መረጃ መንታፊው የትራምፕን ‘ፓስወርድ’ በትክክል ገምቶ ወደ ትዊተራቸው ገብቶ እንደነበረ ተገጸ

ፕሬዝደንት ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, REUTERS/WHITE HOUSE/BBC

የኔዘርላንድስ ዐቃቤ ሕግ አንድ መረጃ መንታፊ የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የትዊተር የይለፍ ቃልን በትክክል በመገመት ወደ ትዊተራቸው መግባት መቻሉን አረጋገጠ።

ሃከሩ በትክክል መገመት የቻለው የፕሬዝደንት ትራምፕ የትዊተር ፓስዎርድ - “MAGA2020!” የሚል ነው።

ቪክተር ጌቬርስ የተባለው ሃከር ፓስዎርድ ገምቶ ወደ ፕሬዝደንቱ የትዊተር አካውንት ዘልቆ መግባቱ አያስከስሰውም ተብሏል።

የኔዘርላንድስ ዐቃቤ ሕግ ቪክተር ይህን የፈጸመው “ስነ-ምግባርን” በተከተለ መንገድ ነው ብሏል።

ቪክተር ወደ ፕሬዝደንቱ ትዊተር አካውንት መግባቱን ያስታወቀው ጥቅምት 12 ላይ ሲሆን ለዚህም ማረጋገጫ ይሆኑት ዘንድ ‘ስክሪንሾትስ’ አጋርቶ ነበር።

በወቅቱ ግን ዋይት ሃውስ የፕሬዝደንቱ የትዊተር አካውንት ‘ሃክ’ አልተደረገም ሲል ትዊተር በተመሳሳይ የትራምፕ አካውንት ሃክ ስለመደረጉ ምልክት የለም ብሎ ነበር።

የኔዘርላንድስ ዐቃቤ ሕግ ቪክተር ወደ ፕሬዝደንቱ አካውንቱ መግባቱን አረጋግጫለሁ ካለ በኋላም ቢሆን ትዊተር ለዚህ ማረጋገጫ ማግኘት አልቻልኩም ብሏል።

ትዊተር የእውቅ ሰዎች እና ከአሜሪካ ምርጫ ጋር በተያያዘ መረጃ የሚያወጡ የትዊተር አካውንቶች ደህንነት የተጠበቀ ስለመሆኑ ለማረጋገጥ ተጨማሪ ጥብቅ እርምጃዎችን ሲወስድ ቀሞየቱን አስታውቋል።

ከኔዘርላንድ ዐቃቤ ሕግ ማረጋገጫ በኋላ ዋይት ሃውስ በጉዳዩ ላይ ያለው ነገር ይለም።

ቪክተር ጌቬርስ በሳይበር ደህንነቶች ላይ ጥናት በማከናወን ዝናን የታረፈ ሲሆን የሚሰራቸው የጥናት ስራዎች የሳይበር ደህንነትን እንዴት ማረጋገጥ እንደሚቻል የሚጠቁሙ ናቸው።

ቪክተር ከአራት ዓመታት በፊትም በተመሳሳይ እርሱ እና ጥናት አድራጊ አጋሮቹ የፕሬዝደንት ትራምፕ የይለፍ ቃል “yourefired” በትክከል በመገመት ወደ ትዊተር አካውንታቸው መግባት ችለው እንደነበረ ተናግሯል።

ቪክተር የፕሬዝደንቱን የትዊተር የይለፍ ቃል በትክክል መገመቱም እንዳስደሰተው ተናግሯል።

“ይህ ለግል ጥረቴ ብቻ ሳይሆን በኢንተርኔት ላይ የሰዎችን ተጋላጭነት ለመቀነስ በበጎ ፍቃድ ለሚሰሩ ሁሉ ደስታን የሚሰጥ ነው'' ብሏል። ትራምፕ በግል ከሰዎች ጋር ይለዋወጡት የነበረውን መልዕክት እና ፎቶግራፎች እንዲሁም፤ ትራምፕ “ብሎክ” ያደረጓቸውን ሰዎች ዝርዝር ጭምር ቪክተር ሳይመለከት አልቀረም ተብሏል።

የኔዘርላንድስ ፖሊስ በምርመራው ያገኘውን መረጃ ለአሜሪካ ባለስልጣናት ልኳል። ፕሬዝደንት ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው ላይ 89 ሚሊዮን ተከታዮች አሏቸው