አሜሪካ ከሩሲያ ነው ተብሎ የተገመተ ‘ከባድ’ የሳይበር ጥቃት እየተከላከለች መሆኑ ተሰማ

የፎቶው ባለመብት, AFP
አሜሪካ በዚህ ሳምንት መጀመርያ ከባድ የሳይበር ጥቃት እየዘነበብኝ ነው፤ ጥቃቱ አሁንም አላባራም ብላለች።
የሳይበር ጥቃቱም በተለይ በመንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ላይ ከባድ አደጋን ሊያደርስ እንደሚችል ሰግታለች።
ጥቃቱ በዋናነት የአሜሪካ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ ዒላማ ያድርግ እንጂ ለግዙፍ የግል ተቋማትም አደጋን ጋርጧል።
ግዙፉ የአሜሪካ ግምጃ ቤት እና የአሜሪካ የንግድ ሚኒስቴር የዚህ የሳይበር ጥቃት ሰለባ ሆነዋል።
የአሜሪካ የበይነ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ሲሳ) እንዳመነው ይህንን ጥቃት ለማክሸፍ እንዲህ እንደሚወራው ቀላል አልሆነም።
ሐሙስ ዕለት ይህ መሥሪያ ቤት ባወጣው ሪፖርት ዋና ዋና የመንግሥት መሠረተ ልማቶች በዚህ ጥቃት ዒላማ ተደርገዋል ብሏል።
መሥሪያ ቤቱ ጨምሮም፥ "ጥቃቱ የዋዛ አይደለም፥ የአንድ ጊዜ ጥቃት ብቻም አይደለም፣ አሁንም ቀጥሏል" ሲል የጉዳዩን አሳሳቢነትና ውስብስብነት ዘርዝሮታል።
ብዙዎች ከዚህ ውስብስብ ጥቃት ጀርባ ሩሲያ ካልሆነች ሌላ አካል ሊሆን አይችልም ሲሉ ይከስሳሉ።
ሞስኮ ግን መሠረተ ቢስ ወሬ ነው ስትል ክሱን አስተባብላለች።
ከዚህ ጥቃት ጀርባ በዋናነት ትልቅ አገር ልትኖር እንደምትችል የተገመተው መረጃ መንታፊዎቹ ያሳዩት ታጋሽነት፣ ጥቃቱን ለማድረስ የሚሄዱበት ውስብስብ ርቀት እና ዲሲፕሊን፣ ጥቃቱን ሲያደርሱ ማንነታቸው እንዳይታወቅ ያዘጋጁት ከለላ ጥብቅነት ያለው በመሆኑ ነው።
ሲሳ እስካሁኗ ደቂቃ ድረስ ሩሲያን በይፋ አልከሰሰም። ለጥቃቱ ኃላፊነትን ለየትኛው አካል አልሰጠም።
በተጨማሪም የትኞቹ የመንግሥት መዋቅሮች የትኛው መረጃ እንደተመነተፈባቸው በዝርዝር አልገለጸም።
ይህ በአንዲህ እያለ ከአንድ ወር በኋላ ወደ ዋይት ሐውስ የሚገቡት ተመራጭ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ባይደን የሳይበር ደኅንነት ጉዳይ መንግሥቴ እጅግ አንገብጋቢ ከሚላቸው አጀንዳዎች አንዱ ነው ብለዋል።
በርካታ የአሜሪካ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሰሞኑ የሳይበር ጥቃት ክፉኛ እንደተሸመደመዱ ይነገራል። ይህ የሳይበር ጥቃት አሁንም ድረስ አልቆመም።
ሮይተርስ እንደዘገበው በርባሪዎቹ በአሁን ሰዓት በአሜሪካ መከላከያ፥ በአሜሪካ አገር ውስጥ ደኅንነት (ሆምላንድ ሴኩሪቲ)፥ በአሜሪካ ግምጃ ቤትና ንግድ ሚኒስቴር ዳታዎችን በከፊል መቆጣጠር ላይ ናቸው።
የአሜሪካ የኢነርጂ ዲፓርትመንት እና የብሔራዊ ኒውክሊየር ደኅንነት አስተዳደር መሥሪያ ቤቶችም በተመሳሳይ መረጃዎቻቸው እንደተበረበሩባቸው ተናግረዋል።
ሲሳ እንዳለው በርባሪዎቹ የኮምፒውተር ኔትዎርኮችን ሰብረው መግባት የቻሉት መቀመጫውን ቴክሳስ ባደረገ የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ኩባንያ በሆነው ሶላርዊንድስ ሶፍትዌር ተጠቅመው ነው።
18ሺ የሚሆኑ የሶላር ዊንድስ ኦሪዮን ሶፍትዌር ተጠቃሚዎች ይህንን ሶፍትዌር እድሳት (አብዴት) ሲያደርጉ ነው በዚያው በርባሪዎች ሰተት ብለው መግባት የቻሉት።
ይህንን ተከትሎ ሁሉም የመንግሥትና የግል ድርጅቶች የሶላር ዊንድስ ሶፍትዌርን ከኮምፒውተራቸው በአስቸኳይ እንዲያስወግዱ ተነግሯቸዋል።
አሁንም ቢሆን የአሜሪካ የበይነ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (Cisa) እና የአሜሪካ የወንጀል ምርመራ ቢሮ (FBI) ከዚህ መጠነ ሰፊ የሳይበር ጥቃት ጀርባ ማን እንዳለ ከመናገር ተቆጥበዋል።
ሆኖም በሳይበር ደኅንነት የመሰሩና የበይነ መረብ ደኅንነት ጉዳይ አዋቂዎች፣ አማካሪዎችና ተመራማሪዎች እንዲህ ያለ አቅም ያላት ሩሲያ ብቻ ናት ሲሉ ጣታቸውን ወደ ክሬምሊን ይጠቁማሉ።















