ዘመኑን ለኦሮሞ ሙዚቃ እና ባህል የሰጠው ታላቁ የኪነጥበብ ሰው- አሊ መሐመድ ቢራ

አሊ ቢራ

የሕይወት ዘመን የኦሮሞ ሕዝብ የጥበብ እና ባህል ባለውለታ ታላቁ አሊ ቢራ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

በወረሃ ግንቦት 1940 ዓ.ም. በድሬ ዳዋ የተወለደውን አቀንቃኝ ብዙዎች አሊ ቢራ በሚለው ስም ይወቁት እንጂ ወላጆቹ ያወጡለት አሊ መሐመድ ሙሳ ነበር።

አሊ ቢራ ነጻነት፣ እኩልነት እንዲሁም አንድነት ለናፈቁ ትዕምርታቸው ነው።

ከ1960ዎቹ ጀምሮ የኖረበትን ዘመንን ሁሉ በሙዚቃው ቀስቅሷል፤ አወድሷል፤ አዝናንቷል።

በአንድ ወቅት ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ ወቅት አሊ ቢራ 'ታሪክ ነጋሪ ነው፣ሙዚቀኛ ነው፣ የነጻነት ታጋይ ነው ይሉሀል፤ አንተስ ራስህን ምን ብለህ ነው የምትጠራው?' ተብሎ ተጠይቆ

 እኔ ተማሪ ነኝ። . . . ራሴን የማየው በዛ አይነት መንገድ ነው። ዛሬም እማራለሁ፤ ነገም እማራለሁ፤ ትላንትም ተማርኩኝ . . . እኔ የዓለም ተማሪ ነኝ። . . . በቀላሉ ራሴን የምገልጸው እንዲህ ነው።” ሲል መልሶ ነበር።

አሊ መሐመድ ቢራ በኦሮምኛ፣ በአደርኛ፣ በሶማሊኛ፣ በአፋርኛ፣ በአማርኛ፣ በእንግሊዘኛ፣ በአረብኛ እና በስፓኒሽኛ ይዘፍን ነበር።

የተለያዩ የሙዚቃ መሳርያዎችን ይጫወት የነበረው አሊ፣ ግጥምና ዜማም ይደርስ ነበር።

ከራሱ አልፎ ለመሐሙድ አህመድ፣ ለእሳቱ ተሰማ፣ ለጥላሁን ገሰሰ እና ለሌሎች ድምጻውያን ዜማዎችን ደርሷል።

የራሱን ሙዚቃ ራሱ የሚያቀናብረው አሊ፣ ከሙዚቃ መሳርያዎች አኮርዲዮን፣ ኡድ፣ጊታር፣ቶም ቶም ይጫወት ነበር።

አሊ ወደ ኢትዮጵያ ሙዚቃ መድረክ ብቅ ያለው በ1950ዎቹ ነው።

ዘመንን አልፎ የሚሄድ ሙዚቃ መስራቱን አድናቂዎቹ ይናገራሉ። “የምስራቁ ዋርካ” በማለት የሚያንቆለጳጵሱትም አሉ፤ የተወለደበትን ምስራቅ ኢትዮጵያን በማመላከት።

የአሊ ልጅነት

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አሊ ለአባቱ አንድ ልጅ ነው። በርግጥ ከእናቱ ወገን የሚወለዱ በርካታ እህትና ወንድሞች አሉት።

እናቱ እና አባቱ ሲለያዩ እርሱ የሶስት ዓመት ልጅ ነበር።

አባቴ የቧንቧ ሰራተኛ ነበር ይላል አሊ። ያደገውም ከአባቱ ጋር ነው።

አሊ የአምስት አልያም የስድስት ዓመት ልጅ እያለ፣ አባቱ ከአጎቱ ሚስት፣ ወ/ሮ መይሮ ጋር እንዲኖር አድርገውት ነበር።

ታድያ ያኔ የእለት ገቢያቸውን ዳቦ በመሸጥ የሚገፉት ወ/ሮ መይሮን ለመርዳት አሊ ዳቦውን በጭንቅላቱ ተሸክሞ ደንበኞችን ለመሳብ እያንጎራጎረ ይሸጥ ነበር።

