የበይነ መረብ ሰርሳሪዎች ከዘረፉት ገንዘብ የተወነሰውን ለበጎ አድራጎት ሰጡ

የበይነ መረብ ሰርሳሪዎች 10 ሺህ ዶላር የለገሱበትን ደረሰኝ ይፋ አድርገዋል

የፎቶው ባለመብት, EDUARD MUZHEVSKYI / SCIENCE PHOTO LIBRARY

ማንነታቸው አሁንም አልታወቀም፡፡ እንዴትስ ይታወቃል?

‹ዳርክሳይድ ሐከርስ› በሚል ስም ነው ራሳቸውን የሚጠሩት፡፡

የበይነ መረብ ሰርሳሪዎች የኩባንያዎችን ገጽ ሰብረው በመግባት መረጃን ይቆልፋሉ፡፡ ከዚያም ገንዘብ እየተደራደሩ ኩባንያዎችን በሚሊዮን ዶላሮች ይዘርፋሉ፡፡

ከእገታ የማስለቀቂያ ገንዘብ በመጠየቅ ነው በስፋት ኪሳቸውን የሚያደልቡት። ኩባንያዎቹ የታገተባቸውን መረጃ ለማስለቀቅ ሲሉ የሚጠየቁትን ገንዘብ ከመክፈል ውጭ አማራጭ አይኖራቸውም፡፡

ታዲያ አስገራሚው ነገር እነዚህ ሰርሳሪዎች ለበጎ ተግባር እጃቸውን መዘርጋታቸው ነው፡፡

‹ዳርክሳይድ ሐከርስ› በሚል መጠርያ ሕቡዕና ውስብስ ዝርፍያ ላይ የተሰማሩት እነዚህ የበይነ መረብ ሰርሳሪዎች ‹‹በጎ አድራጎቱን የፈጸምነው ዓለምን የተሻለች ለማድረግ ቁርጠኛ ፍላጎት ስላለን ነው›› ብለዋል፡፡

ዳርክሳይድ እስካሁን ከኩባንያዎች በይነመረብ ሰርስረው በሚሊዮን ዶላሮች ዘርፈዋል፡፡

ዘራፊዎቹ በድረገጻቸው ላይ ለበጎ ተግባር የላኩትን የገንዘብ መጠን የሚያሳይ ደረሰኝ ለጥፈዋል፡፡

10ሺ ዶላር እርዳታ ያደረሱት በጥሬ ገንዘብ ሳይሆን በቢትኮይን መልክ ነው፡፡

በሰርሳሪዎቹ እርዳታው ከተሰጣቸው ድርጅቶች መሀል አንዱ የሆነው ‹ቺልድረን ኢንተርናሽናል› (Children International) ገንዘቡን ለመቀበል እንደሚቸገር ይፋ አድርጓል፡፡

የሰርሳሪዎቹ ድርጊት የሞራልና የሕግ ጥያቄን የሚያስነሳ በመሆኑ በመላው ዓለም አነጋጋሪነቱ ቀጥሏል፡፡

ሰርሳሪዎቹ በኦክቶበር ወር በቀን 13፣ በጡመራ ገጻቸው ላይ ያጋሩት መረጃ እንደሚለው ቡድናቸው ዘረፋ የሚፈጽመው እጅግ ግዙፍ ትርፍ ከሚያጋብሱ ሀብታም ድርጅቶች ብቻ ነው፡፡

የግዙፍ ኩባንያዎችን የበይነ መረብ መረጃቸውን ሰብረው ከማረኩ በኋላ መረጃ እንዲለቀቅ ኩባንያው ከፈለገ የሚጠይቁትን ገንዘብ በአስቸኳይ እንዲያስተላልፍ ያደርጋሉ፡፡

‹ዳርክሳይድ ሐከርስ› ይፋ ያደረጉት የ10 ሺህ ዶላር ታክስ ደረሰኝ

ገንዘቡ ዘራፊዎቹ ባስቀመጡት ሂደት ሲተላለፍ የድርጅቶቹን በይነመረባዊ መረጃ ከእገታ ይለቀቃል፡፡

‹‹ከምንዘርፈው ሚሊዮን ዶላር የተወሰነው ለበጎ አድራጎት ማዋል መልካም ተግባር ሆኖ አግኝተነዋል›› ይላል ዘራፊዎቹ ለዓለም ያጋሩት ዜና፡፡

ቀጥለውም፣ ‹‹ምንም እንኳ መጥፎ ተግባር ላይ እንደተሰማራን ብታስቡም እኛ ግን የአንድን ሰው ሕይወት ለመቀየር መሞከራችን ልዩ እርካታ ይሰጠናል›› ብለዋል፡፡

‹‹ለዚህም ነው ገንዘቡን የለገስነው፡፡››

በይነመረብ ሰርሳሪዎቹ በቢትኮይን የእርዳታ እጃቸውን ከዘረጉላቸው የግብረ ሰናይ ድርጅቶች መሀል ሁለተኛው ዘዎተር ፕሮጀክት (The Water Project) ነው፡፡

የመጀመርያው የእርዳታው ተቀባይ ቺልድረን ኢንተርናሽናል በድህነት ላይ የሚገኙ ልጆችንና ቤተሰባቸውን የሚረዳ ግብረ ሰናይ ድርጅት ሲሆን በተለይ በህንድ፣ በፊሊፒንስ በካምቦዲያና ዛምቢያ፣ ጓቲማላ እና ሐንዱራስ በስፋት ይንቀሳቀሳል፡፡

