በምዕራብ ወለጋ ታጣቂዎች ከተሞችን መቆጣጠራቸው እና ባለሥልጣናትን ማገታቸው ተነገረ

ምዕራብ ወለጋ

በመንግሥት በሽብርተኝነት የተፈረጀው እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ቡድን ታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን አንዳንድ ቦታዎችን መቆጣጠሩ እና የመንግሥት ባለሥልጣናትን ማገቱ ተነገረ።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ተቆጣጠረዋቸዋል በተባሉ ቦታዎች ንብረት ማውደማቸውን ነዋሪዎች እና አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች እና አንድ የዞኑ ባለሥልጣን እንዳሉት ከሆነ፣ መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራቸው ታጣቂ ቡድን አባላት መንዲ፣ ቂልጡ ካራ እና ለታ ሲቡ ተብለው የሚጠሩ ከተሞችን ተቆጣጥረዋል።

በከተሞቹ የሚገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ገሚሱ በታጣቂዎቹ የታገቱ ሲሆን፣ የተቀሩት ደግሞ ሸሽተው ጫካመግባታቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በቁጥር ያልተገለጹ የአካባቢዎቹ የመንግሥት ባለሥልጣናት መታገታቸውን ታጣቂዎቹ እራሳቸው አረጋግጠዋል።

ይህን ተከትሎ ታጣቂዎቹ በከተሞቹ የሚገኙ ባንኮች ላይ ዘረፋ መፈጸማቸውን እንዲሁም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ደግሞ ማውደማቸውና መዝረፋቸው ተገልጿል።

በጉዳዩ ላይ የክልሉ መንግሥትን አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። የዞኑ አስተዳዳሪዎች ለማግኘት ያደረግነው ጥረትም ሳይሰምር ቀርቷል።

ነዋሪዎች ምን ይላሉ?

አንድ የመንዲ ከተማ ነዋሪ ከሰኞ ጥቅምት 21/2015 ዓ.ም. ጀምሮ በከተማዋ የተኩስ ድምጽ መሰማት መጀሩን ይናገራል።

“የሚንቀሳቀስ ተሸከርካሪ የለም። ሱቆች በሙሉ ዝግ ናቸው። ነዋሪውም በቤቱ ተቀምጧል” በማለት ማክሰኞ ዕለት በከተማዋ ስለነበረው ሁኔታ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ሰኞ ዕለት በከተማዋ የሚገኙ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ሲቄ (በቅርቡ የተቋቋመ ባንክ) እና የብርሃን ባንክ ቅርንጫፎች እና የኢትዮ ቴሌኮም ቢሮ መዘረፉ እና መውደሙን ነዋሪዎች አክለው ተናግረዋል።

ምንም እንኳ ከላይ በስም የተጠቀሱት ባንኮች ዝርፊያ እና ውድመት እንዳጋጠማቸው ያሉት ነገር ባይኖርም ነዋሪዎች ግን ባንኮች መዘረፋቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ የደረሰውን ውድመት ሲገልጹ፤ “ሁሉም የመንግሥት ቢሮዎች ወድመዋል። የቀረ የለም” ብለዋል።

ጉዳት ካጋጠማቸው የመንግሥት ቢሮዎች መካከል ፖሊስ ጣቢያዎች እና የአስተዳደር ቢሮዎች ይገኙበታል።

አንድ ነዋሪ የመንግሥት ተቋማቱ የወደሙት ወጣቶች ከታጣቂዎች ጋር ከተባበሩ በኋላ መሆኑን ተናግረዋል።

ስሜ አይጠቀስ ያሉ አንድ የምዕራብ ወለጋ ዞን ባለሥልጣን ከላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች እንደሚገኙ ለቢቢሲ አረጋግጠው፤ ከማክሰኞ ጥቅምት 22/2015 ንጋት ጀምሮ ከመንግሥት ፀጥታ ኃይል አባላት ጋር የተኩስ ልውውጥ አድርገው ከተማ ከገቡ በኋላ በባንኮች ላይ ዝርፊያ መፈጸማቸውን ተናግረዋል።