ይህ ብልሃቱ ከሌሎች ዳቦ ቸርቻሪዎች ፈጥኖ እንዲጨርስ ብቻ ሳይሆን፣ ከዘመዱ የአምስት ሳንቲም ጉርሻ እንዲያገኝ ያስችለዋል።

ትንሹ አሊ የፊደል ዘር ሲለይ መማር የጀመረው አረብኛን ነው።

በትምህርት አቀባበሉ ፈጣን ስለነበርም ሌሎችን አረብኛ እስከማስተማር ደርሶ ነበር።

ከዚያ በኋላ ነው መደበኛ ትምህርት ቤት ገብቶ አማርኛ እና እንግሊዘኛ የመማር እድል ያገኘው።

አሊ በትምህርት ቤት፣ መምህር በሌለበት ጊዜ አልያም በእረፍት ሰዓት በማንጎራጎር እና በመደነስ ሌሎችን ማዝናናት ያስደስተው ነበር።

በተለይ የአረብኛ እና የሕንድ ሙዚቃዎችን ይጫወት ነበር።

የአሊ አባት ልጃቸው የእጅ ሙያ እንዲኖረው፣ የእንጨት ባለሙያ እንዲሆን ቢፈልጉም እርሱ ግን ከሙዚቃ ጋር ልቡ ሸፈተ።

አሊ እና አባቱ በጋራ ሲኒማ የማየት ልምድ ነበራቸው።

ለእግር ኳስም ፍቅር ነበረው። ብዙ ጊዜ ግብ ጠባቂ በመሆን ቢሳተፍም አምስት ቁጥር ለብሶ በተከላካይ መስመር ይጫወት ነበር።

ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ክቡር ዘበኛን ከተቀላቀለ በኋላም በመደፈኞቹ እና በሙዚቀኞች መካከል የእግር ኳስ ግጥሚያ ሲደረግ ሙዚቀኞችን ወክሎ ተሳትፎ ያደርግ ነበር።

አሊ ቢራ

አፍረን ቀሎ እና አሊ ቢራ

አማሌሌ፣ ሰዋሰዋ፣ ትሩምቡሌ እና ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሙዚቃዎችን ያቀነቀነው አሊ መነሻው አፍረን ቀሎ ዘመናዊ የሙዚቃ ባንድ ነው።

'አፍረን ቀሎ' አራቱ የቀሎ ልጆች እንደማለት ነው።

ስሙ መጀመርያ ለሙዚቃ ባንድ የተበጀ ሳይሆን ለሲቪክ ማህበር፣ የእድር መጠርያ ነበር፤ የአፍረን ቀሎ እድር።

በሚተዋወቁ እና አብዛኞቹ በጫት መላክ ንግድ ላይ በተሰማሩ ሰዎች የተመሰረተ ነው፤ አፍረን ቀሎ እድር።

እነዚህ የእድር አባላት በወቅቱ በድሬ ዳዋ በተለያዩ ሰርጎች እና ሕዝባዊ በዓላት ላይ ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ሙዚቀኞችን ሲመለከቱ የኦሮምኛ ሙዚቃ ቡድን እንዲኖር አጥብቀው ሻቱ።

በወቅቱ የኦሮሞን ባህል እና ቋንቋ የሚያስተዋውቅ በወጣቶች የተደራጀ ዘመናዊ የሙዚቃ ባንድ የመመስረት ፍላጎት በአፍረን ቀሎ እድር አባላት ልብ ውስጥ ይነድ ነበር።

ድሬ ዳዋ ደግሞ በእቅፏ የሙዚቃ ተሰጥኦ ያላቸውን ልጆች አቅፋ ይዛለች።

ከዚያም በ1950ዎቹ በድሬ ዳዋ ከተማ የሚኖሩ እና የሙዚቃ ፍቅር ልባቸውን ሰቅዞ የያዛቸው ወጣቶች ተሰባስበው አንድ ዘመናዊ ባንድ አቋቋሙ።

የእነ አሊ የሙዚቃ ባንድ ስያሜ ኡርጂ በከልቻ (የንጋት ኮከብ) የሚል ነበር።

የሙዚቃ ፍላጎት እና ተሰጥኦ ያላቸው ልጆች ሲሰባሰቡ የአፍረን ቀሎ ሲቪክ ማህበር አባላት በገንዘብ፣ በቁሳ ቁስ እና በሞራል ደገፏቸው።

