የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በነቀምት ከተማ ከፍተኛ ተኩስ መክፈቱ ተሰማ

የፎቶው ባለመብት, Nekemit Communication
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በምዕራብ ኦሮሚያ ነቀምት ከተማ ዛሬ ማለዳ ጥቅምት 27፣ 2015 ዓ.ም ላይ ከፍተኛ ተኩስ መክፈቱ ተሰማ።
ከአዲስ አበባ በ330 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው እና በምዕራብ ኦሮሚያ ከሚገኙ ትላልቅ ከተሞች አንዷ በሆነችው ነቀምት ከተማ ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ እየተሰማ መሆኑን ምንጮች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
በመንግሥት በሽብርተኝነት የተፈረጀውና መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች ዛሬ ጠዋት ወደ ከተማዋ ገብተው በመንግሥት የጸጥታ ሃይሎች ላይ ተኩስ መክፈታቸውን ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ዛሬ (እሁድ)ጎህ ሲቀድ ማንም ሰው መንቀሳቀስ ሳይጀምር ወደ ከተማ ገቡ። በመሃል ከተማ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ እየተካሄደ ነው። ቤታችን ውስጥ ተቀምጠን የተኩስ ድምጽ እየሰማን ነው” ብለዋል እኚሁ ነዋሪ
የቢቢሲ ምንጮች ተኩሱ በከተማዋ በሰፈረው ወታደራዊ ካምፕ አካባቢ እንደነበረም ገልጸዋል።
አንድ ሌላ ነዋሪ በበኩሉ የሰው ህይወት ስለማለፉ እንዳልሰማ እና በከተማዋ እንቅስቃሴ እንደተገደበ ለቢቢሲ ገልጾ ታጣቂዎች ወደ ከተማዋ መግባታቸውንና ተኩስ መኖሩን ተናግሯል።
ከመንግሥት በኩል ምንም አይነት መግለጫ ያልተሰጠ ሲሆን ቢቢሲ የከተማውን ከንቲባ እና የጸጥታ ባለስልጣናትን ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።
የዛሬው በከተማዋ ተኩስ መከፈት የተሰማው መንግሥት በምዕራብ ወለጋ በምትገኘው ቢላ በተሰኘችው አነስተኛ ከተማ የገቡ የኦነግ ታጣቂዎች ላይ ያነጣጠረ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ በርካታ ንፁሃን ዜጎች መገደላቸውን እማኞችና ተጎጂዎች ለቢቢሲ ከተናገሩ ከቀናት በኋላ ነው።
በዚህ ሳምንት የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ከሰባት በላይ የምዕራብ ወለጋ ወረዳዎችን መያዙን ገልጿል።
መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ቃለ አቀባይ ኦዳ ታርቢ ሰራዊታቸው ይህንን ዘመቻ እንደሚቀጥልበት እና በምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኙ የጦር ካምፖችን (ሰፈሮችን) ኢላማ ማድረጉንም ተናግረዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ተቆጣጥረዋቸዋል በተባሉ ቦታዎች ንብረት ማውደማቸውን ነዋሪዎች እና አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናግረዋል
ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች እና አንድ የዞኑ ባለሥልጣን እንዳሉት ከሆነ፣ መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራቸው ታጣቂ ቡድን አባላት መንዲ፣ ቂልጡ ካራ እና ለታ ሲቡ ተብለው የሚጠሩ ከተሞችን ተቆጣጥረዋል።
በከተሞቹ የሚገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ገሚሱ በታጣቂዎቹ የታገቱ ሲሆን፣ የተቀሩት ደግሞ ሸሽተው ጫካመግባታቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በቁጥር ያልተገለጹ የአካባቢዎቹ የመንግሥት ባለሥልጣናት መታገታቸውን ታጣቂዎቹ እራሳቸው አረጋግጠዋል።
ይህን ተከትሎ ታጣቂዎቹ በተቆጣጠሯቸው እንደ ማንዲ ባሉ ከተሞች የሚገኙ ባንኮች ላይ ዘረፋ መፈጸማቸውን እንዲሁም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ደግሞ ማውደማቸውና መዝረፋቸው የተገለጸ ሲሆን ጦሩ ይህንን አልፈጸምኩም ብሏል።
ኦዳ ተርቢ ቡድኑ በአካባቢው ያሉ የመንግሥት ጦር ካምፖችን ለመያዝ ዘመቻ እያካሄደ መሆኑን ይናገራሉ።
ቃል አቀባዩ “በአካባቢው ያለውን የመንግሥት ጦር ሙሉ በሙሉ ማፍረስ ነው” ይበሉ እንጂ ታጣቂዎች ንብረት መዝረፋቸውን እና ማውደማቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ ቃል አቀባዩ ታጣቂዎቻቸው ይህንን አለመፈጸማቸውን አስረድተዋል።።
“መምጣታችንን የፈሩ የካቢኔ አባላት እና የመንግሥት ወታደሮች ከዚያ ዘርፈው ወጡ። የአስተዳደር ቢሮዎች የጦር ካምፕ ሆነዋል። ባካሄድነው ጦርነት የጦር ካምፖቹን ስንይዝ ንብረት ወድሟል” ብለዋል።
ቃል አቀባዩ ጨምረውም ታጣቂ ቡድኑ አንድ አካባቢን ሲይዝ አለመረጋጋት ሲፈጠር እድሉን በመጠቀም ዘረፋ የሚፈጽሙ ሰዎች አሉ ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል መንግሥትም ባለፉት ዓመታት በርካታ የአካባቢ ባለሥልጣናት በታጣቂ ቡድኑ መገደላቸውን ሲገልጽ ቆይቷል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰውና በመንግሥት ሽብርተኛ ቡድን ተብሎ የተፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን በመፈጸም ይከሰሳል።
ቡድኑ ቢያስተባብልም ነዋሪዎችና መንግሥት በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰላማዊ ነዋሪዎች ሞት ምክንያት ለሆኑ ጥቃቶች የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ተጠያቂ ያደርጋሉ።












