የትዊተር መስራች ከኤሎን መስክ ግዢ በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ አስተያየቱን ሰጠ

የትዊተር ተባባሪ መስራች እና የቀድሞው ዋና ስራ አስፈጻሚ ጃክ ዶርሲ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የትዊተር ተባባሪ መስራች እና የቀድሞው ዋና ስራ አስፈጻሚ ጃክ ዶርሲ በቅርቡ በጅምላ ለተቀነሱ የትዊተር ሰራተኞች ድርጅቱን ‘’በፍጥነት አሳድጌዋለሁ’’ ሲል ይቅርታ ጠየቀ።

የአለማችን ቁንጮ ሃብታም ኤሎን መስክ 44 ቢሊዮን ዶላር አውጥቶ የማህበራዊ መገናኛ ሚዲያውን ከገዛው ወዲህ ሰራተኞቹን በግማሽ በማባረር ላይ ይገኛል።

ለዚህ እርምጃውም ትዊተር በቀን 4 ሚሊዮን ዶላር እየከሰረ ስለሚገኝ ነው የሚል ምክንያትን ሰጥቷል። የትዊተር ሰራተኞች ማሕበራዊ መገናኛ ዘዴውን በመጠቀም ቁጣቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

ጃክ ዶርሲ በአንድ የጡመራ ዘዴ ላይ ባጋራው መግለጫ ‘’የትዊተር ሰራተኞች ጠንካራ እና የማይበገሩ ናቸው’’ ብሏል። ‘’የቱንም ያህል አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ ሁል ግዜም መውጫ መንገዱን ያገኛሉ’’ ሲል ገልጿል።

አክሎም በርካታ የድርጅቱ ሰራተኞች በእርሱ ላይ መቆጣታቸውን እንደሚረዳ እና እርሱም አሁን ለገቡበት ሁኔታ ተጠያቂነቱን እንደሚወስድ ተናግሯል።

‘’የድርጅቱን መጠን ያለልክ በፍጥነት አሳድጌዋለሁ። ለዚህም ይቅርታ እጠይቃለሁ’’ ሲል በመግለጫው ላይ አስፍሯል።

‘’ትዊተር ውስጥ ለነበሩ ሁሉም ሰራተኞች ምስጋናዬን አቀርባለሁ’’ ያለው ዶርሲ አክለሎም ‘’ምንም እንኳን በዚህ ወቅትም ይሁን ለዘለአለሙ የእነሱ ምላሽ ሌላ ሊሆን እንደሚችል ብረዳም እኔ ግን እወዳቸዋለሁ’’ ሲልም ተናግሯል።

ጃክ ሶርሲ በዚሁ መግለጫው ላይ የኤለን መስክን ውሳኔ በመደገፍ ጽፏል። እንዲሁም መስክ ትዊተርን መግዛቱን ሲደግፍም ነበር። ከወራት በፊትም መስክ ትዊተርን የመግዛት እርምጃውን ሲጀምር ጃክ ዶርሲ ‘’እኔ የማምነው ብቸኛው መፍትሄ እሱ ነው’’ ሲልም ተናግሮ ነበር። እንዲሁም ‘’በሙሉ ልቤ የማምነው ትክክለኛው መንገድ ይህ ነው’’ ሲልም ድጋፉን ቸሯል።

ጃክ ዶርሲ ከሌሎች አጋሮቹ ጋር በመሆን እኤአ በ2006 ነበር ትዊተርን የመሰረተው።

ቅነሳው እስከ 7500 የትዊተር ሰራተኞችን ሊነካ ይችላል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ተቋሙ የሚያደርገውን የይዘት ክትትል ስራም ጫና ውስጥ ይከታል ተብሎ ይታመናል።

ቅነሳው የተቋሙን ፖሊሲዎች ግን በጭራሽ የማይነካ ነው ሲል መስክ ተናግሯል።

የትልልቅ ኩባንያ ማስታወቂያ ስራዎችን የሚሰሩ ተቋማት በቅርቡበትዊተር ላይ ማስታወቂያ ማስነገራቸውን አቁመዋል። ከእነዚህም መካከል ቮልስ ዋገን፣ ጀነራል ሞተርስ እና ፋይዘር ይገኙበታል።

በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚያስችል ሁኔታ የትዊተር ገቢ የሚመጣው ከማስታወቂያ ነው። ታዲያ ቢሊየነሩ መስክ ይህንን ለማስቀረት እና ከትዊተር በተለያዩ ዘዴዎች ገንዘብ ለመስራት አቅዷል።

ከእነዚህም መካከል አንዱ የማንነት ማረጋገጫ የሆነውን ሰማያዊ የራይት ምልክት ለማግኘት በየወሩ ስምንት ዶላር ገደማ ክፍያን መሰብሰብ ይገኝበታል።