ከዚያ በኋላ የቡድኑ ስያሜ አፍረን ቀሎ ሆነ።

አሊ ቢራ የኡርጂ በከልቻ 'ቡድን ለ' ውስጥ ይሰራ ነበር።

ልክ እንደ እግር ኳስ ቡድን የታዳጊዎች እንደማለት ነው።

ያ የታዳጊዎች ስብሰብ ደግሞ ሂሪያ ጃለላ (የፍቅር ጓደኛሞች) ይሰኝ ነበር።

እነዚህ የ ለ ቡደን አባላት ገና ታዳጊዎች ነበሩ። ያው አሊም 14 ዓመቱ ነው። ሌሎቹም የእርሱ እኩዮች ናቸው።

አሊ አንድ ስድስት ወር ከ ለ ቡድን ጋር ከተጫወተ በኋላ ወደ ትልልቆቹ ዘንድ ተመርጦ ሄደ።

በዚህ የሙዚቃ ባንድ ውስጥ ግን የነበሩት ሶስት አሊዎች ነበሩ።

አሊ ሸቦ፣ አሊ አሕመድ አሊ (አሊ ቱቼ)፣ እና አሊ መሐመድ (ትንሹ አሊ) ናቸው።

አሊ ቢራ ከሁለቱ አሊዎች አንጻር በእድሜ ትንሹ ስለነበር 'ትንሹ አሊ' ይሉት ነበር።

አሊ ቢራ ለመጀመርያ ጊዜ በሙዚቃ አድናቂዎች ፊት፣ ከአፍረን ቀሎ ባንድ ጋር መድረክ ላይ የወጣው በ1955 ዓ.ም. በኢድ አል ፈጥር በዓል ላይ እንደሆነ በሕይወት ታሪኩ ዙርያ የተጻፉ ድርሳናት ያስረዳሉ።

ይህ መድረክ በአሊ ሕይወት ውስጥ አሻራውን አተመ። ያኔ የተጫወተው “Birraa dhaa Barihe” ነበር።

ወዙ በተመጠጠ ትርጉም “ብራ ፈነጠቀ” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። ይህ ዘፈን የባንዱን ስራ በታደሙ ዘንድ ሁሉ ተዋዳጅ ሆነ። ለአሊም የአባት ስም ሆኖ አገለገለው።

ከዚያን ቀን ጀምሮ አሊ ቢራ ሙሉ መጠርያው ሆነ።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አሊ መሐመድ የሚለው ስም በአሊ ቢራ ተተክቶ በመታወቂያው ላይ ሰፈረ።

ከዚያ በኋላ ላለፉት 60 ዓመታት በኢትዮጵያ ሙዚቃ ናኘበት።

ይህ ለኦሮሞ እና ለኢትዮጵያ ሙዚቃ የተሰጠው ታላቅ ድምጻዊ ከአፍረን ቀሎ ባንድ ጋር ረዥም ጊዜ ዘልቋል።

የሙዚቃ ባንዱ ስለተመሰረተበት ዓላማ ለቢቢሲ ሲናገርም፤

“. . . ማንነታችን፣ ኦሮሞነታችን፣ ቋንቋችንና ህልውናችን ተደምስሶ በነበረበት ወቅት ነው። እኛም ታግለን እንትን እናደርጋለን በማለት ተነስቶ፤ እንግዲህ የዛሬ 57 ዓመት ፍሬ እያፈራ፤ ትንሽ የተስፋ ጭላንጭል እየታየ፤ ዛሬ እንግዲህ ፈጣሪ ይመስገን ብሔር ብሔረሰቦች እኩል የሆኑበት፤ ሁሉም የየራሱን ማንነት እያስከበረ የሚኖርበት ዘመን ተፈጥሯል። የአፍረንቀሎ መነሻውና መድረሻው በጣም የሚያስደስት ነገር ነው። ነገር ግን ከብዙ መራራ ትግል በኋላ ነው። እስር፣ ግድያ ነበረው” ብሏል።

አሊ ቢራ

አዲስ አበባ እና አሊ

አሊ ተወልዶ ያደገባት ድሬ ዳዋ ሁሉን አቅፋ ደግፋ የያዘች ነበረች።

ከአገር ውስጥ ቋንቋዎች አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ አደርኛ እና ሶማሊኛ ሲነገርባት ከባህር ማዶዎቹ ደግሞ ጣልያንኛ እና ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎችም ነበሩባት።

