ለዕርዳታ እጆችዋን የምትዘረጋው ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራሷን ትችል ይሆን?

ባለፈው ወር መጨረሻ ላይ ጎረቤት አገር ኬንያ ስንዴ ከኢትዮጵያ ማስገባት እንድትችል ስምምነት ላይ መድረሷን አስታወቀች።
የኬንያው ስቴት ሃውስ ይህንን የገለጸው አዲሱ የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ከተመረጡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን መጎብኘታቸውን ተከትሎ ነው።
ሩቶ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር የሁለትዮሽ የምጣኔ ኃብትና ንግድ ውይይትን ጨምሮ በስንዴ ግዥ ላይ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ኬንያ ከኢትዮጵያ ስንዴ ለመውሰድ ያቀደችው በሃገሪቷ እየተከሰተ ያለውን የምግብ ዋጋ መናር ለማረጋጋት እንዲያስችላት መሆኑን ገልጻለች።
ከስንዴ ምርት ጋር ተያይዞ ሌላኛው ዜና የነበረው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም አማካኝነት ለኢትዮጵያ ከዩክሬን የተገዛው የእርዳታ እህል ጉዳይ ነበር።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ስንዴው ተቋሙ በጦርነት እና በአስከፊ ድርቅ ምክንያት የተጎዱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ለመመገብ የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፍ ተነግሯል።
ከእነዚህ ሁለት ከሚቃረኑ ሃሳቦችም ጋር ተያይዞ እርዳታ እየጠየቀች ያለች አገር እንዴት ራሷን በስንዴ ሳትችል ወደ ውጭ መላክ ትችላለች? የሚልም ጥያቄ አስነስቷል።
ኢትዮጵያ የተቸገሩ ህዝቦቿን ለመመገብ እርዳታ ከውጭው አለም ብትሻም ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ ስንዴ አምራች ናት።
ሆኖም በምታመርተው ስንዴ የአገር ውስጥ አቅርቦቱን መሸፈን አልቻለችም።
ለዚያም ነው አገሪቷ እየተከሰተ ያለውን እጥረት ለመሙላት መዋዕለ ንዋይ በማፍስስና በእርዳታ ስንዴ ከውጭ የምታስገባው።
ይህንንም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ታሪክ ለማድረግ፤ የህዝቧን የስንዴ ፍላጎት አሟልታ ወደ ውጭ ስንዴ ለመላክ በማለም በባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት መጠነ ሰፊ የስንዴ ምርት ልማት ውስጥ መግባቷን ትናገራለች።
በበጋ ወቅት ስንዴን ማምረት እና ተግዳሮቶቹ
በኢትዮጵያ በአብዛኛው የስንዴ ምርት የሚመረተው በአነስተኛ አርሶ አደሮች ነው።
ሆኖም ከመንግሥት በተገኘው መረጃ መስረት ባለፉት 15 ዓመታት የመካናይዝድ እርሻ ምርት በእጥፍ ጨምሯል።
ከዚህም በተጨማሪ በቅርብ ዓመታት መንግሥት 'ኩታ ገጠም' (ክላስተር)ና መካናይዝድ እርሻን በማበረታታትና እንደ ማዳበሪያና ጥራት ያለው ዘር ያሉ ግብአቶችን ድጎማ በማድረግና በማከፋፈል ላይ እንደሚገኝ ሲገልጽም ይሰማል።
እነዚህን ሁሉ ዕቅዶች ተግባራዊ በማድረግ ሃገሪቷ በአውሮፓውያኑ 2023 የስንዴ ፍላጎቷን በሀገር ውስጥ ምርት በማሟላት ከውጪ የሚገባውን ለማቆም አቅዳ እየሠራች እንደሆነም መንግሥት ይገልጻል።
