ የተሳተፉት ሩሲያዊያን መሆናቸውን በግልፅ መናገር እንችላለን" ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለአንድ ራዲዮ በሰጡት በዚሁ ቃለመጠይቃቸው "ሩሲያ ለወራቶች በመላው ዓለም ያሉ ድርጅቶችን ጨምሮ በርካታ የአሜሪካ መንግሥት ተቋማት እና የግል ድርጅቶችን ዘልቃ እንደገባች አምናለሁ" ብለዋል።
አክለውም በአሜሪካ የመንግሥት ሥርዓት ውስጥ ኮድ ለማስገባት የሦስተኛ ወገን ሶፍትዌርን ለመጠቀም ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ እንደነበርም ተናግረዋል።
ውስብስብ በተባለው በዚህ የሳይበር ጥቃት ዒላማ ከሆኑት የአሜሪካ ኢነርጂ ቢሮ እና ፌደራል መሥሪያ ቤቶች በተጨማሪ የመከላከያ ፣ የአገር ውስጥ ደኅንነት (ሆምላንድ ሴኩሪቲ)፣ የአሜሪካ ግምጃ ቤትና ንግድ ሚኒስቴር ዳታዎች ዒላማ ተደርገዋል።
ፖምፒዮ ጥቃቱን እየተመለከቱ ያሉ የአሜሪካ ተመራማሪዎች አሁንም የተፈጠረው ምን እንደሆነ እያጠኑ መሆኑን ጠቅሰው "አብዛኛው መረጃም በምስጢር ሊቆይ ይችላል" ብለዋል።
ሚኒስትሩ "ሩሲያ የአኗኗር ዘይቤያችንን ለማዳከም እሞከረች ነው፤ የሩሲያ ፕሬዚደንትም አደጋ ናቸው" ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው "በቁጥጥር ሥር ውሏል" ሲሉ የጥቃቱን 'አደገኛ' መባል አጣጥለውታል። ትራምፕ በንግግራቸው በድርጊቱ የቻይና እጅ እንዳለበት ፍንጭ የሰጡ ሲሆን በሩሲያ ሚና ላይ ግን ጥርጣሬን አሳድረዋል።
ሩሲያም በጥቃቱ ተሳትፋለች በሚል የቀረበባትን ክስ ተቃውማለች።
በአሜሪካ ሶፍትዌር አምራች ድርጅት ሶላርዊንድስ የተሰራ ሶፍትዌር ላይ ያነጣጠረው ይኸው ጠለፋ የተደረሰበት ባሳለፍነው ሳምንት ነበር። ይሁን እንጂ ኦፕሬሽኑ ለወራቶች ሲካሄድ ነበር ተብሏል።
የጥቃቱ ኢላማ ከሆኑ የአሜሪካ ድርጅቶች የኒውዩክሊር መሳሪያዎችን የሚያስተዳድረው መሥሪያ ቤት ይገኝበታል። የመንግሥት ተቋም የሆነው የአሜሪካ ኢነርጂ ቢሮ በጥቃቱ "የጦር መሳሪያ ደህንነቱ አልተደፈረም" ብሏል።
ከኦፕሬሽኑ ጀርባ ያሉ ጠላፊዎች የብሔራዊ ደህንነት፣ የመከላከያ እና ሌሎች ተዛማጅ መረጃዎችን ለመስረቅ ሲሉ የተወሰኑ ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ ናቸው ተብሎ ይታሰባል።
ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በርካታ በዓለም ላይ የሚገኙ ድርጅቶችም ተመሳሳይ የኔትወርክ አስተዳዳር ሶፍትዌር በመጠቀም በጠላፊዎች ዒላማ መሆናቸው ተሰምቷል።
የጠለፋውን ስያሜ 'ሰንበርስት' ሲሉ ስያሜ የሰጡት ተመራማሪዎች፤ ከመቼውም ጊዜ በላይ አስከፊ የተባለውን የሳይበር ጥቃት ሙሉ ለሙሉ ለመረዳት ዓመታት ሊወስድ ይችላል ብለዋል።
የአሜሪካ የበይነ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (Cisa) በርባሪዎቹ የኮምፒውተር ኔትዎርኮችን ሰብረው መግባት የቻሉት መቀመጫውን ቴክሳስ ባደረገ የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ኩባንያ በሆነው ሶላርዊንድስ ሶፍትዌር ተጠቅመው መሆኑን ገልጿል።
ከ300 ሺህ የሶላርዊንድስ ኦሪዮን ሶፍትዌር ተጠቃሚዎች መካከል18ሺ የሚሆኑት ጥቃት ሳይደርስባቸው እንዳልቀረም ተነግሯል። ይሁን እንጂ የተወሰደ የግለሰብም ሆነ የደንበኞች መረጃ ስለመኖሩ የሚያመላክት ነገር የለም።
ተመራማሪዎች በሶላርዊንድስ አማካኝነት ወራትን የፈጀው ኦፕሬሽን የጀመረው ባሳለፍነው መጋቢት ወር ላይ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ከሞስኮ ጋር የተገናኙ ጠላፊዎች የአሜሪካን ምስጢሮች ለመስረቅ እንደሞከሩ ይታመናል።
ከአንድ ወር በኋላ ወደ ዋይት ሃውስ የሚገቡት ተመራጩ ፕሬዚደንት ጆ ባይደንም የሳይበር ደህንነት ጉዳይ መንግሥቴ እጅግ አንገብጋቢ ከሚላቸው አጀንዳዎች አንዱ ነው ብለዋል።












