የአሜሪካው የኢነርጂ ዲፓርትመንት የሳይበር ጥቃት ደረሰበት

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካው የኢነርጂ ዲፓርትመንት የሳይበር ጥቃት እንደደረሰበትና በአሜሪካ መንግሥት ላይ የደረሰበት ከባዱ የመረጃ ብርበራም ነው ተብሏል።
ዲፓርትመንቱ የኒውክሊየር መሳሪያዎችን በበላይነት የሚቆጣጠር ሲሆን በጥቃቱ ምክንያት በኒውክሊየር መሳሪያዎቹ ላይ የደህንነት ክፍተት አላጋጠመም ተብሏል።
የቴክኖሎጂው ግዙፉ ኩባንያ ማይክሮ ሶፍት በትናንትናው እለት በሲስተሙ ውስጥ አጠራጣሪ መተግበሪያዎች አግኝቻለሁ ብሏል።
ከዚህ ጥቃት ጀርባ በዋናነት ሩሲያ ልትኖር እንደምትችል የተገመተው መረጃ መንታፊዎቹ ያሳዩት ታጋሽነት፣ ጥቃቱን ለማድረስ የሚሄዱበት ውስብስብ ርቀት እና ዲሲፕሊን፣ ጥቃቱን ሲያደርሱ ማንነታቸው እንዳይታወቅ ያዘጋጁት ከለላ ጥብቅነት ያለው በመሆኑ ነው።
ሩሲያ ከጥቃቱ ጀርባም የለሁበትም ብላለች። የአሜሪካ የበይነ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ሲሳ) እስካሁኗ ደቂቃ ድረስ ሩሲያን በይፋ አልከሰሰም። ለጥቃቱ ኃላፊነትን ለየትኛው አካል አልሰጠም።
በተጨማሪም የትኞቹ የመንግሥት መዋቅሮች የትኛው መረጃ እንደተመነተፈባቸው በዝርዝር አልገለጸም።
በርባሪዎቹ በአሁን ሰዓት በአሜሪካ መከላከያ፥ በአሜሪካ አገር ውስጥ ደኅንነት (ሆምላንድ ሴኩሪቲ)፥ በአሜሪካ ግምጃ ቤትና ንግድ ሚኒስቴር ዳታዎችን በከፊል መቆጣጠር ላይ ናቸው።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራም በጥቃቱ ላይ አስተያየት አልሰጡም።
ከአንድ ወር በኋላ ወደ ዋይት ሐውስ የሚገቡት ተመራጭ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ባይደን የሳይበር ደኅንነት ጉዳይ መንግሥቴ እጅግ አንገብጋቢ ከሚላቸው አጀንዳዎች አንዱ ነው ብለዋል።
በርካታ የአሜሪካ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሰሞኑ የሳይበር ጥቃት ክፉኛ እንደተሸመደመዱ ይነገራል። ይህ የሳይበር ጥቃት አሁንም ድረስ አልቆመም።
ሲሳ እንዳለው በርባሪዎቹ የኮምፒውተር ኔትዎርኮችን ሰብረው መግባት የቻሉት መቀመጫውን ቴክሳስ ባደረገ የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ኩባንያ በሆነው ሶላርዊንድስ ሶፍትዌር ተጠቅመው ነው።
18ሺ የሚሆኑ የሶላር ዊንድስ ኦሪዮን ሶፍትዌር ተጠቃሚዎች ይህንን ሶፍትዌር እድሳት (አብዴት) ሲያደርጉ ነው በዚያው በርባሪዎች ሰተት ብለው መግባት የቻሉት።
ይህንን ተከትሎ ሁሉም የመንግሥትና የግል ድርጅቶች የሶላር ዊንድስ ሶፍትዌርን ከኮምፒውተራቸው በአስቸኳይ እንዲያስወግዱ ተነግሯቸዋል።
አሁንም ቢሆን የአሜሪካ የበይነ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (Cisa) እና የአሜሪካ የወንጀል ምርመራ ቢሮ (FBI) ከዚህ መጠነ ሰፊ የሳይበር ጥቃት ጀርባ ማን እንዳለ ከመናገር ተቆጥበዋል።
ሆኖም በሳይበር ደኅንነት የመሰሩና የበይነ መረብ ደኅንነት ጉዳይ አዋቂዎች፣ አማካሪዎችና ተመራማሪዎች እንዲህ ያለ አቅም ያላት ሩሲያ ብቻ ናት ሲሉ ጣታቸውን ወደ ክሬምሊን ይጠቁማሉ።