ከደጋ እስከ ቆላማ አካባቢዎች የሃገሪቷ የመሬት አቀማመጥና የአየር ፀባይ ለስንዴ ምርት በጣም ምቹ መሆኑንና ይህንን እምቅ ሀብት በአግባቡ ስራ ላይ በማዋል ሃገሪቷ ለረጅም ጊዜ የምትታወቅበት የስንዴን ልመና ታሪክ ለመቀየር በተለየ ትኩረት እየተሰራ እንደሆነም ተነግሯል።
ከዚህም ጋር ተያይዞው የሚነሳው ስንዴን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ በመስኖም ለማልማት እየተሰራ ያለው ነው።
በተለምዶ ስንዴ በኢትዮጵያ የሚመረተው በከፍተኛ (በደጋ) አካባቢዎች ሲሆን ከዝናብም ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት አለው።
በአሁኑ ወቅት ዝቅተኛ (ቆላማ) በሆኑ ስፍራዎች የበጋ ስንዴ በተሰኘ የልማት ፕሮግራም የመስኖ ልማትን በመጠቀም ምርቷን ለመጨመር እየሰራች እንደምትገኝ ባለስልጣናቱ ሲናገሩ ይሰማሉ
ከአስር ዓመት በላይ በግብርና ስራ ላይ መቆየቱን የሚናገረው የሀያ ዘጠኝ ዓመቱ እንግዳ፣ 25 ሄክታር የሚሆን መሬት ተከራይቶ ሽንኩርትና ቲማቲም በማምረት ለገበያ ያቀርባል።
ይኹን እንጂ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በተከራየው ማሳ ላይ እሱ እና ሌሎች የሉሜ ወረዳ ቆቃ ቀበሌ ነዋሪዎቸው የበጋ ስንዴ እንዲያመርቱ መንግሥት ማስገደድ እንደ ጀመሩ ይናገራል።
በመሬት ኪራይ፣ የትራክተር፣ የነዳጅ፣ የውሃና ሌሎች ውጪዎችን አስልቶ አርሶ አደሩ የትኛው ምርት በየትኛው ወቅት እንደሚያዋጣው መወሰን አለበት የሚለው እንግዳ የወረዳው የመንግሥት ኃላፊዎች ግን “ሁሌ በማሳ ላይ ስንዴ ብቻ ካላየን” እያሉ እያስቸገሩ እንደሆነ ያብራራል።
ባለፈው የክረምት ወቅት ከመግባቱ በፊት በበጋ ወቅት ከስድስት ሄክታር መሬት 320 ኩንታል ስንዴ ምርት ማግኘቱንም ለቢቢሲ ተናግሯል።
እርሱና ሌሎች ስንዴ ለማምረት ፍላጎት ቢኖራቸውም በአስገዳጅነትና ያለ ፍላጎታቸውና ከዕቅዳቸው ውጪ ሲሆን ግን ተገቢ እንዳልሆነም ያስረዳል።
ባለፈው የበጋ ወቅት ስንዴ ያመረቱበት ማሳ ላይ በዚህ ክረምት ግን ሽንኩርት የዘሩ ቢሆንም የአካባቢው የመንግሥት አካላት ግን ‘ለምን ስንዴ አልዘራችሁም?’ በማለት ከማስፈራራት አልፈው የዘሩን ሽንኩርት እንዲነቅሉ እንዳስገደዱዋቸው ይገልጻል።
የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በበጋ ስንዴ ለማምረት ወደ ሙከራ ሲገባ በሃገሪቷ ከዚህ ቀደም ያልተሰራበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መጠራጠር ብቻም ሳይሆን ተቃውሞም እንደነበረ ያወሳሉ።
በክረምት ወቅት ከአንድ ሄክታር በአማካይ እስከ 32 ኩንታል የስንዴ ምርት ማግኘት የሚቻል ሲሆን በበጋ ወቅት ደግሞ በሄክታር እስከ 45 ኩንታል ይገኛል ይላሉ የክልሉ የግብርና ምክትል ኃላፊ አቶ ጌቱ።
በአንዳንድ ቦታ እንዲያውም የበጋ ወቅት ስንዴ ከተለመደው የክረምት ወቅት ምርት በእጥፍ እንደሚበልጥ ይናገራሉ።
እንግዳ በበጋ ስንዴ ወቅት የሚከሰቱ ወፎችን መከላከል፣ የተሻለ የማዳበርያ አቅርቦት ቢመቻችላቸው ስንዴን እያፈራረቁ በመዝራት ለምርታማነታቸው መጨመርም ሆነ ለማሳቸው ለምነት አስተዋጽኦው ከፍ ያለ መሆኑን ያስረዳል።
