ተማሪዎችን አግተው የሚገኙ ታጣቂዎች መከበባቸውን የናይጄሪያ መንግሥት አስታወቀ

የናይጄሪያ ጦር አባላት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ተማሪዎቹ በታገቱበት ትምህርት ቤት አቅራቢያ መንግሥት ተጨማሪ ጸጥታ አስከባሪ ኃይል አሰማርቷል

አሥር ታዳጊዎችን አግተው የሚገኙት ታጣቂዎች መከበባቸውን የናይጄሪያ መንግሥት አስታወቀ።

በሰሜን ምዕራባዊ ናይጄሪያ ተማሪዎች ታግተውበታል ተብሎ የተገመተ አካባቢ በመንግሥት ወታደሮች መከበቡን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሙሀመዱ ቡሃሪ ቃል አቀባይ አስታውቀዋል።

አሥር ተማሪዎች በታጣቂዎች ተይዘው እንደሚገኙ ቃል አቀባዩ ጋርባ ሼሹ የገለጹ ሲሆን ጠፍተዋል ከተባሉት ተማሪዎች ቁጥር አንጻር ግን አሁን የተገለጸው ቁጥር በጣም አነስተኛ ነው ተብሏል።

በሰሜን ምዕራባዊ ናይጄሪያ ካትሲና ግዛት በሚገኘው የወንዶች ትምህርት ቤት 800 የሚሆኑ ተማሪዎች ተመዝግበው ይማሩ የነበረ ሲሆን እስካሁን ድረስ ግማሽ የሚሆኑት የት እንደሚገኙ አይታወቅም ተብሏል።

ቃል አቀባዩ እንደሚሉት ታጣቂዎቹ ተማሪዎቹን አግተው የወሰዱት የማስለቀቂያ ገንዘብ ለመጠየቅ ነው።

መንግሥት እንዲህ አይነት ተግባር የሚፈጽሙት በአካባቢው ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ሽፍታዎች እንደሆኑ ያስታወቀ ሲሆን ጠፍተዋል የተባሉት ቀሪዎች ተማሪዎች ግን እስካሁን የት እንደሚገኙ አልታወቀም።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደሚለው በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ብቻ ከ1 ሺ 100 በላይ ሰዎች በሰሜናዊ ናይጄሪያ በሽፍታዎች የተገደሉ ሲሆን መንግሥት እስካሁን ተጠያቂዎችን ለሕግ ማቅረብ አልቻለም።

ታጣቂዎች በሞተርሳይክል ተጭነው በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ ከደረሱ በኋላ ወደ ሰማይ መተኮስ እንደጀመሩና በርካቶችም በፍርሃት ከአካባቢው ተበታትነው እንደጠፉ የዓይን እማኝ ተናግሯል።

በትናንትናው ዕለት የናይጄሪያ ጦር ታጣቂዎቹ የተደበቁበትን ስፍራ እንዳገኘውና ከሠራዊቱ አባላትም ጋር የተኩስ ልውውጥ እንደነበርም ተገልጿል።

የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ ጥቃቱን አውግዘው የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዲቀጥልና ምን ያህል ተማሪዎችም በትክክል እንደጠፉ ቆጠራ እንዲካሄድም ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

በናይጄሪያ ሰሜን ምዕራባዊ ክፍል አፈና እና የማስፈቻ ገንዘብ መጠየቅ በእጅጉ እየተለመደ የመጣ ነገር ሆኗል ይላል የቢቢሲ ናይጄሪያ ዘጋቢው ማዬኒ ጆንስ።

ልጆቻቸው የት እንደገቡ ማወቅ ያልቻሉ በርካታ ወላጆች በትምህርት ቤቱ አቅራቢያ በመሰባሰብ ባለስልጣናት ልጆቻቸውን እንዲያስመልሱላቸው እና የት እንደሚገኙ እንዲነግሯቸው ሲማጸኑ ታይተዋል።

የፕሬዝዳንቱ ቃል አቀባይ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ የታገቱትን ተማሪዎች ለማስለቀቅ በርካታ ወታደሮች መሰማራታቸውንና ሽፍታዎቹ የሚገኙበትን ቦታ መለየታቸውን ገልጸዋል።

''ተማሪዎቹን ለማስለቀቅ የቻልነውን በሙሉ እያደረግን ነው፤ ወንጀለኞችና ሽፍታዎቹም በቅርቡ ይደመሰሳሉ'' ብለዋል።