ምንም እንኳ አሊ የተገኘው ኦሮምኛ ከሚናገሩ ቤተሰቦች ቢሆንም ከአባቱ ጋር አረብኛ እና ኦሮምኛን እየቀላቀለ ይናገር ነበር።

ኦሮምኛ አፉን የፈታበት ነው። አረብኛ በልጅነቱ ተምሯል፤ አማርኛም በመደበኛ ትምህረት ቤት በኩል ተምሮታል።

ከዚህ ባሻገር ግን በበርካታ ቋንቋዎችም አዚሟል። ከአገር ቤት በኦሮምኛ፣ አደርኛ፣ ሶማልኛ አፋርኛ እና አማርኛ ዘፍኗል። ከባህር ማዶ ደግሞ በአረብኛ፣ ሲውድንኛ እና እንግሊዘኛ ዘፍኗል።

አሊ ቢራ ከአፍረን ቀሎ የሙዚቃ ባንድ ጋር በመሆን በድሬዳዋ ስራውን ሲያቀርብ የተመለከቱ፣ ጅቡቲ መጥቶ ለሌሎች ወጣቶች ያለውን ልምድ እንዲያካፍል እና ስራውን እንዲያቀርብ ጠየቁ።

በወቅቱ የነበሩ የድሬዳዋ አስተዳዳሪዎች ግን የአፍረን ቀሎ ባንድ አባላት ጅቡቲ የቀረበላቸውን ግብዣ ሲሰሙ ሊስማሙ አልቻሉም።

አሊ እና የባንድ ጓደኞቹ ግን በራሳቸው ወደ ጅቡቲ በማምራት ስራዎቻቸውን አቀረቡ።

ከጅቡቲ የአራት ወር ቆይታ በኋላ ሲመለሱ ግን የቡድኑ አባላት ተይዘው ዘብጥያ ወረዱ።

የተከሰሱት ደግሞ 'በጅቡቲ ስታዲየም ንጉሰ ነገስቱን [አፄ ኃይለ ስላሴ] ተሳድበዋል' በሚል የሐሰት ክስ እንደነበር ያስታውሳል።

በዚህ የተነሳ በ1956 ዓ.ም ለሶስት ሳምንት ያህል ታስሯል። ምንም እንኳ ከቀረበበት ክስ በነጻ ቢሰናበትም በወቅቱ የነበሩ የፀጥታ አካላት በውሳኔው ደስተኛ ባለመሆናቸው በተደጋጋሚ ወደ ፖሊስ ጣብያ በመውሰድ ያንገላቱት እንደነበር አሊ ይናገራል።

ከእስር ከተፈታም በኋላ ቢሆን ከእዚያው ከድሬዳዋ ሳይወጣ፣ የቁም እስረኛ ሆኖ በየጊዜው ፖሊስ ጣብያ እየቀረበ እንዲፈርም ተደረገ።

አባቱ ልጃቸው በዚህ ሁኔታ መቀጠሉ ስላሳሰባቸው ዘመድ አስቸግረው፣ ስንቅ አስይዘው ወደ አዲስ አበባ ላኩት።

አዲስ አበባ ከመጣ በኋላም የክቡር ዘበኛ ባንድ ውስጥ በ1957 ክረምት ላይ ተቀላቀለ።

አፍረን ቀሎ በድሬዳዋ የለኮሰውን ዘመናዊ የኦሮሞ ሙዚቃ አሊ ቢራ አዲስ አበባ ይዞት መጣ።

ከአፍረን ቀሎ የሙዚቃ ባንድ አባላት መካከል አዲስ አበባ መጥቶ የኦሮሞ ዘመናዊ ሙዚቃን ሰንደቅ ከፍ አድርጎ ማውለብለብ የቻለው አሊ ቢራ ብቻ ነው።

አሊ ክቡር ዘበኛን ለመግባት ከተፈተነ በኋላ ለአዲስ ዓመት ዋዜማ ስድስት ኪሎ በሚገኘው ልደት አዳራሽ ስራውን ሊያቀርብ ተዘጋጀ።

ነገር ግን የእርሱ ሙዚቃ ወደ ኋላ በመገፋቱ እና ቀጣይ ባንድ የሚጫወትበት ሰዓት በመድረሱ ለመስቀል ዋዜማ በሲኒማ ራስ እንዲጫወት ቀጠሮ ተያዘለት።