አቶ እንግዳ የበጋ ስንዴ ለማምረት በማሳቸው ውስጥ የውሃ ጉድጓድ መቆፈራቸውን ይናገራሉ።
ሶስት እና አራት ሄክታር መሬት ሊያጠጣ የሚችል የጎድጓድ ውሃ ለማስቆፈር ደግሞ እስከ 60 ሺህ ብር ፈጅቦታባቸዋለe።
ስንዴ ላለመዝራት የወሰኑ በርካታ አርሶ አደሮች የውሃ ሞተር ፓምፕ በቀበሌው ባለስልጣናት እንደተወሰደባቸውና ከገበሬዎች መካከል 10 የሚሆኑትም ለሁለት ሳምንታት ታስረው እንደተለቀቁ ለቢቢሲ ይናገራል አቶ እንግዳ።
አሁን ከተዘራ ሁለት ወር የሆነው ሽንኩርት ከማሳው ላይ ከተነቀለ ከአንድ ወር በኋላ ማሳውን በበጋ ስንዴ ለመሸፈን ቃል ቢገባላቸውም ሊቀበሉዋቸው አልቻሉም።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ከሳምንት በፊት አዳማ ወደሚገኘው የምስራቅ ሸዋ አስተዳዳሪ በመሄድ አቤቱታ ካቀረቡ በኋላ "ማንም ሳያስገድዳችሁ ማምረት ትችላላችሁ ስለተባሉ የወረዳና ቀበሌ አመራሮች ዛቻ ለጊዜም ቢሆን ጋብ ብሏል" ይላል።
የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ ጌቱ ምስራቅ ሸዋን ጨምሮ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ ባሉት ቦታዎች የጉድጓድ ውሃን ከስምንት እስከ 10 ሜትር ጥልቀት ማግኘት መቻሉ አዲስ በዚህ የበጋ ስንዴን በመስኖ በማምረት ሙከራ ሂደት ያገኙት መልካም ተሞክሮ እንደሆነ ያነሳሉ።
ይህ ደግሞ ያልጠበቁት ነገር ግን ለበጋ ስንዴ ምርት ቀጣይነት ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ እንዳለው ያብራራሉ።
አብዛኛውን ጊዜ የምርት ግብዓትንና ሙያዊ ድጋፎችን በአግባቡ ለመጠቀም፣ እንደዚሁም የወፍ ወረራን ለመከላለከል የበጋ ስንዴ በተበጣጠሰ ትናንሽ የአርሶ አደሮች ማሳ ይዞታ ላይ ሳይሆን ለኩታ ገጠም የሚመቹና ወጥነት ባላቸው ይዞታዎች ላይ እንደሚካሄድ ይገልጻሉ።
በበጋ ወቅት በበሬ ማረሱ አስቸጋሪ ስለሚሆንም በተለያዩ ወረዳዎች የእርሻ ትራክተሮች የማቅረብ ስራም እንደተሰራም ጨምረው አስረድተዋል።

ግብርናው ከዝናብ ጥገኝነት ይላቀቅ ይሆን?
ዶ/ር ደምስ ጫኔ ከኢህአዴግ ግዜ ጀምሮ የተለያዩ የግብርና ፖሊሲና የጥናት እንቅስቃሴዎች ላይ የተሳተፉ ምሁር ናቸው።
በዚህ ርእሰ ጉዳዩ ላይ አምስት የምርምር ስራዎች አዘጋጅተዋል። ከእነዚህም በአውሮፓውያኑ 2015 በእንግሊዝኛ የተዘጋጀው ‘ኢትዮጵያ ግብርናዋን እንዴት ማዘመን’ እንዳለበት የሚያታተው ጽሁፍ ይገኝበታል።
እርሳቸው ከሌሎች የውጪ ምሁራን ጋር ሆነው ባቀረቡት ጥናት በአገሪቱ ዝናብ ላይ ጥገኛ የሆነውን ግብርናን ለማላቀቅ መስኖን መሰረት ያደረገ ግብርና እንዲጀመር ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል።
ሆኖም በወቅቱ ስንዴ ስንዴ በመስኖ ልማት ማምረት ብዙም አልተሰራበትም ነበር ይላሉ።
“ ባለፈው ዓመት ግን ስንዴን ለማምረት በመስኖ ልማት የተሸፈነ የመሬት ስፋት 670 ሽህ ሄክታር ደርሷል” ይላሉ።
ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ባሉት አገራት ስንዴን በስፋት የማምረት ዓቅም ያላት መሆኗን ኢካርዳ [ICARDA] በተባለው ድረገጽ የሰፈረው መረጃ ያመላክታል።
