አፍጋኒስታናዊው በገደለው ሰው አባት በአደባባይ መገደሉን ታሊባን ገለጸ

ወታደር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አፍጋኒስታን ውስጥ በግድያ የተፈረደበት አንድ ግለሰብ በገደለው ሰው አባት በአደባባይ መገደሉን ታሊባን ገለጸ።

ታሊባን ወደ ሥልጣን ከተመለሰ ወዲህ ይህ የመጀመሪያው የአደባባይ ግድያ ነው።

የታሊባን ቃል አቀባይ እንዳሉት፣ ግለሰቡ የተገደለው ፋራህ በተባለ ግዛት በሚገኝና ሰው በተሰበሰበበት ስታድየም ውስጥ ነው።

አባቱ የተገደለበት ሰው ገዳዩን ሦስት ጊዜ ተኩሶ እንደደለው ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።

በርካታ የታሊባን አመራሮች የአደባባይ ግድያውን ተመልክተዋል።

ከሳምንታት በፊት የሸሪዓ ሕግን ለመተግበር ታሊባን መወሰኑን ተከትሎ ነው ይህ የአደባባይ ቅጣት የተፈጸመው።

ባለፈው ወር የታሊባን ከፍተኛ መሪ ሃባቱላህ አኩንዳዝዳ ዳኞች በቅጣትነት የአደባባይ ግድያ፣ በድንጋይ መውገርና የሰውነት አካልን መቁረጥን እንዲወስኑ ፈቅደዋል።

ለእነዚህ ቅጣቶች የሚያበቁት የትኞቹ ወንጀሎች እንደሆኑ ግን በግልጽ አልታወቀም።

 በቅርቡ በርካታ የአደባባይ ግርፋቶች ተፈጽመዋል። ከእነዚህ አንዱ ሎጋር በተባለ ግዛት በሚገኝና በሕዝብ በተሞላ የኳስ ስታድየም ውስጥ ብዙ ሰዎች በግርፋት መቀጣታቸው ነው።

ታሊባን ለመጀመሪያ ጊዜ በአደባባይ ቅጣት እንደሚፈጽም ያመነበትም ነበር።

ቃል አቀባዩ ዛቢሁላህ ሙጃሂድ እንዳሉት፣ ቅጣቱን የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች፣ ወታደራዊ ባለሥልጣኖች እና ሌሎችም ከፍተኛ አመራሮች በቦታው ተገኝተው ተከታትለዋል።

ታሊባን እንዳለው፣ በአደባባይ ግድያ የተፈጸመበት ሰው ታጅሚር ይባላል። ከአምስት ዓመት በፊት ሙስጠፋ የሚባል ግለሰብን በስለት ከወጋ በኋላ በሦስት የታሊባን ፍርድ ቤቶች ቅጣት ተላልፎበታል።

ቅጣቱ ከመፈጸሙ በፊት ሰዎች እንዲታደሙ ጥሪ ቀርቧል።

የተገደለው ሰው እናት ገዳዩን ይቅር እንድትለው ታሊባን በተደጋጋሚ ቢጠይቅም ይቅር ማለት ስላልቻለች እንዲገደል መጠየቋን ለቢቢሲ ተናግራለች።

“ገዳዩን በእግዚአብሔር ስም ይቅር እንድለው ታሊባን ለምኖኛል። ልጄን እንደገደለው ተገድሎ መቀበር አለበት ብያቸዋለሁ። ካልተገደለ በቀጣይም ወንጀል ይፈጽማል። ለሌሎችም መቀጣጫ ይሆናል” ብላለች።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶንዩ ጉቴሬዝ የአደባባይ ቅጣቱ “እጅግ እንዳሰጋቸው” መግለጻቸውን ቃል አቀባዩዋ ስቴፈን ትሬምብሊ ተናግረዋል።

“የግድያ ቅጣት እንዲቀለበስ እንጠይቃለን” ብለዋል።

እአአ ከ1996-2001 ታሊባን የአደባባይ ቅጣት በመፈጸም ይወገዝ ነበር።

በድጋሚ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ሴቶችን እንደማይጨቁን ቢገልጽም፣ በቆይታው የሴቶችን ነጻነት የሚገድቡ ውሳኔዎች ማሳለፉን ቀጥሏል።

መብታቸው እንዲከበር የጠየቁ ሴቶች ድብደባ ደርሶባቸዋል።

ታሊባን ወደ ሥልጣን ከተመለሰ ወዲህ ዕውቅና የሰጣቸው መንግሥት የለም። ሴቶች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን እንዲያቋርጡ ካደረገ በኋላ የዓለም ባንክ 600 ሚሊዮን ዶላር እንዳይለቀቅ አድርጓል።

አሜሪካም በመላው ዓለም የሚገኙና በቢሊዮን ዶላሮች ያሏቸው የአፍጋኒስታን ብሔራዊ ባንክ አካውንቶችን አግዳለች።