የሴቶች መብት፡ እየተለመደ የመጣው ሐሰተኛ የሴቶች የእርቃን ምስል በበይነ መረብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቅርቡ በተሰራ አንድ ትኩረቱን በይነ መረብ ላይ ባደረገ ጥናት መሰረት ከ100 ሺ በላይ የሚሆኑ ሴቶች በማህበራዊ ሚዲያ የተፈጠሩ ሲሆን የአብዛኛዎቹ ሴቶች ገጾች ሐሰተኛ የእርቃን ምስሎችን ለማጋራት ጥቅም ላይ ውለዋል።
እነዚህ ሴቶች በግል የማህበራዊ ሚዲያዎቻቸው ላይ የሚለቋቸውን ፎቶዎች በመውሰድና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በመጠቀም የለበሱትን ልብስ ከምስሉ በማጥፋት ሴቶቹ እርቃናቸውን ፎቶ የተነሱ እያስመሰሉ በቴሌግራም በኩል የሚያሰራጩ ሰዎች ስለመኖራቸውም ደርሼበታለሁ ብሏል ጥናቱ።
ጥናቱን የሰራው የደህንነት ተቋሙ ''ሴንሲቲ'' እንዳለው ከሚሰራጩት በሺዎች ከሚቆጠሩ ምስሎች መካከል ታዳጊዎችም ጭምር ይገኙበታል።
ነገር ግን እነዚህን አይነት አገልግሎት የሚሰጡት ሶፍትዌሮችን የሚሰሩ ሰዎች ይህንን የሚያደርጉት ለመዝናኛ ጥቅም ለማዋል ብቻ እንደሆነ ይገልጻሉ።
እነዚህ ሐሰተኛ ምስሎች እውነተኛ ፎቶተዎችን እና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በመጠቀም ስለሚሰሩ ሐሰተኛነታቸውን ለማወቅ በዘርፉ ከፍተኛ እውቀት እፈልጋል። ነገር ግን በርካታ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች እንዲህ አይነት እውቀት ስለማይኖራቸው በቀላሉ ይሸወዳሉ።
ሶፍትዌሮቹ ከዚህ በፊት በዋነኛነት ጥቅም ላይ የሚውሉት ሐሰተኛ የታዋቂ ሰዎችን የወሲብ ቪዲዮ ለመስራት ሲሆን የሌሎች ሰዎችን ምስል በመጠቀም ሐሰተኛ የእርቃን ምስል መስራት ግን ያልተለመደ እንደሆነ ድርጅቱ ገልጿል።
'' ማንኛውም ሰው በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚለቃቸው ምስሎች ካሉት ለእንደዚህ አይነት ጥቃት ያለው ተጋላጭነት ከፍተኛ እየሆነ መጥቷል። ከዚህ በፊት እንደዚህ አይነት ነገሮች እምብዛም ነበሩ'' ይላሉ የሴንሲቲ ዋና ስራ አስፈጻሚው ጆርጂዮ ፓትሪኒ።
በዋነኛነት በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች ባሉት ቴሌግራም ውስጥ ይህንን ሶፍትዌር መጫን ቀላል ነው። ከዛም ተጠቃሚዎች የሴቶቹን ማንኛውም አይነት ምስል ወደዚህ ሶፍትዌር ሲልኩ በደቂቃዎች ውስጥ ያለምንም ክፍያ እርቃን አድርጎ ይልክላቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, SENSITY
ቢቢሲ የዚህን ሁኔታ ለማረጋገጥ በርካታ ምስሎችን ከፈቃደኛ ሰዎች በመሰብሰብ ሞክሮ ነበር። ነገር ግን ያገኘው ውጤት አብዛኛው ከእውነተኛነት በእጅጉ የራቁ ምስሎችን ነው።
አንዳንዶቹ ምስሎች ላይ እንደውም ሶፍትዌሩ የሴቶቹን እምብርት ጎድናቸው ላይ በማድረግ መልሶ ልኳል።
እንደዚህ አይነት አገልግሎት የሚሰጥ መተግበሪያ ባሳለፍነው ዓመት እንዲዘጋ መደረጉ የሚታወስ ሲሆን አሁንም ድረስ ግን የዚህ መተግበሪያ ርዝራዦች በአንዳንድ ሰዎች እጅ ይገኛሉ።
ይህንን አገልግሎት ይሰጥ የነበረው 'ፒ' የሚባለው ድርጅት በበኩሉ ''እኛን እምብዛም አያስጨንቀንም፤ ዋናው ኣላማችን የመዝናኛ አገልግሎት መስጠት ሲሆን ምንም አይነት መጥፎ ነገር የለውም'' ብሏል።
አክሎም ''የምስሉ ጥራት እጅግ ዝቅተኛ ስለሆነ የሴቶቹን ማንነት መለየት በራሱ ከባድ ነው። ስለዚህ ሰዎችን ይህንን በመጠቀም ሴቶቹን ለማስፈራራት ሊሞክሩ አይችሉም'' ብሏል።
ምንም እንኳን እነዚህ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶችን ምስል ለማሰራጨት በዋነኛነት ጥቅም ላይ የሚውለው ቴሌግራም የተሰኘው የማህበራዊ ሚዲያ ቢሆንም በጉዳዩ ላይ ግን እስካሁን ምንም ነገር የለም።
ጥናቱን የሰራው ሴንሲቲ እንደሚለው ከሆነ ከአውሮፓውያኑ ሐምሌ 2019 ጀምሮ እስከ 2020 ባለው ጊዜ ውስጥ 108 ሺ 852 ሴቶች የዚህ ጥቃት ሰለባ ሆነዋል፤ ሐሰተኛ የእርቃን ምስላቸውም ለህዝብ ይፋ ተደርጎባቸዋል።
በተጨማሪ ደግሞ ነገሮችን ይበልጥ አሳሳሳቢ የሚያደርገው እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊ ሴቶችም ጭምር ሐሰተኛ የእርቃን ምስላቸው ለሚሊዮኖች ይፋ እየተደረገባቸው ነው።
ቴሌግራም እስከያዝነው ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ድረስ ሩሲያ ውስጥ ታግዶ እንደነበር ይታወሳል።
''እንዲህ አይነት ነገሮችን የሚፈቅዱት በርካታዎቹ ድረ ገጾች በድብቅ እንኳን አይደለም ምስሎቹን የሚያጋሩት። ይህ ደግሞ የሚሆነው በበቂ ሁኔታ ቁጥጥር ስለማይደረግባቸው ነው'' ይላሉ ጆርጂዮ ፓትሪኒ።
ጥናቱን የሰራው ሴንሲቲ ያገኘውን መረጃ በሙሉ ቴሌግራምን ጨምሮ ለሚመለከታቸው በሙሉ ቢያጋራም ምንም አይነት ምላሽ እንዳላገኘ ገልጿል።















