የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው የኡጋንዳው የትራንስፖርት ሚንስትር ቆሰሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የኡጋንዳ የትራንስፖርት ሚንስትር በታጣቂዎች የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸው የቆሰሉ ሲሆን የሚንስትሩ ልጅና ሹፌር ግን በጥቃቱ መገደላቸው ተገለጸ።
የቀድሞው የመከላከያ ኃላፊና የአሁኑ የትራንስፖርት ሚንስትር ጄነራል ካቱምባ ዋማላ የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው ካምፓላ የሚገኘው ቤታቸው አቅራቢያ መሆኑን የአይን እማኞች ገልጸዋል።
በሞተርሳይክል ይጓዙ የነበሩ ታጣቂዎች የሚንስትሩ መኪና ላይ ደጋግመው መተኮሳቸው ነው የተነገረው።
ከግድያ ሙከራው ጋር የተያያዙ ናቸው የተባሉ የስልክ ጥሪዎች ላይ ምርመራ እየተካሄ እንደሆነ መከላከያ ኃይሉ አስታውቋል።
ጄነራል ካቱምባ የደረሰባቸው ጉዳት ለሕይወታቸው አስጊ እንዳልሆነና ሕክምና እያገኙበት ያለው ሆስፒታል በወታደሮች እየተጠበቀ እንደሆነ ተገልጿል።
ኡጋንዳ ውስጥ እጅግ ከሚከበሩ ፖለቲከኞችና ወታደራዊ ግለሰቦች አንዱ ናቸው። የአገሪቱ መከላከያ ኮማንደር እንዲሁም የፖሊስ ኃላፊም ሆነው አገልግለዋል።
የቢቢሲዋ የኡጋንዳ ዘጋቢ ፔሸንስ አቲሬ እንደምትለው፤ መሰል ጥቃቶች የተለመዱ ቢሆኑም የግድያ ሙከራው አስደንጋጭ ነው።
ዛሬ ጥቃት ሲፈጸምባቸው በወታደር መኪና ውስጥ ነበሩ። መኪናው ላይ ከጎን እና ከፊት ተተኩሶበታል።
ልጃቸው ብሬንዳ ዋማላ እና ሹፌራቸው ሀሩና ካዮንዶ ሕይወታቸው አልፏል።
ጄነራሉ ደም በደም ሆነው፣ በፍርሀት ሲንቀጠቀጡና ከዚያም በሞተርሳይክል ወደ ሆስፒታል ሲወሰዱ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ወጥቷል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሞተርሳይክል የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ተኩስ እየከፈቱ አገሪቱን እየናጧት እንደሆነ የቢቢሲ ዘጋቢ ትናገራለች።
እአአ ሰኔ 2018 ላይ ኢብራሒም አቢርጋ የተባለ ፖለቲከኛና የፕሬዘዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ቀንደኛ ደጋፊ ቤቱ አቅራቢያ ተተኩሶበት ተገድሏል።
የቀድሞው የፖሊስ ቃል አቀባይ አንድሪው ፌሊክስ ካውሲም በሚያዝያ 2017 ተገድሏል።
የእስልምና መምህራንም በተመሳሳይ ሁኔታ ተገድለዋል።
እስካሁን ድረስ ግድያዎቹ ተመርምረው ውጤት ሲገኝ ወይም ተጠያቂዎች ለፍርድ ሲቀርቡ አልታየም።