ከመንዲ፣ ከቂልጡ ካራ እና ከለታ ሲቡ ከተሞች በተጨማሪ በነጆ ከተማ የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበር እና ለጊምቢ ከተማ ቅርብ የሆነችው ዶንጎሮ ከተማ በታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር መግባቷን እኚሁ ኃላፊ ተናግረዋል።

የአመራሮች እገታ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት በታጣቂዎች ዒላማ ስለሚደረጉ ቀድመው ሸሽተው መውጣታቸውን ይናገራሉ።

“አብዛኛው ሽሽቶ የሄደው የመንግሥት ወታደሮች ወዳሉበት የጦር ካምፕ ነው። ይሁን እንጂ ታጣቂዎቹ የጦር ካምፑን ሰብረው ሲገቡ በካምፑ የነበሩ የመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎች ሸሽተው ወጡ። በጦር ካምፑ የነበሩት በታጣቂዎቹ ሲታገቱ የተቀሩት ደግሞ ሸሽተው ጫካ ገብተዋል” በማለት ሁኔታውን አስረድተዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ምንጮች ከጦር ካምፑ የተያዙት የመንግሥት ባለሥልጣናት ወደ ታጣቂዎቹ ካምፕ መወሰዳቸውን ተናግረዋል።

ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን አዛዥ የሆነው መሮ ዲሪባ የሚመራቸው ታጣቂዎች የአካባቢዎቹን ባለሥልጣናት ከመንግሥት የጦር ካምፕ ውስጥ መያዛቸውን ተናግሯል።

መሮ ዲሪባ ይዘናቸዋል ያሏቸው የመንግሥት ሠራተኞች በጦር ካምፕ ውስጥ ሆነው ሥራቸውን ሲያከናውኑ የቆዩ ናቸው ብሏል።

ሰዎቹ የታገቱት “ከመንግሥት ጋር በመስራታቸው ነው” ያለው መሮ፤ “ከሕዝብ ጋር ካስታረቅናቸው በኋላ ወደ ቤተሰቦቻቸው ይመለሳሉ” ብለዋል።

መሮ ይህን ይበሉ እንጂ ከዚህ ቀደም በታጣቂ ቡድኑ የታፈኑ የመንግሥት ባለሥልጣናት የገቡበት ሳይታወቅ እንደቀረ የቤተሰብ አባላት እና ነዋሪዎች ሲገልጹ ቆይተዋል።

የኦሮሚያ ክልል መንግሥትም ባለፉት ዓመታት በርካታ የአካባቢ ባለሥልጣናት በታጣቂ ቡድኑ መገደላቸውን ሲገልጽ ቆይቷል።

የታጣቂ ቡድኑ ቃል አቀባይ እንደሆኑ የሚናገሩት ኦዳ ተርቢ ቡድኑ በአካባቢው ያሉ የመንግሥት ጦር ካምፖችን ለመያዝ ዘመቻ እያካሄደ መሆኑን ይናገራሉ።

ቃል አቀባዩ “በአካባቢው ያለውን የመንግሥት ጦር ሙሉ በሙሉ ማፍረስ ነው” ይበሉ እንጂ ታጣቂዎች ንብረት መዝረፋቸውን እና ማውደማቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ይሁን እንጂ ቃል አቀባዩ የታጣቂ ቡድኑ አባላት ይህንን ያስተባብላሉ።

“መምጣታችንን የፈሩ የካቢኔ አባላት እና የመንግሥት ወታደሮች ከዚያ ዘርፈው ወጡ። የአስተዳደር ቢሮዎች የጦር ካምፕ ሆነዋል። ባካሄድነው ጦርነት የጦር ካምፖቹን ስንይዝ ንብረት ወድሟል” ብለዋል።

ቃል አቀባዩ ጨምረውም ታጣቂ ቡድኑ አንድ አካባቢን ሲይዝ አለመረጋጋት ሲፈጠር እድሉን በመጠቀም ዘረፋ የሚፈጽሙ ሰዎች አሉ ብለዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰውና በመንግሥት ሽብርተኛ ቡድን ተብሎ የተፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሲፈጽም ቆይቷል።

ቡድኑ ቢያስተባብልም ነዋሪዎችና መንግሥት በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰላማዊ ነዋሪዎች ሞት ምክንያት ለመሆኑ ጥቃቶች የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ተጠያቂ ያደርጋሉ።