በአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ትራምፕና ባይደን በቅስቀሳ ተጠምደዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ቀዳሚያቸው ዶናልድ ትራምፕ በተለያዩ ግዛቶች በቅስቀሳ ተጠምደዋል።
ባይደንና ትራምፕ በየፊናቸው መራጮችን 'ከፊታችሁ አደጋ አለ፤ አኛን ካልመረጣችሁ' ሲሉ ቀስቅሰዋል።
በአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ የሚደረገው በኅዳር ወር አዲስ ፕሬዝዳንት ወይም ለሁለተኛ ዘመን የተመረጠ ፕሬዝዳንት ነጩ ቤተ መንግሥት በገባ በ2ኛ ዓመቱ ላይ ነው።
በዚህ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ በተጓደሉና ዘመናቸውን በጨረሱ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤትና የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አባላት ምርጫ ይደረጋል።
በአጋማሽ ዘመን ምርጫ ለሁለቱ ምክር ቤቶች አባላት የሟሟያ ምርጫ ብቻም ሳይሆን የግዛት አቃቢያን ሕግ፣ አስተዳዳሪዎች፣ ተወካዮች ወዘተ ምርጫዎች አብረው ይደረጋሉ።
የዘንድሮ ምርጫ ከረዥም ዓመታት በኋላ ከፍተኛ ውጥረት የነገሰበት ነው ተብሏል።
በተለይም ዲሞክራቶች በሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ያላቸውን የአንድ ድምጽ የበላይነት ጨርሶውኑ ያጣሉ የሚል ስጋት አድሯል።
የሕግ መወሰኛው ብቻም ሳይሆን የሕግ መምሪያው ምክር ቤትም ቢሆን አሁን ሪፐብሊካኖች ይቆጣጠሩታል የሚለው ፍርሃት/ተስፋ በስፋት እየተሰማ ነው።
የሕዝብ አስተያየት መለኪያዎች የሚያሳዩትም ይህንኑ ነው።
ሪፐብሊካኖች አንዱን ምክር ቤት ከተቆጣጠሩት ጆ ባይደን ደንቦችንና ሕጎችን ለማጽደቅ ከዚህ ወዲያ ፈተና ይሆንባቸዋል።
ዛሬ ሰኞ የምርጫ ቅስቀሳው የመጨረሻ ቀን ነው።
ጆ ባይደን ትናንት በኒው ዮርክ ከተማ ገዥ ለመሆን ለሚወዳደሩት ካቲ ሆቹል የቅስቀሳ ንግግር አድርገዋል። በኒው ዮርክ የትራምፕ ወዳጅ ሊ ዘልዲን ጥሩ ተፎካካሪ ሆነው ቀርበዋል።
ካቲ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን፣ ከምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሐሪስ እና ከቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሒላሪ ክሊንተን የቅስቀሳ ድጋፍ አግኝተዋል።
በዘንድሮ አጋማሽ ዘመን ምርጫ ከዚህ ቀደም ዲሞክራቶች በቀላሉ ያለምንም ውጣ ውረድ ድምጽ የሚያገኙባቸው ግዛቶች ሳይቀሩ ፊታቸውን አዙረውባቸዋል።
ብዙዎቹ የቅስቀሳ ንግግሮች መራጮችን በማስጠንቀቅ ላይ ያተኮሩ ናቸው።
ጆ ባይደን በአንድ የቅስቀሳ ንግግራቸው ይህ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ አሜሪካ ለሚቀጥሉት 20 ዓመታት ምን እንደምትመስል የሚወሰንበት ይሆናል፤ ልብ አድርጉ!' ብለዋል።
ጨምረውም፣ ሁለት ፍጹም የማትመሳሰል የአሜሪካ ገጽታዎች ለምርጫ ቀርበዋል፤ የምትመርጡትን ከወዲሁ እወቁበት ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ዶናልድ ትራምፕ በማያሚ ባደረጉት ቅስቀሳ ደግሞ 'ይሄ ጆ ባይደን አሜሪካንን ኮሚኒስት አገር አደረጋት' ሲሉ ከሰዋል።
የዶናልድ ትራምፕ የማያሚ ቅስቀሳ ለአንድ ሰዓት የዘለቀ ነበር።
‘ዲሞክራቶች አሜሪካንን እንደ ቬንዝዌላና ኩባ ሊያደርጓት ይሻሉ’ ሲሉም ተናግረዋል ዶናልድ ትራምፕ።
ዶናልድ ትራምፕ በፈረንጆች 2024 ወደ ሥልጣን ለመመለስ እንዳሰቡ ፍንጭ ሰጥተዋል ትናንት ኦሃዮ ላይ በነበራቸው የቅስቀሳ ንግግር።
ዶናልድ ትራምፕ በድጋሚ ለፕሬዝዳንትነት ከተወዳደሩ የመመረጥ ሰፊ እድል እንዳላቸው ይነገራል።
የሕዝብ አስተያየቶች እንደሚያሳዩት አሁን ባለው ሁኔታ ዲሞክራቶች በሕግ መምሪያው ምክር ቤት የሚኖራቸውን የበላይነት ለሪፐብሊካኖች ማስረካባቸው አይቀርም።
በሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ደግሞ ማን የበላይነቱን ይይዛል የሚለው ከፍተኛ ፉክክር ይታይባቸዋል ተብለው በሚጠበቁት ሦስት ግዛቶች ማለትም በፔኒሲልቬኒያ፣ በጆርጂያ እና ኔቫዳ ምርጫ ውጤቶች ይወሰናል።
ላለፉት ሁለት ዓመታት ዲሞክራቶችና ሪፐብሊካኖች በሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ያላቸው መቀመጫ እኩል 50-50 ቢሆንም የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሚላ ሐሪስ ስለሆኑ ዲሞክራቶች በአንድ ድምጽ የበላይነት ነበራቸው።
እስከ አሁን 40 ሚሊዮን አሜሪካዊያን በፖስታ ድምጽ ሰጥተዋል።
ዛሬ ሰኞ አሜሪካ ሲነጋላት ባይደን በሜሪላንድ የመጨረሻ ቅስቀሳ ያደርጋሉ።
ማምሻ ላይ ደግሞ ዶናልድ ትራምፕ በኦሃዮ ለጄዲ ቫንስ የቅስቀሳ ድጋፍ ይሰጣሉ።
ቀዳማዊት እመቤት ጂል ባይደን ወደ ቨርጂኒያ አቅንተው ለእንደራሴ ጄኔፈር ዌክስተን ድጋፋቸውን ይሰጣሉ።
የዘንድሮ አጋማሽ ምርጫ ዋንኛ አጀንዳዎች የኑሮ መወደድ፣ የነዳጅ ዋጋ ንረት፣ ወንጀል መበራከት፣ ውርጃ፣ እና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት አደጋ ላይ መውደቅ ናቸው።
ዲሞክራቶች በተደጋጋሚ ትራምፕን መሰል ሰዎች ሥልጣን ከያዙ የአሜሪካ ዲሞክራሲ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይቀለበሳል ሲሉ በተደጋጋሚ ያስፈራራሉ።












