አርሰናል ቼልሲን አሸንፎ መሪነቱን ሲያስቀጥል ኒውካስል በግስጋሴው ቀጥሏል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images/Reuters
ትናንት እና ከትናንት በሰቲያ የተከናወኑት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ባማረ ጨዋታ ታጅበው አስደናቂ ውጤቶች ተዘምግቦባቸው ተጠናቀዋል።
አርሰናል፣ ኒውካስትል ዩናይትትድ እና ሊቨርፑል ከሜዳቸው ውጪ ተጉዘው ወሳኝ ሦስት ነጥቦችን ይዘው ተመልሰዋል።
ማንችስተር ዩናይትድ ደግሞ በቪላ ፓርክ የበላይነት ተይዞበት 3 ለ 1 ሲሸነፍ ዌስትሃም ዩናይትድ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት በተጨማሪ ሰዓት በተቆጠረበት ጎል በክርስታል ፓላስ 2 ለ 1 ተሸንፏል።
አርሰናል ትናንት በስታንፎርድ ብሪጅ ሄዶ ያገኘው ሦስት ነጥብ በትክክልም የሊጉ የዋንጫ ተፎካካሪ መሆኑን ያስመሰከረበት ነበር።
ቀደም ሲል ቶተንሃምን፣ ቀጥሎ ሊቨርፑልን ከዚያም ቼልሲ በመርታት የዋንጫ ተፎካካሪ መሆኑን አሳይቷል። በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ላይም ማንችስተር ሲቲን በሁለት ነጥብ በመብለጥ መሪነቱን አጠናክሮ ቀጥሏል።
ከዚህ ድል በኋላ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ቡድኑ “ወደ አዲስ ደረጃ ከፍ ብሏል” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
ወደ ሴንቲ ሜሪ ያቀነው ኒውካስል ደግሞ በተጋጣሚው ላይ አራት ጎሎችን በማስቆጠር በአስደናቂ ግስጋሴው ቀጥሏል።
ኒውካስል የትናንት ድሉን ተከትሎ ከቶተነሃም በላይ ከሲቲ በታች ሆኖ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ፓራጓዊው የፊት መስመር ተጫዋቹ ሚጉኤል አልሚሮን በትናንቱ ጨዋታው ጎል በማስቆጠር ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ለኒውካስል የተቀሩትን ጎሎች ክሪስ ውድ፣ ጆ ዊልሎክ እና ብሩኖ ጉሜሬሽ አስቆጥረዋል።
ሳውዝሃምፕተን በሜዳው እና በደጋፊው ፊት በሰፊ የጎል ልዩነት በመሸነፉ አሰልጣኝ ራልፍ ሃሳንሃትል ከሰራቸው ሊነሱ ይችላሉ የሚሉ መረጃዎች በስፋት እየወጡ ይገኛሉ።
ሳውዝሃምፕተን ከባለፉት 8 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንዱን ብቻ ነው። አሰልጣኙ ግን ከኒውካስል ጨዋታ በኋላ በሰጡት አስተያየት ትኩረታቸው የወደፊት ጨዋታዎች ላይ እንጂ ስለ ሥራቸው እንዳልሆነ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቪላ 3 - 1 ዩናይትድ
ክርስቲያኖ ሮናልዶን በቋሚ አሰላልፍ ይዘው የገቡት አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ በቪላ ፓርክ ሽንፈትን ተከናንበው ተመልሰዋል።
ስፔናዊው አሰልጣኝ ኡናይ ኤምሪ በመጀመሪያ ጨዋታቸው ቪላን መርተው በሜዳቸው ቀያይ ሴጣኞቹን ከ23 ዓመታት በኋላ ማሸነፍ ችለዋል።
ቴን ሃግ ተጫዋቾቻው ያሳዩት አቋም “መጥፎ” ነበር ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል። አሰልጣኙ ለፊት መስመር ተጫዋቹ ሮናልዶ ኳስ ለማድረስ ሲባል በረዥሙ ሲሻሙ የነበሩት ኳሶች ውጤታማ እንዳልነበሩ ተናግረዋል።
15ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ የተጠናቀቀው በቶተነሃም እና ሊቨርፑል ጨዋታ ነበር። ሞ ሳላህ በመጀመሪያው አጋማሽ ያስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች ቡድኑ ወሳኝ ሦስት ነጥብ ይዞ እንዲወጣ ረድቶታል።
በሁለተኛው አጋማሽ ቶተነሃም አጥቅቶ በመጫወት ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረገ ቢሆንም ከአንድ ጎል የዘለለ ማስቆጠር አልቻለም።
ሊቨርፑል ቶተነሃምን ያሸነፈው በኖቲንግሃም ፎረስት እና በሊድስ ዩናይትድ ተከታታይ ሽንፈቶች ከደረሰበት በኋላ ነው።
ሊጉን አርሰናል፤ ማንችስተር ሲቲ፣ ኒውካስል እና ቶተነሃምን አስከትሎ እየመራ ሲሆን ማንችስተር ዩናትድ እና ብራይተን 5ኛ እና 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ቼልሲ እና ሊቨርፑል ደግሞ 7ኛ እና 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
በወራጅ ቀጠናው ላይ ደግሞ ሳውዝሃምፕተን፣ ዎልቭስ እና ኖቲንግሃም ፎረስት ይገኛሉ።