እነዚህ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአውሮፓውያኑ 2020 በአገሪቱ በመስኖ የለማ መሬት ስፋት 20 ሽሕ ሄክታር ብቻ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኩታ ገጠም የማምረት ለበጋ ስንዴ ምርት የተሻለ መሆኑን ከማብራራት በተጨማሪ ስንዴ ከውጪ ማስገባት ለማስቀረት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
አቶ ጌቱ በኩታ ገጠም አማካኝነት የሚካሄደው የበጋ ስንዴን በመስኖ ማልማት አዲስ እንደመሆኑ መጠን ማመንታቱ መኖሩን ያስረዳሉ።
“ይቅርና ለአርሶ አደሩ ለባለሙያዎች፤ ለአመራሩም ጭምር የበጋ ስንዴ እንዴት ተግባራዊ ይሆናል? የሚለው ጥያቄ ነበር። በኋላ ላይ በጥናትና ምርምር ከደጋ እስከ ቆላ ድረስ ምርታማነቱ ስለተረጋገጠ በሁሉም ደረጃ አርሶ አደሩ ስለበጋ ስንዴ ግንዛቤ እንዲያገኝ ተደርጓል” ይላሉ።
አሁን ግንዛቤው ከመፈጠሩ የተነሳ ከአንድ ሚሊዬን ሄክታር በላይ በበጋ ስንዴ የተሸፈነው ማሳ አርሶ አደሩ አምኖበትና ተረድቶት በራሱ ተፈጻሚ እያደረገ እንደሆነ በመግለጽ “አሁን ባለቤቱ አርሶ አደሩ ሆኗል” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢትዮጵያ እንዴት ስንዴ ወደ ውጭ መላክ ትችላለች?
ኢትዮጵያ የአገር ውስጥ የስንዴ አቅርቦት ፍላጎቷን ለማሟላት ከበጀቷ ቀንሳ በውጪ ምንዛሪ ከሌሎች አገራት ታስገባለች።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱ ሃገሪቱ የምትጠቀመው ስንዴ 70 በመቶ የሚሆነው በሃገር ውስጥ የሚመረት ሲሆን 30 በመቶውን ደግሞ በግዢ ወይም በእርዳታ መልክ ከውጪ ታስገባለች።
በተለያዩ ምክንያቶች ድጋፍ ለሚፈልጉት የህብረተሰብ ክፍልም ከውጪ በእርዳታ መልክ በሚመጣ ይሸፈናል።
በሀገሪቷ በተራዘመ ድርቅ፣ በግጭቶችና በተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ ችግሮች ምክንያት ለችግር የተጋለጡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች እርዳታ ጠባቂ ሲሆኑ ለዚህ እርዳታ ደግሞ አሁንም ስንዴ ከውጪ ይመጣል።
በቅርቡም በጦርነት ቀጠና ካለችው ዩክሬን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም አማካኝነት ለኢትዮጵያ ተገዝቶ የመጣው ስንዴ የሚጠቀስ ነው።
በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ሳብያ በተለይም በትግራይና አዋሳኝ በሆኑ የአማራና አፋር ክልሎች እስከ 9 ሚሊዮን ህዝብ የእርዳታ ጠባቂ መሆኑንን የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት ያመለክታል።
በምስራቁ የአገሪትዋ ክፍል ደግሞ በድርቅ ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አስቸኳይ ዕርዳታው እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ይነገራል።
በዚህ ሁኔታ ኢትዮጵያ እንዴት ስንዴን በወጪ ንግድ መላክ ትችላለች? የሚለው ጥያቄ የሚነሳ ከዚህም አንጻር ይመስላል።
አቶ ጌቱ ጥያቄው መኖሩ የሚገርም እንዳልሆነ በመጥቀስ እንዲህ ያብራራሉ።
መጀመሪያ የበጋ ስንዴ ልማት ተግባራዊ ይሆናል ወይ? የሚለውን መጀመሪያ ባለሙያዎች ራሳቸው አላመኑበትም ነበር ይላሉ።
