የ 'ሆቴል ሩዋንዳ' ፊልም ዝነኛ አፍኖ ያመጣውን አየር መንገድ ሊከስ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሩዋንዳ ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ተቃዋሚ እንደሆነ የሚነገርለትና በርዋንዳ እልቂት ወቅት በጎ ተግባር ፈጽሟል በሚል 'ሆቴል ሩዋንዳ" የሚል ፊልም በሆሊውድ የተሰራለት ሰው አሁን በሩዋንዳ እስር ቤት ይገኛል።
ፖል ሩሰሳባጊና የሚል መጠርያ ስም ያለው ይህ ዝነኛ ሩዋንዳዊ ከ1994ቱ እልቂት በኋላ በአሜሪካና በቤልጂየም በስደት ነበር የሚኖረው።
በሩዋንዳ የዘር ፍጅት ወቅት ሰዎችን እየደበቀ ከራሱ ጎሳ ገዳዮች ሰዎችን አድኗል በሚል ትልቅ ሙገሳና ክብር ያገኘው ይህ ሰው ታሪኩ ለሆሊዉድ ስኬታማ ፊልም መሰራትም ምክንያት መሆኑ ይታወሳል።
ሆኖም አሁን በሩዋንዳ ፍርድ ቤት ተቃዋሚዎችን በገንዘብ ይደግፍ ነበር በሚል ክስ ቀርቦበት ኪጋሊ እስር ቤት ይገኛል።
እንዴት ከሚኖርበት አገር ተይዞ ወደ ሩዋንዳ መጣ የሚለው ግን እስከዛሬ ብዙዎችን ሲያነጋግር ነበር።
አሁን ፖል ዝምታውን ሰብሯል። በሩዋንዳ የሽብር ክስ የተከፈተበት ፖልን አፍኖ ወደ ሩዋንዳ ያመጣውን አየር መንገድ እንደሚከስ ይፋ አድርጓል።
ፖል እንደሚለው አየር መንገዱ ወደ ሩዋንዳ ይዞት የመጣው በማታለል ነው።
እሱ እንደሚለው ባለፈው ነሐሴ ወር ቡሩንዲ ሄዶ ለቤተክርስቲያን አነቃቂ ነግግር ለማድረግ ይሰናዳል።
ከዱባይ በቻርተርድ አውሮፕላን ተከራይቶ ለመሄድ ሲሳፈር ግን አውሮፕላኑ ወደ ቡሩንዲ ሳይሆን ወደ ሩዋንዳ ነበር ያደረሰው።
አሁን በቴክሳስ በተከፈተ ክስ ይህ ጌይን ጄት የሚባል አውሮፕላን አከራይ ኩባንያ የፖልን አፈና በማመቻቸት ክስ ተከፍቶበታል።
ድርጅቱ ከኪጋሊ ባለሥልጣናት ጋር የቅርብ ግንኙነት አለው ተብሎ ይታመናል።
ተመሳሳይ ክስ ከቴክሳስ ሌላ በቤልጂየምም ይከፈታል ተብሏል። ምክንያቱ ደግሞ ፖል የቤልጂየም ዜግነት ስላለው ነው።
ቢቢሲ ለዚህ ዘገባ የጄንጄት ኃላፊዎችን ሐሳብ ለማካተት ያደረገው ሙከራ አልተሳካለትም።
በ1994 በነበረው የሁቱ ቱትሲ የሩዋንዳ የዘር ፍጅት ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በመቶ ቀናት ውስጥ አልቀዋል።












