ሎከርቢ ሰማይ ላይ በጋየው አውሮፕላን ጉዳይ ሊቢያዊው ተላልፎ እንዲሰጣት አሜሪካ ልትጠይቅ ነው

የተከሰከሰው አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካ በሎከርቢው ሰማይ ላይ በጋየው አውሮፕላን ጉዳይ ሊቢያዊው ተላልፎ እንዲሰጣት ልትጠይቅ ነው

ከ32 ዓመት በፊት በስኮትላንድ ሎከርቢ ሰማይ ላይ የፈነዳውን የፓን አም አውሮፕላን በረራ ቁጥር 103 እንዲጋይ ቦንብ ቀምሟል ባለችው ሊቢያዊ ላይ አዲስ ክስ ልትመሰረት መሆኑን የአሜሪካ ጋዜጦች ዘገቡ።

ዘገባዎች እንደሚሉት አቡ አጊላ መሐመድ የተባለው ሰው ወደ አሜሪካ ተላልፎ እንዲሰጥና ለፍርድ እንዲቀርብ የአሜሪካ ዐቃቢ ሕግ በቅርቡ ጥያቄ ያቀርባል።

አቡ አጊላ አሁን የሚገኘው በሊቢያ እስር ቤት ነው የሚል ጠርጣሬ አለ።

አሁን ክሱ ሊንቀሳቀስ የቻለውም ድርጊቱን ስለመፈጸሙ ለሊቢያ ባለሥልጣናት በ2012 ዓ/ም ተናዟል የሚል መረጃ በመገኘቱና የሰውየውም በጊዜው የነበረው የጉዞ ታሪክ ይህንኑ ያሳብቃል ተብሎ በመታመኑ ነው።

የዛሬ 32 ዓመት በስኮትላንድ ከተማ ሎከርቢ ሰማይ ላይ የጋየው አውሮፕላን ተሳፍረውበት የነበረው 270 ሰዎችን በሙሉ የጨረሰ ነበር።

ከተሳፋሪዎችም መካከል 190 የሚሆኑት ከለንዶን ወደ ኒውዮርክ እየተጓዙ የነበሩ አሜሪካዊያን ነበሩ።

እስከዛሬ በዚህ የአሸባሪዎች ጥቃት ክስ የተመሰረተበት የሊቢያ ዜግነት ያለው አብዱልባሲጥ አል መግራሂ ሲሆን ይህም በ2001 በኔዘርላንድስ የተከፈተበት ክስ ነበር።

አልመግራሂ ግን ድርጊቱን በፍጹም አልፈጸምኩም ሲል ተከራክሯል። ለሞት የሚያበቃ ካንሰር ስለነበረበትም በ2012 ወደ አገሩ ሊቢያ እንዲመለስ ተፈቅዶለት እዚያው በትሪፖሊ ሕይወቱ አልፋለች።

አሁን በሚስተር መስኡድ የሚከፈተው አዲስ ክስ ለሦስት ዐሥርታት ምስጢር ሆኖ የቆየውንና በታሪክም ረዥም ጊዜ ፈጀ በሚባለው የሽብር ምርመራ አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል ነው የተባለው።

ሚስተር መስኡድ በትክክል የት እንዳለ እንደማይታወቅ የገለጸው ኒው ዮርክ ታይምስ በሊቢያ ከዚህ ጥቃት ጋር ባልተያያዘ ክስ እስር ቤት እንደሚገኝ አስቀምጧል።

የአሜሪካ መርማሪዎችም እሱን የመረመሩ ሊቢያዊያን የደህንነት ሰዎችን በቱኒዚያ አግኘተው መርምረዋቸዋል የሚል መረጃ ዎልስትሪ ጋዜጣ አስነብቧል።

ሚስተር መስኡድ የሟቹ ሙአመር ጋዳፊ ሁነኛ የቦምብ ቀማሚ እንደነበር ይነገርለታል።

በጉዳዩ ላይ እስካሁን የሊቢያ ባለሥልጣናት በይፋ ያሉት ነገር የለም።

የአሜሪካና የእንግሊዝ መርማሪዎች ሟቹንና ብቸኛውን ተጠርጣሪ መግራሂን የከሰሱት በ1991 ሲሆን ሊቢያ ግን እስከ 1999 ሰውየውን አሳልፋ አልሰጠችውም ነበር።

በግንቦት 2000 ዓ/ም በኔዘርላንድስ ክሱ መታየት ጀመረ። ከዚያም በጥር 2011 ይህ የሊቢያ ደህንነት ሰው ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ እድሜ ይፍታህ ተበየነበት።

በተደጋጋሚ ክሱን ሲያስተባብል ቆይቶ በከፍተኛ የካንሰር ሕመም መታመሙ ስለተረጋገጠ ከእስር እንዲፈታ ሆነ። ወደ አገሩ ሊቢያ በመመለስም በ2012 ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

ጋዳፊ አገራቸው ለቦምብ ጥቃቱ ኃላፊነት እንደምትወስድ ገልጸው ለሟች ቤተሰቦች ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የካሳ ገንዘብ መክፈላቸው ይታወሳል። ሆኖም ጥቃቱን እሳቸው ስለማዘዛቸው ሳያምኑ ነው የተገደሉት።