በመስቀል በዓል ዋዜማ ሲኒማ ራስ ስራውን አቅርቦ ተወደደለት።

አሊ ክቡር ዘበኛ ሲቀጠር ደመወዙ 30 ብር የነበረ ሲሆን በሶስት ዓመት ውስጥ 90 ብር እንደደረሰለት ይናገራል።

ለድሬዳዋ ልጅ ግን ይህች ገንዘብ ምንም አልነበረችም።

አሊ ቢራ ከክቡር ዘበኛ ጋር ሶስት ዓመት ከሰራ በኋላ ጥሎ ምድር ባቡር በመቀጠር፣ አዋሽ ተመድቦ መስራት ጀመረ።

በወቅቱ ምድር ባቡር 138 ብር ወርሃዊ ደሞዝ ቢከፍለውም አሊ እና የሙዚቃ ፍቅሩ ግን በቀላሉ የሚለያዩ አልሆኑም።

ለሁለት ዓመት ያህል በአዋሽ ምድር ባቡር ውስጥ ከሰራ በኋላም ዳግም ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ መጣ።

አዱ ቢራ ባንድ

አሊ ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ ከመጣ በኋላ በተለያዩ ስፍራዎች የሙዚቃ ስራውን ሲሰራ ቆይቷል።

ወቅቱ አፄ ኃይለሥላሴ ከስልጣን የወረዱበት ጊዜ ነው።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከግራ ወደ ቀኝ፣ ከቀኝ ወደ ግራ የሚላጋበት።

በዚህ መካከል አሊ የኦሮሞን ሙዚቃ ለማሳደግ እንዲረዳ ድምጻውያንን፣ ከድሬዳዋ አምጥቶ እንዲያሰለጥን ጥያቄ ቀረበለት።

አሌ ሀሳቡን ሲዋጥ በመረቅ ብሎ ተቀበለው።

የማሰልጠኑን ሃሳብ ያመጡ ወገኖች በጀት መድበው ድምጻውያንና ሙዚቀኞች ወደ አዲስ አበባ መጡ።

ሰሜን ማዘጋጃ ራስ ደስታ ትምህርት ቤት አቅራብያ ቤት ተከራይተው ሰራተኛ ቀጠሩላቸው።

በተመሳሳይ ወቅት እነ አብተው ከበደ እና ዘሪሁን ወዳጆ ያሉበት ቡድን (Burqa Boji) ከወለጋ አዲስ አበባ መጥቶ በአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ድራማ ያቀርቡ ነበር።

