ቴሌሜዲሲን ምንድነው? የርቀት ሕክምና በኢትዮጵያ ይሠራል?

አቶ አብዲ ድንገታ
የምስሉ መግለጫ, አቶ አብዲ ድንገታ

አንድ ታካሚና አንድ ሐኪም በአካል ሳይገናኙ ሕክምና ሊካሄድ ይችላል? ለዚያውም "ወሬ በዓይን ይገባል" በሚል ማኅበረሰብ ውስጥ፤ ለዚያውም በሚቆራረጠው ቀጭኑ ሽቦ?

ይህ ቴሌሜዲስን ተብሎ ይጠራል። ለመሆኑ በእኛ አገር ይህ የአማካሪዎች ሕክምና እንዴት ውጤታማ ሊሆን ይችላል?

የሰመመን ሕክምና ባለሙያና የዮኮ ቴሌሚዲስን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዲ ድንገታ፣ "እውነት ነው የማኅበረሰባችን አስተሳሰብ በዚህ ረገድ መቀየር አለበት" ይላሉ።

የማኅበረሰቡን ለሕክምና ሂደቶች የሚሰጠውን አረዳድ ሲተቹም፣ "…መርፌ ሳያዝልኝ ነው በኪኒን የላከኝ፤ ዛሬ ደግሞ ራጅ እንኳ ያላዘዘ ሐኪም ነው የገጠመኝ" ብሎ በሐኪሙ ቅር የሚሰኝ ብዙ ሰው መኖሩን አያይዘው ያነሳሉ።

"ይህ አስተሳሰብ እኛንም ፈተና ውስጥ ከቶን ነበር። አሁን ግን ኅብረተሰቡ እየለመደን ነው፤ እኛም የጤና መረጃን በጥራት በማቅረብ እምነቱን ለማግኘት እየሰራን ነው" ይላሉ።

ዮኮ የማማከር የሕክምና አገልግሎት (ቴሌሜዲሲን) የተጀመረው የኮቪድ-19 ወረርሽን ከመከሰቱ ትንሽ ቀደም ብሎ ነው።

ይሁን እንጂ በጤና ዘርፍ በተለያየ ስፍራ ይሰሩ የነበሩት መስራቾቹ የኮቪድ-19 ወረርሽኙ ከገባ ወዲህ ምሥረታውን ማፋጠን እንዳለባቸው ተሰማቸው።

ምክንያቱ ደግሞ ወረርሽኙን ተከትሎ ሆስፒታሎች እየተራቆቱ በመምጣታቸው ነው። ሰዎች ሆስፒታል መሄድ ከፈሩ በጤና ለመቆየት ሐኪማቸውን በስልክ ማግኘት አለባቸው። ይህ ሁኔታ ቀደም ብሎ ተጸንሶ የነበረውን ዮኮ ቴሌሜዴስንን አዋለደ።

"በወረርሽኙ ምክንያት ሰዎች የሆስፒታል ደጆችን መርገጥ ፈሩ። ከበድ [ክሮኒክ] በሽታ ያለባቸው ሰዎችም ሆስፒታል አይሄዱም ነበር። በዚህ የተነሳ የቴሌሜዲሲን አስፈላጊነት ከምንጊዜውም በላይ ጎልቶ ታየን" ይላሉ አቶ አብዲ።

ቴሌሜዲሲን በአገራቸው አዲስ ዘርፍ ይመስላል።

ሐሳቡ ጠቃሚ የጤና መረጃዎችን ታማሚውና ሐኪሙ በአካል ሳይገናኙ በስልክ ብቻ በመገናኘት ማቀበል ነው።

አቶ አብዲ ድርጅታቸው የሚሠራቸው ተግባራትን በአራት አምዶች ይቦድኗቸዋል።

የመጀመርያው በሽታን ማወቅና መለየት እንዲሁም ስለ ሕክምናው መወያየት ነው።

ሁለተኛው ተራ የሚመስሉ ግን ጠቃሚ መረጃዎችን ከታማሚው ጋር መወያየት ነው። "እርግጥ ነው በጤና ዘርፍ ተራ የሚባል መረጃ የለም" የሚሉት አቶ አብዲ ትንሽ የጤና ምክር ስህተት ለትልቅ አደጋ ሊያጋልጥ እንደሚችል ያወሳሉ።