በኋላ በተግባር በሰርቶ ማሳያ በኩታ-ገጠም ማሳ ላይ የበጋ ስንዴ ውጤታማ ሆኖ ሲያዩ ግን ሁሉም አምኖ መቀበል ብቻ ሳይሆን ድጋፍ ወደ ማድረግም ተሸጋግረዋል ይላሉ ።
“ሰው የተረዳውን ያህል ይናገራል” የሚሉት አቶ ጌቱ “ኢትዮጵያ እንዴት ስንዴ ወደ ውጪ መላክ ትችላለች ? የሚለውም ጥያቄም በተግባር እስከሚያዩት እንደሆነ “ያመላክታሉ።
ተመራማሪው ዶ/ር ደምስ ጫኔ በበኩላቸው “የምትለምን አገር ወጪ ንግድ ማድረግ አትችልም” በሚለው አይስማሙም።
“በቅርብ ጊዜያት እንደሚባለው አይደለም። እኛ ስንናገር በጥናት አስደግፈን ነው። መጀመርያ ኢትዮጵያ ስንዴን ከውጭ መግዛት መቆም እንዳለበት ነው የተናገርነው። ይህንን ሃሳብ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በስልጣን ላይ ባሉበት ወቅት ነው ሃሳቡ የቀረበው” ይላሉ።
በወቅቱ ወደ 600 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የሚጠጋ ስንዴ ከውጭ ይገዛ እንደነበር ያስታውሳሉ።
የዛሬ አራት ዓመት የመንግሥት ለውጥ በሚደረግበት ወቅት አገሪቷ ያላት የማምረት ዓቅምና ምን መምሰል እንዳለበት ተጨማሪ ጥናት ለመንግሥት ማቅረባቸውን ያስታውሳሉ።
“በመጀመርያ አገር ውስጥ ያለው ፍላጎት መሸፈን አለብን። ያንን ሸፍነን የሚተርፈን ከሆነ ለወጪ ንግድ ቢውልም ችግር የለውም” ይላሉ።
በዋናነት ስንዴ ወጪ ንግድ መደረግ አለመደረጉ ብዙም እንደማያሳስባቸው የሚናገሩት ዶ/ር ደምስ በዋናነት “በዘላቂነት እንዴት ማስቀጠል ይቻላል?” የሚል ጥያቄ እንደሚፈጥርባቸው ይናገራሉ
በተጨማሪም ወደ ሃገሪቱ በእርዳታ መልክ የሚገባው የስንዴ እርዳታም ቢሆን በጦርነት ለተፈናቀሉና በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚደርስ ስለሆነ አስፈላጊ ነው የሚል እምነት አላቸው።

የፎቶው ባለመብት, PM Abiy
‘ፖሊሲው አዲስ አይደለም’’
የኢህአዴግ መራሹ መንግሥት አገሪቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ግብርና መር ፕሮግራም [አድሊ] እንደነበር ይታወሳል።
ለተከታታይ በርካታ ዓመታትም የአገሪቱ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ሁለት አኃዝ የነበረ ሲሆን የግብርናው ዘርፍ የአንበሳ ድርሻ ይዞ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በጥናቶቻቸው የአድሊን ጥንካሬንና ድክመትን የገመገሙት ዶ/ር ደምስ፣ ቀድሞ የተቀረጸው ፖሊሲ ውጤት አላስገኘም ማለት ሳይሆን ተገኝቶ የነበረውን ውጤት “ለበለጠ ደረጃ ማሸጋገር ያስፈልጋል” ይላሉ።
በኢህአዴግ የግብርና አሰራር በመሬትና በጉልበት ላይ የተመሰረተ እንደነበር ጠቅሰው በጥናታቸው በካፒታል የተመሰረተ ቢሆን የበለጠ ውጤት ማምጣት ይቻላል የሚል አንጸባርቀዋል።
እንደ እርሳቸው እምነት ይሄ ወደ መካናይዝድና ዘመናዊ እርሻ የሚያሸጋግር መንገድ እንደሆነ ጠቅሰው ኮመርሻል የሆኑ እርሻዎችን ማስፋፋት በምሳሌነት ይጠቅሳሉ።
በአሁኑ ወቅት “ከመሬትና ጉልበት ላይ ተኮር ከሆነው ስትራቴጂ ወደ መካናይዜሽን የመግባት እንቅስቃሴዎች” እንዳሉ ዶ/ር ደምስ ይገልጻሉ።