አሊም በፊናው ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ሙዚቃ ያቀርባል።

በዚህ ወቅት አሊ ለህብረት ትርኢት የቴሌቪዥን ፕሮግራም ሙዚቃ እንዲያቀርብ ተጋበዘ።

በአሊ ቢራ የተመራው ቡድን ግብዣውን ተቀብሎ 'አሊና ጓደኞቹ' በሚል ስም ስራውን ለማቅረብ ተገኘ።

የፕሮግራሙ ዳይሬክተር ግን አዱ ቢራ (Adduu Birra) ይባል አለ። እነ አሊም ተስማሙ።

አሊ ቢራም በዛምቤዚክ ምሽት ክበብ ከአዱ ቢራ ጋር የተለያዩ ሙዚቃዎቹን በማቅረብ አድናቂዎቹን ማዝናናት ተካነበት።

ከዚህ በኋላም በ1967 ዓ.ም ከአዱ ቢራ ባንድ የመጀመርያውን አልበም አሳተመ።

የዚሁ አልበም ቀረጻ በብስራተ ወንጌል ሬዲዮ ጣብያ የተካሄደ ሲሆን መጠርያውም አባ ለፋ (Abaa Lafaa) ይሰኛል።

በ1970ዎቹ የአሊ ዝና ጣርያ የደረሰበት ነበር። በተደጋጋሚም የሙዚቃ አልበሞቹን አሳትሟል።

አሊ ከዛምቤዚክ የምሽት ክበብ ጎን ለጎን ሆቴል ዲአፍሪክ መስራት ጀመረ።

በኦሮምኛ፣ በሶማልኛ፣ በአማርኛ እና አረብኛ የሚዘፍነው አሊ አድናቂዎቹም እንደ ቋንቋው ሁሉ መልከ ብዙ ነበሩ።

ከዚያ በኋላ አሊ ዛምቤዚክ እና ዲአፈሪክን ትቶ ራስ ሆቴል፣ ከአይቤክስ ባንድ ጋር ለመስራት እነ መሐሙድ አህመድን ተቀላቀለ።

አሊ ከአይቤክስ ባንድ ጋር አራተኛ አልበሙን የቀረፀ ሲሆን መሐመድ አህመድ በዚህ አልበም ላይ አብሮት አቀንቅኗል።

አይቤክስ ባንድ ከፈረሰ በኋላ ከኢትዮ ስታር ባንድ ጋር ሰርቷል።

አሊ ከአገር እስኪወጣ ድረስ ከአይቤክስ ባንድ ጋር ሶስት ዓመት፣ ከኢትዮ ባንድ ጋር አራት ዓመት አሳልፏል።

አሊ በአንድ ወቅት ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ እንግዲህ ለ56 ዓመት ዘፍነሀልና ላንተ ለየት ያለ ዘፈን የምትለው የትኛውን ነው? ተብሎ ሲጠየቅ እኔ 'ኮምፖዝ' ያደረኳቸው [ያቀናበርኳቸው] 267 ዘፈኖች ናቸው ካለ በኋላ "ሁሉም የኔ ልጆች ናቸው። እኔ ልጆችም የሉኝም። ያለኝ 267 ዘፈኖች ናቸው። እና ከነሱ የትኛውን ትመርጣለህ? ቢባል በየጊዜው የራሳቸው ስሜት አላቸው። ስሠራቸው የሚሰማኝ ስሜት። ስለ ፍቅር፣ ስለ ቆንጆ ልጅ፣ ከዘፈንኩ በዛን ጊዜ የተሰማኝ ስሜት አለ። ስለ 'ኢንቫይሮመን'ት [አካባቢ] ከዘፈንኩ በዛ ጊዜ ስለዘፈንኩት የሚሰማኝ ስሜት አለ። ስለ ፖለቲካም ከዘፈንኩ [እንደዛው]። እውነቴን ነው። ብዙ ሰዎች ይጠይቁኛል. . . ለዚህ ጥያቄ ግን የኔ 'ፌቨራይት' [ምርጥ] ይሄ ነው የምለው የለኝም። 267ቱንም በደንብ እንወዳቸዋለን። ለአድማጭ 'ሪፈር' የማደርገውም [የምጋብዘውም] 267ቱን ነው።" ብሎ ነበር።

እንስሳ ወዳዱ አሊ

አሊ ለእንስሳት እና ለሰው ልጆች መብት አብዝቶ ተቆርቋሪ ነው።

ይህንንም በሙዚቃ ስራዎቹ እንዲሁም በተግባር በበጎ ፈቃደኝነት በተሳተፈበት ድርጅት ውስጥ አሳይቷል።

እርሱ እና ባለቤቱ ሊሊ፣ በድሬዳዋ ለችግር የተጋለጡ 302 ሕጻናትን፣ የበጎ አድራጎት ድርጅት በማቋቋም እና በመርዳትም ይህንኑ ለተቸገሩ ድጋፍ የመሆን ባህሪውን አስመስክሯል።

አሊ በአንድ ወቅት ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቃለ ምልልስ ላይ "የሀቅ፣ የመብት፣ የሰላም፣ የበጎ ነገር ታጋይ ነኝ" ብሎ ነበር።

በእንስሳት ላይ የሚደርስ ማንኛውንም በደል የሚቃወመው አሊ፣ አህያ እና ውሻ በይበልጥ እንደሚወድ ይናገራል።

በተለይ አህያን ስልጣኔ እንዲህ የሰው ልጅን በባለ አራት እግር ጎማ ሳያንሸራሽር በፊት፣ 'አገር በማቅናት ውስጥ ትልቅ ድርሻ አላት' ሲል ይገልጻታል።

"አንዳንዴ ፈጣሪ የሚቀጣን ለእንስሳት ካለን ጭካኔ የተነሳ ነው" ሲልም ተደምጧል።

ታድያ አሊ ለአህያ ያለው መቆርቆር ወደ ዘብጥያ አስወርውሮት ያውቃል።

አንድ ቀን ራስ ሆቴል የነበረውን ስራ አጠናቅቆ ወደ ቤቱ እየተመለሰ ባለበት ወቅት ጥቁር አንበሳ ዳገቱ ላይ ከባድ ሸክም የተጫነች አህያ አልሄድ ብላ ባለቤቷ በዱላ ሲነርታት ይመለከታል።