ተራ የሚባል ከታማሚው የሚሰጥ መረጃም በአንጻሩ ለሐኪሙና ለሕክምናው መሳካት ትልቅ ግብአት እንደሚሆን በመግለጸወ፣ የጥቃቅን መረጃን አስፈላጊነት ያስረዳሉ።

"አንድ ሰው ከሐኪሙ ጋር ውሎ መድኃኒት ገዝቶ ቤቱ ገብቶ ስለ መድኃኒቱ አወሳሰድ ግራ ቢገባው ደውሎ ከሐኪሞቻችን ጋር ሊወያይበት ይችላል" ይላሉ።

ወይም ደግሞ አንድን የሕክምና ሂደት [ፐሮሲጀር] ለማድረግ ያሰበ ታማሚ የሕክምና ሂደቱን በተመለከተ ሊያውቃቸው የሚገቡ ቅድመ ጥንቃቄና ድኅረ ጥንቃቄዎችን ከሐኪሞቹ በተጨማሪ በስልክ ከዮኮ ሐኪሞች ሊመከር ይችላል።

ሌላው የቴሌሜዲሰን አገልግሎት አንድ ታማሚ በአካል ሆስፒታል ሄዶ ታክሞ ከሐኪሙ ጋር የነበረው ቆይታ ግን አደናጋሪ ቢሆንበትና ተጨማሪ መረጃን ቢሻ፤ ስልክ ደውሎ ይህንኑ አገልግሎት ማግኘት ይችላል። በጤና ረገድ ተጨማሪ ሐሳብ መስማት የብዙ ተማሚዎች ፍላጎት እንደሆነ ሳይዘነጋ።

ሦስተኛው የቴሌሜዲስን አገልግሎት የድንገተኛ የስልክ ሕክምና አገልግሎት ነው።

አይበለውና አንድ ሰው ቤት ውስጥ ወይም መንገድ ላይ አደጋ ቢደርስበትና በቅርብ ያለው ሰው የመጀመርያ እርዳታ ለመስጠት ፈልጎ ነገር ግን ምን ማድረግ እንዳለበት ግራ ቢገባው፤ የስልክ ጥሪ በማድረግ በዚሁ ከሰለጠኑ ሐኪሞች ዘንድ አስፈላጊውን እርዳታን ማግኘት ይችላል።

እነዚህ በአራት አምድ የቆሙ ግልጋሎቶች ከጠቅላላ ምክር አገልግሎት ጋር ማቅረብ ነው የቴሌሜዲስን ግብ።

ከአራቱ አገልግሎቶች በተጨማሪ ዮኮ ጥቅል የጤና ምክርን ለሚሹ እገዛ ይሰጣል።

Hojjattu Yookoo doktor keessaa tokko

የፎቶው ባለመብት, Yookoo Doktor

አንድ ሰው ለምሳሌ የጤና እክል ገጥሞት ነገር ግን የት ሆስፒታል መሄድ እንዳለበት፣ በየትኛው ሐኪምና ስፔሻሊስት ቢታይ እንደሚሻለው አማራጮችን ማወቅ ቢፈልግ፣ የትኞቹ በሽተኞች፣ ለየትኞቹ በሽታዎቻቸው የት መታከም እንዳለባቸው፣ በዘርፉ ያሉ ሐኪሞች መቼና የት እንደሚገኙ፣ ቀጠሮ ከማስያዝ ጀምሮ የተሟላ አገልግሎት መስጠት ተጫማሪ ተግባሩ ነው።

ዮኮ ቴሌሜዲስን በሁለት ስፔሻሊስቶችና በስድስት ጠቅላላ ሐኪሞች በመታገዝ ነው የ24 ሰዓት የስልክ የሕክምና ምክር አገልግሎት የሚሰጠው።

አንዳንድ በዘርፉ የተጠኑ የምርምር ወረቀቶ በጤናው ዘርፍ የቴሌሜዲስን ትሩፋቶች አያሌ እንደሆኑ ያወሳሉ።

ለምሳሌ የሆስፒታል መጨናነቅን ያስወግዳል፤ ታማሚዎች በሆነ ባልሆነው ክሊኖኮችን ማጨናነቃቸውን ማስቀረት ያስችላል፤ ለአቅመ ደካሞች እንግልትን ያስቀራል። በታካሚና በአካሚ መካከል መግባባትን ያሳልጣል፤ ገንዘብና ጊዜን ይቆጥባል።