አክለውም “በእርግጥ ይሄ ከዛኛው የተለየ ነው ማለት አንችልም። ይሄኛው በፊት ከነበረው ጠንካራ ጎኑ ላይ እየተረማመደ መስተካከል ያለባቸው ፖሊሲና ስትራተጂዎችን እያሰተካከለ የመጣ ነው።አዲስ ነገር ተከስቶ ነው የሚል እምነት የለኝም” ይላሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኩታ ገጠም አሰራር ላይ የሚነሱ ስጋቶች
በዚህ ዘርፍ ላይ ጥናት ካደረጉት ባለሞያዎች መካከል አንዱ ዶ/ር ዮሴፍ ገብረ ሃዋርያት ናቸው።
ዶ/ር ዮሴፍ በአዲስ አበባ ጽህፈት ቤት የሚገኘው የቢኦቨርሲቲ ኢንተርናሽናል እና የሲአይኤአር ሲጂአይአር ማዕከል አለም አቀፍ ሳይንቲስት ሲሆኑ ጥናታቸው የተለያዩ ዝርያዎች የመጠቀም አስፈላጊነትን ይመለከታል።
“በስንዴ ራሳችንን ችለን እንደተባለው የወጪ ንግድ ለማድረግ አቅሙ አለን። ነገር ግን የምንሰራበትን መንገድ መምረጥ አስፈላጊ ነው” ይላሉ።
በኢትዮጵያ ውስጥ ኩታ ገጠም በምን መልኩ እየተተገበረ እንደሆነ “ጥልቅ መረጃ የለኝም” ቢሉም አልፎ አልፎ ይታያሉ ስላሏቸው ችግሮች ያነሳሉ።
ተመራማሪው ስንዴ እየተመረተ ያለው ሌሎችን ምርቶችን ገሽሽ በማድረግ እንዳይሆን ስጋት አላቸው።
“ሌሎች ሰብሎች ይመረቱበት የነበሩ ቦታዎችን ‘ዲስፕሌስ’ [ሙሉ በሙሉ በመተካት የሚደረግ ከሆነ] የስንዴ ምርት ሊጨምር ይችላል። ነገር ግን የዛኛው የተተወ ሰብል ምርት መጠን የመቀነስ ሁኔታ ሊኖር ይችላል” ሲሉም ያብራራሉ።
ሁለቱ ቢቢሲ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች ሽንኩርትና ቲማቲም ሲያመርቱበት የነበረው የእርሻ ቦታ አሁን ባለው አሰራር ስንዴ እየተመረተበት እንደሆነ ይናገራሉ።
አጥኚው ይሄ የሚሆነው ዓላማውን በትክክል አለመረዳት ያስከተለው ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አላቸው።
በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው ዘዴ ‘ኩታ-ገጠም’ አንዱ መንገድ እንደሆነ የሚገልጹት ተመራማሪው የአርሶ አደሮችን ፍላጎት መሰረት ያደረገና በመግባባት ላይ የተመሰረተ ብቻ መሆን እንዳለበት ያምናሉ።
“የተበጣጠሰ የመሬት ይዞታ ባለበት ሃገር፣ አንድ ላይ አቅዶ ለመስራት ያስቸግራል። ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት አሰራሮች ማምጣቱ ተገቢ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ተገቢነቱ ልክ የሚሆነው አርሶ አደሮችን ያማከለ መሆን ሲኖርበት ብቻ ነው” ብለዋል።
ከአሰራሩ ዘላቂነት አንጻርም አንድ ሰብል ብቻ ላይ ማተኮር በዘላቂነት የአካባቢውን የተፈጥሮ ሁኔታ ሊጎዳ የሚችል እንደሆነም ያስረዳሉ።
“ አሰራሩ ‘ባዮዳይቨርሲቲው ኮምፕሮፕሮማይዝ’ የሚያደርግ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም፣ አንድ ዓይነት ዝርያ ብቻ የሚመረት ከሆነ ለአየር ለውጥ ተጋላጭነት ሊጨምር ይችላል። ምክንያቱም ያንን ዝርያ የሚያጠፋ አንድ ክስተት ቢከሰት መጥፎ ውጤት ነው የሚያስከትለው” ይላሉ።
“አንዱ አካባቢ ላይ ስንዴን ብቻ መመረት የለበትም ። ባቄላ ወይም ሌሎች ሰብሎች ተመርተው በቀጣዩ ዓመት መቀያየር ይኖርበታል። የተፈጥሮ ጸጋን የጠበቀና የአዝርዕት ብዝሃነት መሰረት ያደረገ መሆን ሊኖርበት ይገባል” በማለት ምክራቸውን ይለግሳሉ።












