በታንዛኒያ አውሮፕላን ሐይቅ ላይ ተከስክሶ የ19 ሰዎች ሕይወት አለፈ

ሐይቅ ላይ የወደቀ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, CHARLES MWEBEYA TBC

አንድ የታንዛኒያ የመንገደኞች አውሮፕላን ቪክቶሪያ ሐይቅ አቅራቢያ በምትገኛ ቡኮባ ከተማ በሚገኝ አየር ማረፊያ ለማረፍ ያደረገው ጥረት ሳይሳካ በመቅረቱ ሐይቁ ላይ ወድቆ ቢያንስ የ19 ሰዎች ሕይወት አለፈ።

አውሮፕላኑ የተከሰከሰበት ፕሪሲሽን የተሰኘው አየር መንገድ እንደገለጸው ከሆነ ከ43 ተሳፋሪዎች መካከል 24ቱ በሕይወት ተርፈዋል።

የአውሮፕላኑ አብራሪዎች አደጋው እንደደረሰ ለባለስልጣናት የድረሱልን መልክት ያስተላለፉ ቢሆንም በሂደት ግን የእነርሱ ሕይወት ሳያልፍ እንዳልቀረ የታንዛኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ተናግረዋል።

አውሮፕላኑ ቡኮባ አየር ማረፊያ አቅራቢያ በሚገኘው የሐይቁ ዳርቻ ላይ ነበር የተከሰከሰው። የነፍስ አድን ሠራተኞች በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ ሰዎችን ለመታደግ ችለዋል።

ወደ ታንዛኒያዋ ትልቅ ከተማ ዳሬ ሰላም ለመመለስ በረራውን ለመጠበቅ በአየር ማረፊያ ተገኝቶ የነበረው አብዲ ኑር ስለተመለከተው ነገር ለቢቢሲ ተናግሯል።

‘’በጣም ነው የደነገጥነው። አንዳንድ ሰዎች በድንጋጤ ሲያለቅሱ እና ሲጮሁ ነበር። . . . መንገደኞችን ለመቀበል የተሰበሰቡ ሰዎችም በጣም ተደናግጠው ነበር። ብዙዎቹ ዘመዶቻቸውን ለመቀበል ሲጠብቁ ነበር’’ ሲልም ተናግሯል።

የበረራ አስተናጋጅ የአውሮፕላኑን የአደጋ ግዜ መውጫ በር ከከፈቱ በኋላ አሳ አጥማጆቹ ወደ አውሮፕላኑ በመግባት ሰዎችን መታደግ መቻላቸውንም ተነግሯል።

ዕሁድ ጠዋት ሶሰት ሰዓት ገደማ ያጋጠመው ይህ አደጋ መነሻው አስቸጋሪ የአየር ጠባይ መሆኑም ይገመታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአደጋ ግዜ ሠራተኞች ኤቲአር-42 የሆነችውን አውሮፕላን ስቦ ወደ ሐይቁ ዳርቻ ለማውጣት ገመድ ሲጠቀሙ እና ሰዎችም ሲጎትቱ ታይቷል።

ምንም እንኳን ከነፍስ አድን ጥረቶች በኋላ የአውሮፕላኑ ግማሽ ከፍል ከውሃው በላይ ከፍ ብሎ ቢታይም በተከሰከሰበት ወቅት ግን ከጭራው በስተቀር የአውሮፕላኑ አካል በሙሉ ሰጥሞ እንደነበር ተነግሯል።

‘’አውሮፕላኑ ወደ ማረፊያው መቃረብ ሲጀምር የአየር ጠባዩ መበላሸት ጀመረ። ይህ ደግሞ አብራሪው የሚያርፍበትን ቦታ ትቶ ሌላ አማራጭ እንዲፈልግ አስገደደው። በአጭር ግዜ እንደምናርፍ ቢነገረንም መናወጥ ጀመረ። ከዛም በቅጽበት ራሳችንን ሐይቁ ውስጥ አገኘነው’’ ሲል ከአደጋው የተረፈው ሪቻርድ ኮምባ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ከዛም በተለይ ከፊት ለፊት ተቀምጠው የነበሩ ሰዎች በውሃ መዋጣቸውን እና ከኋላ የተቀመጡት ደግሞ ከአውሮፕላኑ በመውጣት ነፍሳቸውን ለማዳን መሞከራቸውን ተናግሯል።

እንዲሁም አንድ የበረራ አስተናጋጅ በሩን ለመክፈት ጥረት ማድረጉን እና በሂደትም በሩ መከፈት ችሏል ብሏል።

‘’ከአውሮፕላኑ ስንወጣ ምንም አይነት ጀልባ አልነበረም። የነፍስ አድን ሰራተኞች እስኪመጡ ድረስ የተወሰነ ግዜ ወስዷል። የመጣው ጀልባም ያን ያህል ጥሩ ሁኔታ ላይ አልነበረም’’ ሲል ሪቻርድ ተናግሯል።

በርካታ ሰዎች በአንድ ትንሽ ጀልባ ላይ ለመሳፈር በመሞከራቸው በጣም ሰግተው እንደነበርም ተናግሯል።

የታንዛኒያው ጠቅላይ ሚኒስቴር ቃሲም ማጃሊዋ እንዳሉት በሕይወት የተረፉት ተሳፋሪዎች ወደ ሆስፒታል ተወስደው እርዳታ እያገኙ ነው። ከፍተኛ የሚባል ጉዳት ባያጋጥማቸውም ከባድ ድንጋጤ እና ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ግን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አውሮፕላኑ ወደተከሰከሰበት ቦታ በመሄድ የጎበኙ ሲሆን ሰፊ ምርመራ እንደሚደረግም ቃል ገብተዋል።

‘’እስካሁን ድረስ አስከሬን እየለየን ቢሆንም አብራሪዎቹ ግን ሕይወታቸው ሳያልፍ እንዳልቀረ እንገምታለን’’ ሲሉ ተናግረዋል።

የቡኮባ አየር ማረፊያም ላልተወሰነ ግዜ ተዘግቷል።

የታንዛኒያ ፕሬዘዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሃሰን በአደጋው የተሰማቸውን ሃዘን የገለጹ ሲሆን የነፍስ አድን ስራው እስከሚጠናቀቅ ድረስም ሕብረተሰቡ እንዲረጋጋ ጠይቀዋል።

አውሮፕላኑ ከዳሬሰላም ወደ ቡኮባ እየተጓዘ እንደነበርም ታውቋል።

ፕሪሲሽን የተሰኘው አየር መንገድ በታንዛኒያ ትልቁ የግል አየርመንገድ ሲሆን የተወሰነ ድርሻው ደግሞ በኬንያ አየር መንገድ የተያዘ ነው።