አሊ ይሄድበት የነበረውን ታክሲ እንዲቆምለት በማድረግ፣ አህያዋን ስለምን እንደሚደበድባት ባለቤትየውን ይጠይቃል።

ያገኘው መልስ ግን 'ምን አገባህ' የሚል ነበር።

ለባለ አህያው ሁለት ብር በመስጠት ጭነቱን በታክሲ እንዲያጓጉዝ ይጠይቀዋል።

የአህያዋ ባለቤት ግን ለአሊ ጥያቄ እና ልመና ጆሮ ነፍጎ አህያዋን መደብደቡን ቀጠለ።

ይህንን ጭካኔ መታገስ ያልቻለው አሊ ዱላውን ተቀብሎ ባለቤቱን ያንቆራጥጠው ጀመረ።

ይሄኔ የአብዮት ጠባቂዎች ከአቅራብያው ቀበሌ መጥተው ወደ ፖሊስ ጣብያ ተወሰደ።

በወቅቱ ፖሊሶች ቀንደኛ የኢህአፓ አባል የያዙ ስለመሰላቸው፣ አሊን በሰደፍ ጭንቅላቱን በመምታት በአህያዋ መሳርያ ሲያጓጉዝ መያዙን እንዲያምን ይጠይቁት ጀመር።

የቀበሌው ሊቀመንበር ሲመጣ ግን ቀንደኛ የኢህአፓ አባል የተባለው ራስ ሆቴል የሚሰራው አሊ ቢራ መሆኑን አወቀ።

ከዚያም ለአህያው ባለቤት ካሳ ሁለት ብር እንዲከፍል አድርጎ እርሱን በነጻ አሰናበተው።

አሊ ቢራ

የፎቶው ባለመብት, SOCIAL MEDIA

ሽልማት እና አሊ

አሊ በፈረንጆቹ አቆጣጣር በ1984 ነው ለመጀመርያ ጊዜ ከአገር ወጣ።

ከአገር ከወጣ በኋላ በአሜሪካ ሴይንት ሞኒካ ኮሌጅ፣ሙዚቃ ተምሮ (20 century western music theory) ተመርቋል።

ትምህርት ወዳዱ አሊ ሁሌም ስለትምህርት ጠቃሚነት ይሰብካል። "መሐይምነት አእምሮን ያሳውራል" የሚለው አሊ በሄደበት ሁሉ ትምህርት ለሁሉም እንዲዳረስ ይወተውት ነበር።

በስደት ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በአሜሪካ፣ ስውዲን፣ ካናዳ እና ሌሎች አገራት የኖረው አሊ፣ በሕይወት ዘመኑ ከ50 በላይ ሽልማቶቹን ተቀብሏል።

አብዛኞቹ ከተለያዩ ድርጅቶች ለኦሮሞ ባሕል፣ሙዚቃ፣ ቋንቋ እድገት ላበረከተው አስተዋጽኦ የተሰጡ የሕይወት ዘመን ሽልማቶች፣ የአድናቆትምስክር ወረቀቶች ናቸው።

ከዚህም በተጨማሪ አሊ፣ ከጅማ ዩኒቨርስቲ እና ድሬዳዋ ዩኒቨርስቲም የክብር ዶክተሬቶችን ተቀብሏል።

ቢቢሲ የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት በሰጠው ወቅት፤ ከትውልድ ቦታውና ሙዚቃ ከጀመረበት ስፍራ ስለተሰጠው ክብር የተለየ ስሜት ተሰምቶት እንደሆነ ጠይቆት

". . . ጎንደርም ሆነ ጎጃም የትኛውም ያከበሩኝ ቦታ አንዱን ካንዱ አብልጬ አይደለም የማየው ማለቴ ነው። አንድ ፎቶ ከብዙ ሺ ቃላቶች የበለጠ ራሱን ይገልፃል ይባላል። እጄን ዘርግቼ የተነሳሁትን ፎቶግራፍ አይተው፤ ከጅማ ዩኒቨርስቲ የበለጠ ደስታ እንደተሰማኝ አድርገው ሲያወሩ ነበር፤ እኔ የሚሰማኝ ሁለቱም እኩል ነው ያከበሩኝ፤ እግዚአብሔር ያክብራቸው" ብሎ ነበር።