ነገር ግን አተገባበሩ ጥንቃቄን የሚሻ ነው። በዚህ ረገድ ያጋጠሙ ችግሮችን ቆየት ብለን እንመለስባቸዋለን።

አቶ አብዲ ሲናገሩ፣ "ብዙ በሽታዎች በቀላል የሐኪም ምክር ብቻ ቤት ውስጥ የሚጠናቀቁ ናቸው። ሁሉም የሕመም ምልክት ሆስፒታል የሚያስኬድ ላይሆን ይችላል፤ ጊዜንም ገንዘብንም ማባከን ነው የሚሆነው፤ ዋናው ነገር ከትክክለኛ ሐኪም ትክክለኛ ምክር ከማግኘቱ ላይ ነው" ይላሉ።

ለመሆኑ ወደ ዮኮ ቴሌሜዲስን የሚመቱ የስልክ ጥሪዎች በይበልጥ ለየትኞቹ የጤና እክሎች የምክር መሻቶች የተደረጉ ናቸው?

ሥራ አስኪያጁ አቶ አብዲ የተጠና ነገር ባይኖርም ከሐኪሞቻቸው በየቀኑ ከሚሰበስቧቸው ሪፖርቶች በመነሳት ብዙዎቹ የስልክ ጥሪዎች ከባድ [ክሮኒክ] የሚባሉ በሽታዎች ካሉባቸው ሰዎች የሚደወሉ ናቸው ይላሉ።

"ባለፉት 9 ወራት ብቻ ከ5ሺህ በላይ የስልክ ጥሪዎችን ተቀብለናል። በአንደኛ ደረጃ ሊቀመጥ የሚችለው ክሮኒክ የሆኑ ሰው ላይ ለብዙ ጊዜ አብረው የሚቆዩ በሽታዎችና በእነዚህ በሽታዎች የታመሙ ሰዎች የሚደረጉ ናቸው።"

ይሄ በሽታ ምን ያመጣብኝ ይሆን? ይሄን መድኃኒት ብወስድስ/ባልወስድስ? የሚሉ አይነት ጥያቄዎች በብዛት እንደሚቀርቡላቸው ለቢቢሲ አብራርተዋል።

የስኳር በሽታ ያለበት ሰው ለምሳሌ ምን ብመገብ ትክክል ነው፣ ይህንና ያንን መድኃኒት ብወስድ ምን ተጓዳኝ ችግር ያስከትልብኛል፤ በሚሉና ከመድኃኒት አወሳሰድ ጋር በተያያዘም ብዙ ሰዎች ስልክ ይደውላሉ።

ሁለተኛው ወላጆች ከልጆቸው ጋር በተያያዘ የሚያስጨንቋቸው ጥያቄዎች ናቸው ስልክ የሚያስደውላቸው። "ልጄ ትኩሳት አለው፣ ምግብ አልበላ አለ" የሚሉና ሌሎች የጤና መረጃዎች የብዙ ወላጆች ጥያቄዎች ሆነዋል።

በሦስተኛ ደረጃ በብዛት የሚደወሉ ስልኮች ከጾታ ግንኙነት ጋር ተያይዞ መረጃን የሚሹ ናቸው።

"ከስንፈተ ወሲብ ጋር የተገናኙ፣ ባልና ሚስት በወሲብ ካለመረካት ጋር የተያያዙ ችግሮችን የሚያነሱ ብዙ ናቸው" ይላሉ አቶ አብዲ።

"የጾታ ግንኙነት ትምህርት በአገራችን በግልጽ ስለማይሰጥ ብዙ ሰዎች በርካታ ጥያቄዎች አሏቸው" የሚሉት አቶ አብዲ፤ "ምናልባት ሐኪም ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተው እነዚህን ከወሲባ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን የመጠየቅ ድፍረቱ ስለሌላቸው ይሆናል በርካታ ሰዎች በስልክ ምክር የማግኘት ምርጫ ያላቸው" ሲሉ ይገምታሉ።

የዮካ ቴሌሜድስን ከቴሌ ጋር በመቀናጀት እንደሚሰራ የሚገልጹት አቶ አብዲ ደንበኞች የጤና መረጃዎችን ለማግኘት በደቂቃ 4 ብር እንደሚስከፍሉ ገልጸዋል።

ለመሆኑ አንዲት በመረጃ መዛባት የምትፈጠር የሕክምና ስህተት የሕይወት ዋጋ ልታስከፍል እንደምትችል ከመረዳት አንጻር እንዴት ይሆን የቴሌሜዲስን ድርጅቶች የስልክ ምክሮች ላይ ጥንቃቄ የሚያደርጉት? የጤና ጥበቃስ ቁጥጥሩን የሚያደርገው በምን መልኩ ነው?