የድርጅቱ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ‹ገንዘቡ ከዘራፊዎች ጋር የተነካካ ከሆነ› ይህንን ለመቀበል ለኛ ከባድ ይሆናል› ብለዋል፡፡

ዘዎተር ፕሮጀክት በበኩሉ ከሰሀራ በታች ባሉ አገራት ሰዎች የመጠጥ ውሀ እንዲያገኙ የሚተጋ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው፡፡

ከሰርሳሪዎቹ የተገኘውን ገንዘብ ትቀበላላችሁ ወይ የሚለውን ለመጠየቅ ቢቢሲ ሙከራ አድርጎ አልተሳካለትም፡፡

ብሪት ካሎው የበይነ መረብ ደኅንነት ጉዳዮች ኩባንያ ኤሚሶፍት ተንታኝና ባልደረባ ናቸው፡፡

የሰርሳሪዎቹን አስገራሚ ተግባር በተመለከተ በሰጡት አስተያየት ‹ምናልባት ሌቦቹ ይህን በጎ ተግባር ያደረጉት ከጥፋተኝነት ስሜት ለመሰረይ አልያም ‹ሮቢን ሁድ› ፊልሞች ለመምሰል ይሆናል ብለዋል፡፡

የሮቢን ሁድ አፈ ታሪኮች በኖቲንግሐም ኢንግላንድ ከንጉሥ ሪቻርድ አልጋ ወራሽ ልዑል ጆን በድሆች ላይ የሚፈጸመውን ግፍ ለመታደግ ከሀብታሞች እየዘረፈ ለድሆች ስለሚያከፋፍል ሰናይ-ሽፍታ የሚተርኩ ናቸው፡፡

‹ዳርክሳይድ ሐከርስ› ሌላ የ10 ሺህ ዶላር ደረሰኝ

‹‹እነዚህ የበይነ መረብ ሰርሳሪዎች ዓለማቸው ምንም ይሁን ምን ድርጊታቸው ያልተመለደ ነው፡፡ እኔ እንዲህ ዓይነት ነገር ስሰማም የመጀመርያዬ ነው›› ብለዋል የሳይበር ደኅንነት ጉዳዮች ተንታኝ፡፡

ዳርክሳይድ የሰርሳሪዎች ቡድን በበይነ መረብ ዘርፍያ ላይ ብዙ የሚታወቅ ቡድን አይደለም፡፡

ሰርሳሪዎቹ በጎ ተግባሩን ለመፈጸም የተጠቀሙት መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገውን ‹‹ጊቪንግ ብሎክ›› የተባለ ድርጅትን ነው፡፡

ድርጅቱ ለታዋቂዎቹ ሴቭ ዘ ችልድረን፣ ሬይንፎረስት ፋውንዴሽን፣ ሺኢዝ ዘ ፈርስት እና ሌሎች 67 ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በክሪፕቶከረንሲ እርዳታ የሚቀበልና የሚያቀብል ብቸኛው የበይነ መረብ ገንዘብ አስተላላፊ ቋት ነው፡፡ ለትርፍ የተቋቀቋመም አይደለም፡፡

ይህ ኩባንያ በፈረንጆቹ 2018 የተቋቋመ ሲሆን የክሪፕቶከረንሲ ሚሊየነሮችን ገንዘብ ለግብረ ሰናይ ድርጅቶች በቀጥታ እንዲያቀብሉ የሚያበረታታ ነው፡፡

ይህ ድርጅት እነዚህ ሰርሳሪዎቹ ስለሰጡት ገንዘብ በቂ መረጃ እንደሌለው ለቢቢሲ አረጋግጧል፡፡ ሆኖም ገንዘቡ በሌቦች የተለገሰ መሆኑን ሲያውቅ ምን እንደሚያደርግ ተጠይቆ ለለጋሾቹ እመልሰዋለው ብሏል፡፡

ድርጅቱ ‹‹እርዳታ የምቀበለው በክሪፕቶከረንሲ ስለሆነ ለጋሾቹን ለመያዝ ቀላል ነው›› ብሏል፡፡ ይህም ለጋሾች ገንዘብ ሲሰጡ ማንነታቸው ይታወቃል በሚል መላምት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡

ሆኖም ቢቢሲ ለሙከራ አነስተኛ ገንዘብ በተመሳሳይ መልኩ አስተላልፎ የለጋሽ ማንነትን የሚያስገድድ መጠይቅ አላጋጠመውም፡፡

ቢቢሲ በ‹‹ጊቪንግ ፕሮጀክት›› በኩል ገንዘብ የሚያገኙ እንደ ሴቭ ዘ ቺልድረን ያሉ ድርጅቶችን ጠይቆ እንደተረዳው ከዚህ ቀደም በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብ ተቀብለን አናውቅም የሚል ምላሽ አግኝቷል፡፡

ነገር ግን ተቀባዮቹ የበጎ ተግባር ገንዘቡ ምንጭ ማን እንደሆነ የማጣራት ጥረት አድርገው አያውቁም፡፡

ሺ ኢዝ ዘ ፈርስት (She's the First) ግብረ ሰናይ ድርጅት በበኩሉ ወንጀለኞች በዚህ መንገድ ያደፈ ገንዘባቸውን ‹ለማጠብ› መሞከራቸውን አውግዞ ለጋሾች ከዚህ በኋላ የድርጅቱን ደንቦችና እሴቶች እንዲያከብሩ ተማጽኗል፡፡