የዓለም ትልቁ ሥጋ ማቀነባበሪያ የበይነ መረብ ጥቃት ደረሰበት

ጄቢኤስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጄቢኤስ የተባለው የዓለም ትልቁ የሥጋ ማቀነባበሪያ ድርጅት የበይነ መረብ ጥቃት ደረሰበት።

መረጃ ሠርሳሪዎች ባደረሱት ጥቃት በአውስትራሊያ፣ ካናዳ እና አሜሪካ ያሉ የድርጅቱ ቅርንጫፎች በከፊል ሥራ አቁመዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ተቀጣሪዎችም ከሥራቸው ተስተጓጉለዋል።

ዋይት ሀውስ እንዳለው ጥቃቱ የተሰነዘረው ሩስያ ውስጥ ከሚገኝ የወንጀለኞች ቡድን እንደሆነ ነው ድርጅቱ የሚያምነው።

ይህንን ጥቃት ተከትሎ የሥጋ እጥረት ሊያጋጥም ወይም የሥጋ ዋጋ ሊጨምር ይችላል።

እንደዚህ አይነት ጥቃቶች (ራንሰም አታክ) የሚደርሱት የአንድ ድርጅት መረጃ በጠላፊዎች እጅ ሲገባ ነው። ድርጅቱ የሚጠየቀውን ገንዘብ ካልከፈለ መረጃዎቹ እንደሚጠፉ ጠላፊዎቹ ያስፈራራሉ።

ጄቢኤስ ጥቃቱ ሲሰነዘርበት ለዋይት ሀውስ አስታውቋል። የአሜሪካው የምርመራ ተቋም ኤፍቢአይም ጉዳዩን እያጣራ ነው።

የዋይት ሀውስ ቃል አቀባይ ካሪን ጄንፒሬ "ጥቃቱ የተሰነዘረው ሩስያ ውስጥ ካለ የወንጀል ቡድን ሊሆን እንደሚችል ጄቢኤስ ገልጾልናል" ብለዋል።

ዋይት ሀውስ ከሩስያ መንግሥት ጋር እየተነጋገረ እንደሆነ ጠቁመው "መንግሥት የመረጃ ሠርሳሪዎችን በጉያው እንዳይደብቅ እንጠይቃለን" ሲሉ አስረድተዋል።

ጄቢኤስ ማነው?

ድርጅቱ በዓለም ትልቁ የሥጋ ማቀነባበሪያ ነው። በ15 አገራት ከ150 በላይ ቅርንጫፎች አሉት።

እአአ በ1953 ጆሴ ባቲስታ ሶብሪኖ በተባለ ግለሰብ ብራዚል ውስጥ ነበር የተጀመረው። አሁን በመላው ዓለም ከ150,000 በላይ ሠራተኞች አሉት።

ለተለያዩ መደብሮች እና እንደ ማክዶናልድስ ላሉ ምግብ ቤቶች ሥጋ ያከፋፍላል።

አሜሪካ ውስጥ አንድ አራተኛውን የበሬ ሥጋ እንዲሁም አንድ አምስተኛውን የአሳማ ሥጋ ያቀርባል።

ድርጅቱ የደረሰበትን የበይነ መረብ ጥቃት በመመከት ረገድ ጥሩ እንቅስቃሴ እንዳደረገ እና ዛሬ ቅርንጫፎቹ ወደ ሥራ ይመለሳሉ ብሎ እንደሚጠብቅ ይፋ አድርጓል።

ጥቃት የደረሰባቸውን የድርጅቱ ሰርዓቶች ከሥራ ውጪ እንዳደረገና ተጠባባቂ ሰርቨሮቹ እንዳልተጎዱ ተናግሯል።

የጄቢኤስ ሠራተኞችን የሚወክለው ዩናይትድ ፉድ ኤንድ ኮሜርሻል ወርከርስ ዩኒየን፤ ተቀጣሪዎች ደመወዛቸው እንዲከፈላቸው አሳስቧል።

ጥቃቱ የሚያሳድረው ተጽዕኖ

ዘመነኛ የሥጋ ማቀነባበሪያዎች አብዛኛውን ሥራ የሚያከናውኑት በበይነ መረብ ነው።

ቢፍ ሴንትራል የተባለው ተቋም እንዳለው፤ ጄቢኤስ ላይ በደረሰው ጥቃት በግንባር ቀደምነት የሚጎዱት ሥጋ የሚረከቡት መደብሮች እና ማክዶናልድስን የመሰሉ ምግብ ቤቶች ናቸው።

የብሉምበርግ ዘገባ እንደሚያሳየው፤ የጄቢኤስ አምስት ትልልቅ ፋብሪካዎች የሚገኙት በአሜሪካ ነው። በጥቃቱ ሳቢያ የሥጋ አቅርቦት አንድ አምስተኛው ቀንሷል።

አውስትራሊያ እና ካናዳ የሚገኙ ፋብሪካዎችም ተመሳሳይ መሰናክል ገጥሟቸዋል። ያልተቋረጠው በደቡበ አሜሪካ ያለው አቅርቦት ነው።

ባለፈው ወር በደቡብ ምሥራቅ አሜሪካ የሚገኝ ነዳጅ አምራች የበይነ መረብ ጥቃት ደርሶበት ለቀናት ሥራ ማቋረጡ ይታወሳል።

መርማሪዎች እንዳሉት፤ ጥቃቱ ሩስያ ካለ የወንጀል ቡድን ጋር ትስስር አለው።

ኮሎኒያል ፓይፕላየን የተባለው ድርጅት 4.4 ሚሊዮን ዶላር ለመረጃ ሠርሳሪዎቹ ለመክፈል ተገዷል።

የአሜሪካ መንግሥት በበኩሉ ተቋሞች ጥቃት ሲሰነዘርባቸው ለመረጃ ሠርሳሪዎች ገንዘብ እንዳይከፍሉ አስጠንቅቋል። ክፍያ መፈጸም በቀጣይም ለጥቃት ያጋልጣል ይላል መንግሥት።