የአሜሪካ ግምጃ ቤትና የንግድ ተቋማት የሳይበር ጥቃት ተፈጸመባቸው

የአሜሪካ ግምጃ ቤትና የንግድ ተቋማት የሳይበር ጥቃት ተፈጸመባቸው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካ ግምጃ ቤትና ንግድ ሚንስቴር መስሪያ ቤቶች የሳይበር ጥቃት ተፈጸመባቸው።

ይህንንም ተከትሎ አሜሪካ ሎሎች የሲቪል ፌዴራል ኤጀንሲዎች በአስቸኳይ "ሶላርዊንድስ" ተብሎ ከሚጠራው ኮምፒዩተር ኔትዎርክ መሣሪያን መጠቀም እንዲያቆሙ ትዕዛዝ አስተላልፋለች።

ይህ "ሶላርዊንድስ" የተባለው ኮምፒዩተር ኔትዎርክ መሣሪያ በጠላፊዎች እጅ ወድቋል ተብሏል።

አሜሪካ ከጥቃቱ ጀርባ ማን እንዳለ እስካሁን ምንም ያለችው ነገር የለም።

'ፋየርአይ' የተሰኘ የሳይበር ደህንነት ኩባንያ ለደህንነት ማረጋገጫ የሚጠቀምበት የኮምፒዩተር መገልገያ በበይነ መረብ ጠላፊዎች መጠለፉን ካስታወቀ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው ይህ ክስትት ያጋጠመው።

የአሜሪካ ሳይበር ደህንነት እና መሰረተ ልማት ደህንነት ኤጀንሲ እንዳስታወቀው የአሁኑ ጠለፋ የመንግሥት መረጃ ስርዓትን በከፍተኛ ሁኔታ ሊያጋልጥ የሚችል ነው።

ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ሶላርዊንድስ እነዚህ የአሜሪካ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የሚጠቀሙትን የኮምፒዩተር ኔትዎርክ መገልገያ የሰራ ሲሆን በትዊተር ገጹ ላይ አገልግሎቱን የሚያገኙ ተጠቃሚዎች ሊደርስ የሚችለውን የደህንነት ስጋት ለመቀነስ ወደተሻሻለው አዲስ ስርዓት ሊቀይሩ ይገባል ብሎ ነበር።

ፋየርአይ የተሰኘው ኩባንያ ጥቃቱ ከፍተኛ የመንግሠዕት መዋዕለ ንዋዮችን እና መሠረተ ልማቶቸን ኢላማ ያደረገ መሆኑ እና ምናልባት በሌላ መንግሥት የሚደገፍ ሊሆን ይችላል የሚለን ሀሳብ ያጠናክረዋል ብሏል።

እንደዚህ አይነት መሰል ጥቃቶችን በመመርመር የሚታወቁ ሶስት ግለሰቦች ጥቃቱ የተፈጸመው በሩሲያ ሊሆን ይችላል ሲሉ ለሮይተርስ የዜና ወኪል መናገራቸው ተገልጿል።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በበኩሉ በፌስቡክ ገጹ ላይ ባሰፈረው መልዕክት ''ምንም መሰረት የሌለው ውንጀላ ነው'' ብሏል።