ታማሚው በሕክምናው ላይ እምነት እንዲኖረው ምንያደርጋሉ?

"የእኛ አገልግሎት ማማከር ነው፤ ከደዋዮች ያልገባን ነገር ካለ አጥርተን እንጠይቃለን፤ የስልክ ሕክምናው ጠቃሚ መረጃን በመስጠት ላይ የተመሠረተ ነው እንጂ እኛው ራሳችን ሕክምናውን ጀምረን የማጠናቀቅ ጉዳይ አይደለም" ይላሉ አቶ አብዲ።

"ወደ ማከም ሳይሆን ወደ ምክር እናዘነብላለን። ያልገቡን ነገሮች ላይም አንዳፈርም፤ ሐኪም እንደመሆናችን ከታማሚው የተሻለ ስለ በሽታው ስለሚገባን እገዛ ነው የምንሰጠው እንጂ ከዚያ ያለፈ ነገር አንሰራም" ይላሉ።

ለጥንቃቄ ሲባልም ታካሚ የስልክ ጥሪ ሲያደርግ እያንዳንዷ የድምጽ ልውውጥ ተቀድታ ትቀመጣለች፤ ይህም ተጣያቂነት እንዲኖር ለማድረግ ነው ሲሉ በጤና ጉዳይ የጥንቃቄና የተጠያቂነት ርቀቱን ያስረዳሉ።

"መታወቅ ያለበት በሽተኛውን ከመረመረው ሐኪም በላይ እኛ እናውቅልሀለን አንልም። ትክክል መስሎ ካልተሰማን ግን ከደዋዩ ጋር በመነጋገር የግል ሐኪሞቻቸው ጋር በመደወል ተጨማሪ መረጃ እንሰበስባለን። ወይም ደግሞ ታማሚው ወደመረመረው ሐኪም በድጋሚ እንዲሄድ እንመክረዋለን። አለበለዚያ ታማሚን የበለጠ ማወዛገብ ነው የሚሆነው።"

ከቴሌሜዲስን ወደ ቪዲዮ ሜዲስን

የቴሌሜዲሲን ሐሳብ ባደገው ዓለም ከፍ ያለ ደረጃ ደርሶ ቪዲዮሜዲስን ላይ ደርሷል። ከዚያም በላይ የአርቴፊሻል ኢንተለጄንስ [ሰው ሰራሽ ልህቀት] በሕክምና ውስጥ ገብቶ ብዙ ለውጦችን ማየት ተችሏል። በአንዳንድ ብልጹግ አገሮች የሐኪምና ታማሚ በአካል መገናኘት የግድ ወዳለመሆን ደረጃ እየደረሰ ነው።

ለመሆኑ የዮኮ ቴሌሜዲስን ምን አስበዋል?

ሐኪምና በሽተኛ ሌላና ሌላ ቦታ ሆነውም ሕክምናን ማሳካት ይቻላል ብለው የሚያምኑት አቶ አብዲ፣ በቴሌኮም አለመስፋፋት ምክንያት ይህ በእኛ አገር በቅርብ ጊዜ የሚተገበር እንዳልሆነ ያብራራሉ።

ሆኖም ሁኔታዎች እየተሻሻሉ ሲሄዱ አገልግሎቱን ወደ ገጠር የማስፋፋት ሐሳብ አላቸው።

"የቴሌኮም ኢንተርኔት አገልግሎት ወደ ገጠር እየተስፋፋ ሲሄድ ጤና ተቋማት እንደልብ በማይዳረስባቸው የአገራችን ክፍሎች ይህን የቴሌሜዲስን አገልግሎት ማስተዋወቅ እናስባለን። ቨርቹዋሊ ሰዎችን ማከም፣ ሐኪም ቤቶቻችንን የሚጨናነቁበትን ሁኔታ መቀነስ የረዥም ጊዜ እቅዳችን ነው" ይላሉ።