ኤሎን መስክ ለትዊተር ሰማያዊ ምልክት በወር ስምንት ዶላር እንደሚያስከፍል ተናገረ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኤሎን መስክ የተረጋገጠ የትዊተር አካውንት (ገጽ) መሆኑን የሚያመለክተውን ሰማያዊ ምልክት በስማቸው ለሚፈልጉ የትዊተር ተጠቃሚዎች ወርሃዊ ስምንት ዶላር እንደሚያስከፍል ተናገረ።
በ44 ቢሊዮን ዶላር ክፍያ የማህበራዊ ድረ-ገጹን ትዊተርን የገዛው ኤሎን መስክ ይህንን የወሰነው “የማያስፈልጉ መረጃዎችንና ማጭበርበሮችን ለመቆጣጠር ነው” ብሏል።
በትዊተር አካውንት ከተጠቃሚዎች ስም ቀጥሎ ያለው ሰማያዊ ምልክት በዋነኝነት ታዋቂ የሆኑ ሰዎች ገጻቸውን ለማረጋገጥ የሚጠቀሙበት ሲሆን ክፍያም የለውም።
ይህ እርምጃ አስተማማኝ ምንጮችን ለመለየት ፈታኝ እንደሚያደርገው ተቺዎች ተናግረዋል።
የዓለማችን ባለጸጋ የሆነው ኤሎን መስክ አክሎ እንደተናገረው የሚከፍሉ ተጠቃሚዎች ምላሽ ለማግኘት፣ ለፍለጋዎች ቅድሚያ እንደሚሰጣቸውና ከሌሎች በተለየ መልኩ ግማሽ ማስታወቂያ ብቻ በገፃቸው ላይ እንደሚደርስ ተናግሯል።
“ስልጣን ለህዝቡ! ለሰማያዊ ስምንት ዶላር በወር!” በማለት ቢሊዮነሩ በትዊተር ገጹ ላይ አስፍሮ “የጌቶችና የጭሰኞች” ስርዓት በማለት የቀድሞውን የሰማያዊ ምልክት (ብሉ ቲክ) የማረጋገጫ ዘዴን ተችቷል።
ከዚህ ቀደም ተጠቃሚዎች ብሉ ቲክ እንዲኖራቸው ለማድረግ አጠር ያለ የኦንላይን ማመልከቻ ቅጽን መሙላት አለባቸው።
ብዙዎቹም ማንነታቸውን በማስመሰል ኢላማ ለሆኑ ታዋቂ ሰዎች ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች የታሰበ ነበር።
ትዊተር ይህንን ያስተዋወቀው በአውሮፓውያኑ 2009 ነበር።
ለዚህም መነሻ የሆነው ኩባንያው ታዋቂ ሰዎችን በማስመሰል የሚያጭበረብሩ አካላትን ለመከላከል በቂ ጥራት አላደረገም በሚል ክስ መቅረቡን ተከትሎ ነው።
ኤሎን መስክ ለዓመታት ትርፍ ያላስገኘውን የትዊተርን የቢዝነስ አሰራር ለማደስ እየሰራ ባለበት ወቅት ከባድ ፈተና ገጥሞታል።
ትዊተር በማስታወቂያ ላይ ያለውን ጥገኝነት መቀነስ እንደሚፈልግም ተናግሯል።
ከወዲሁ አንዳንድ ኩባንያዎች በእርሳቸው አመራር በትዊተር ገጽ ላይ የማስተዋወቁ ጉዳይ እንዳሳሰባቸው እየገለጹ ነው።
የመስክ የኤሌክትሪክ መኪና ኩባንያ ቴስላ ተቀናቃኝ የሆነው ጄኔራል ሞተርስ ባለፈው ሳምንት በትዊተር ላይ የሚያደርገውን ማስታወቂያዎችን ማቆሙን ተናግሯል ።












