ትራምፕ እና ኦባማ ስለመጪው የግማሽ አመት ምርጫ ምን አሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሁለቱ የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዘዳንቶች ባራክ ኦባማ እና ዶናልድ ትራምፕ በፔንሲልቫኒያ ባደረጉት የግማሽ አመት የምርጫ የድጋፍ ቅስቀሳ ምሽት ላይ ሁለቱም ስለ አገራቸው ያላቸውን የተለያየ ስጋት ገልጸዋል።
ኦባማ ይህ የግማሽ አመት ምርጫ የአሜሪካን የዴሞክራሲ ጉዞ የሚወስን ነው ሲሉ፤ ትራምፕ ደግሞ የአገሪቷን የደህንነት ጉዳይ ቁርጡን የምናውቅበት ነው ሲሉ ቀስቅሰዋል።
የፔንሲልቫኒያ ግዛት ዴሞክራቶችም ሆኑ ሪፐብሊካን የበላይነት የሌላቸው ሲሆን በተለያየ ግዜ ለተለያየ ፓርቲ የሚመረጥበት በተለምዶ ‘’ስዊንግ ስቴት’’ ተብለው ከሚጠሩ ግዛቶች አንዱ ነው።
በግዛቲቱ ሪፐብሊካኑም ሆኑ ዴሞክራቱ በሚያሸንፉበት ወቅት የሚኖረው የድምጽ ልዩነት እጅግ ጠባብ ነው።
በቅርቡ ለሚካሄደው የግማሽ አመት ምርጫ የግዛቲቱ ድምጽ አጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ነው ሁለቱ የቀድሞ ፕሬዘዳንቶች ፓርቲያቸውን ለማገዝ እና ለመቀስቀስ የተገኙት።
እ.ኤ.አ. በ 2016 ትራምፕ ዋይት ሃውስን ለማግኘት የዚሁ ግዛት ድል ረድቷቸዋል። በመቀጠልም በ 2020 የጆ ባይደን የትውልድ ግዛት የሆነችውን ፔንሲልቫኒያን ዴሞክራቶች 2 በመቶ በሚሆን የድምጽ ብልጫ አሸንፈው ተረክበዋታል።
ጆ ባይደን በፊላደልፊያ ቅዳሜ ዕለት ተገኝተው ቅስቀሳቸውን ባደረጉበት ወቅትም ‘’ወደ ቤቴ በመመለሴ ደስ ብሎኛል’’ ብለዋል። ፓርቲያቸው ላቀረባቸው ዕጩም ድጋፋቸውን ለግሰዋል።
ዲሞክራቶች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ ድምጽ የማያገኙ ከሆነ የጤና መድህን ብሎም የጽንስ ማቋረጥ መብቶች ላይ ተጨማሪ እገዳ እንዲጣል ማስቻል እንደሆነም ተናግረዋል።
የምርጫው ውጤት ትንበያዎች እንደሚያሳዩት ዴሞክራቶች በኮንግረስ የበላይነትን አያገኙም። ይህንንም ተከትሎ ቢያንስ በሴኔት የበላይነትን ለማግኘት ከፍተኛ ትንቅንቅ እያደረጉ ናቸው።
‘’በዚች የአሜሪካ የልብ ምት በሆነችው ግዛት ውስጥ መስቀለኛ መንገድ ላይ እንገኛለን’’ ሲሉ ጆ ባይደን ተናግረዋል። አክለውም ለዲሞክራቶች ድምጽ መስጠት ማለት ለሴቶች ጤና፣ በጦር መሳሪያ ቁጥጥር ብሎም ለጤና አገልግሎት ድምጽ መስጠት ነው ሲሉም አክለዋል።
አንድ የግዛቲቱ ነዋሪ የትኛውንም ፓርቲ ይደግፉ የፕሬዘዳንቶቹ መገኘት ነዋሪው ወጥቶ እንዲመርጥ ያስችላል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ነገር ግን ፕሬዘዳንቶቹን ለመመልከት ከወጡት ነዋሪዎች መካከል የተወሰኑ ኦባማን ለማየት መምጣታቸውን እና ባይደን ለብቻቸው ቢሆኑ ኖሮ ግን እንደማይመጡ ተናግረዋል።
በምርጫ ዘመን አጋማሽ ላይ የሚደረገው ይህ ‘የሚድ ተርም’ ምርጫ በስልጣን ላይ ያለው ፕሬዘዳንት ላይ የሚደረግ ሕዝበ ውሳኔ ተደርጎ ይታያል። የጆ ባይደን ተቀባይነት 40 በመቶ ላይ እንዳለ በሚነገርበት በዚህ ወቅት ሪፐብሊካኑ የኑሮ ውድነት እና ስደትን የመሳሰሉ ምክንያቶችን በማንሳት ፕሬዘዳንቱ ላይ ቅስቀሳቸውን እንዲያጧጡፉም ረድቷቸዋል።
ትራምፕ በበኩላቸው ዲሞክራቶች በዋሽንግተን የሚቆዩ ከሆነ ለተጨማሪ ወንጀሎች እንዲሁም ላልተገደበ የስደተኞች ፍሰት ያጋልጣሉ ሲሉ ቀስቅሰዋል።
‘’ለቤተሰባችሁ ደህንነት እና ጥበቃ የምትፈልጉ ከሆነ እያንዳንዱን ዴሞክራት በድምጻችሁ ከወንበሩ ማስነሳት አለባችሁ’’ ብለዋል።
‘’ያለው ምርጫ አንድ ብቻ ነው። የአሜሪካን መውደቅ የምትፈልጉ ከሆነ ድምጻችሁን ለአክራሪ ዴሞክራቶች ስጡ። የአገራችንን መውደም የማትፈልጉ ከሆነ ግን ሪፐብሊካንን ምረጡ’’ ሲሉ ትራምፕ ቀስቅሰዋል።
እንዲሁም በ 2024 ለሚደረገው ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ሊወዳደሩ እንደሚችሉም ጠቁመዋል። እንዲሁም በድጋሚ የአሜሪካ የምርጫ ስርአት የተጭበረበረ ነው የሚለውን የሃሰት ክሳቸውን ማቅረባቸውን ቀጥለዋል።
አንድ የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊ የቀድሞው ፕሬዘዳንት ‘’ህይወትን ያለ ጭቆና እና ምን ማድረግ እንዳለብን ሳይነገረን እንድንኖር ረድተውናል’’ በሚል ለድጋፍ መውጣቱን ተናግሯል።
በርካታ መራጮች በፍርሃት እና በሃሰት ቅስቀሳዎች ታጅበው ከሁለት ቀናት በኋላ በሚካሄደው የግማሽ አመት ምርጫ ይሳተፋሉ። ይህም የአሜሪካን የምርጫ ስርአት ታማኝነት የሚፈተሽበት ነውም ብለው ያምናሉ።












