ከ600 ኪ.ግ በላይ ኮኬይን የጫነች ጀልባ በባህር ዳርቻ ላይ በፖሊስ ተያዘች

ባህር ዳርቻ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በማርሻል ደሴቶች ፖሊስ በታሪኩ ከፍተኛው የተባለ በኮኬይን የተሞላ ጀልባ ብቻውን ሲንሳፈፍ ማግኘቱን አስታውቋል።

ፖሊስ እንዳስታወቀው ኮኬይን የጫነችው ጀልባ ከላቲን አሜሪካ እንደሆነች የተገመተ ሲሆን ጀልባዋ በፓሲፊክ ውቂያኖስ አካባቢ ለወራት ውሀ ላይ እንደቆየችም ግምት አለ ብሏል።

ጀልባዋ ውስጥ የተገኘው ኮኬይን 649 ኪሎ ግራም የሚመዝን ሲሆን ይህ አደንዛዥ እጽ ለገበያ ቢቀርብ እስከ 80 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ሊያወጣ ይችል ነበር ተብሏል።

በፓሰፊክ ውቂያኖስ ላይ በሚገኙ ደሴቶች አቅራቢያ በተመሳሳይ በኮኬይን የተሞሉ ጀልባዎችን ማግኝት የተለመደ ነገር እንደሆነ ፖሊስ አስታውቆ የዚህኛው ግን ከሌሎቹ በተለየ ከፍተኛ መጠን ያለው እንደሆነ ገልጿል።

ፖሊስ ጀልባዋ ላይ ከተገኘው ኮኬይን ሁለት እሽግ ለምርመራ ወደ አሜሪካ እንዲላክ ተደርጓል ብሏል።

5.5 ሜትር እርዝማኔ ያላት ጀልባ በአካባቢው ነዋሪዎች ነበር መጀመሪያ ላይ የታየችው። ነዋሪዎቹ ጀልባዋን ከውሃው ለማውጣት ጥረት ሲያደርጉ ከአቅማቸው በላይ ሲሆንባቸው ነው ለፖሊስ ያመለከቱት።

ፖሊስ በቦታው ከደረሰ በኋላ ምርመራ ሲያደርግ በሁለት ድብቅ ቦታዎች 649 ኪሎግራም የሚመዝነው ኮኬይን ተደብቆ አጊንቷል።

የማርሻል ደሴቶች ዐቃቤ ሕግ ሪቻርድ ሂክሰን እንዳሉት ጀልባዋ ለወራት ምናልባትም ከአንድ ዓመት በላይ በውሃ ላይ ስትንሳሰፈፍ ቆይታለች ካሉ በኋላ መነሻዋም ከማዕከላዊ አልያም ከደቡባዊ አሜሪካ አገራት ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።

በተመሳሳይ መልኩ በኮኬይን የተሞሉ ጀልባዎች ተንሳፈው ሲገኙ ብዙውን ጊዜ የአካባቢው ነዋሪዎች ለፖሊስ ከማሳወቅ ይልቅ አደንዛዥ እጹን ይሸጡታል። ባለስልጣናት እንደገለጹት ይህ ተግባር በደሴቶቹ የአደንዛዥ እጽ ተጠቃሚዎችን ቁጥር እንዲጨምር እና በኮኬይን ምክንያት ሆስፒታል የሚገቡ ሰዎችም ቁጥር ክፍ እንዲል እያደረገ ነው።

ዐቃቤ ሕግ ሪቻርድ ሂክሰን በዚህ ወቅት ግን ነዋሪዎቹ በኮኬይን የተሞለውን ጀልባ ለፖሊስ አሳልፈው መስጠታቸውን በመግለጽ ምስጋናቸውን ችረዋቸዋል።

በአውሮፓውያኑ 2014 ላይ አንድ የኤል ሳልቫዶር ዜግነት ያለው ግለሰብ በጀልባ ውስጥ ሆኖ ኤቦን አቶል በምትባል ደሴት አካባቢ ተገኝቶ ነበር። እሱ እንደሚለውም ለ13 ወራት ባህር ላይ ጠፍቶ ቆይቷል።

በውሃ ላይ ባሳለፋቸው 13 ወራትም በእጁ አሳ፣ ወፎች እንዲሁም የባህር ኤሊዎችን እየያዘ ይመገብ እንደነበር ገልጿል።