ትዊተር በቀን ከ4 ሚሊዮን ዶላር በላይ እየከሰርኩ ነው በማለት ሠራተኞችን እየቀነሰ ነው

ኤሎን መስክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኤሎን መስክ

አዲሱ የትዊተር ባለቤት ኤሎን መስክ ትዊተር በየቀኑ ከ4 ሚሊዮን ዶላር በላይ እየከሰረ ስለሆነ የድርጅቱን ሠራተኞች በግማሽ ለመቀነስ መገደዱን ገለጸ።

መስክ ትዊተርን ከገዛ በኋላ ለውጦችን ለማድረግ የተነሳ ሲሆን የሠራተኞች ቅነሳም ከሚደረጉት ለውጦች ውስጥ አንዱ ነው።

የትዊተር ከፍተኛ ኃላፊዎች ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነው ዮኤል ሮዝ በትዊተር ገጹ ላይ እንዳሰፈረው ትዊተር ካሉት ሠራተኞች “50 በመቶ የሚሆኑት ይቀነሳሉ” ብሏል።

ምንም እንኳን ትዊተር ሠራተኞቹን የሚቀንስ ቢሆንም፣ በመድረኩ ላይ የሚወጡ ይዘቶችን በመቆጣጠር በኩል የሚከናወነው ሥራ “ፈጽሞ አይቀየርም” ብሏል ባለሃብቱ መስክ።

የዓለማችን ቁጥር አንድ ቱጃር የሆነው ኤሎን መስክ ግዙፉን የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ የሆነውን ትዊተርን 44 ቢሊዮን ዶላር በመክፈል ነው በቁጥጥሩ ሥር ያስገባው።

ቢሊየነሩ የትዊተር ባለቤት በድርጅቱ ላይ በሚያካሂደው ለውጥ ከሥራቸው ለሚቀነሱ ሠራተኞች የሦስት ወር የመሰናበቻ ክፍያ እንደሚሰጣቸውና “ይህም ሕጉ ከሚያዘው 50 በመቶ የበለጠ ነው” ሲል በትዊተር ገጹ ላይ አስፍሯል።

ከትናንት አርብ ጀምሮ በዓለም ዙሪያ ለትዊተር የሚሰሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከሥራቸው እየተሰናበቱ መሆናቸው እየተነገረ ነው።

ይህም በማኅበራዊ ገጹ ላይ ሊወጡ የሚችሉ ጉዳትን የሚያስከትሉ ይዘቶችን በመቆጣጠር በኩል ክፈተት ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የበይነ መረብ ደኅንነት ቡድኖች እንደሚሉት ኤሎን መስክ በትዊተር ላይ ያለውን ይዘቶችን የመቆጣጠር ፖሊሲን ሊያላላ እና የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን የመሳሰሉ ከዚህ ቀደም በቋሚነት ከትዊተር የታገዱ ግለሰቦችን ከዕገዳ ነጻ ሊያወጣ የሚችል ውሳኔ ሊሰጥ ይችላል።

ነገር ግን ይህ የሠራተኞች ቅነሳ የትዊተር ይዘት ቁጥጥር ባለሙያዎችን ብዙም የማይጎዳ መሆኑን በመግለጽ፣ የቁጥጥር ሥራው ባለበት እንደሚቀጥል ሮዝ ገልጿል።

በተጨማሪም በሚቀጥለው ሳምንት በአሜሪካ የሚካሄደውና የፕሬዝዳንት ባይደን የሁለት ዓመት የሥልጣን ቆይታ የሚፈተሽበት የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ወቅት የተሳሳተ መረጃ ስርጭትን መቆጣጠር በትዊተር “ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው” ብሏል።

በአሜሪካ በተለያዩ ግዛቶች ውስጥ ለትዊተር የሚሰሩ ሠራተኞች የስንብት ደብዳቤ እየደረሳቸው ሲሆን፣ በደብዳቤው ላይ “ድርጅቱን በስኬት ወደፊት ለማራመድ ሠራተኛ ቅነሳ ውሳኔው አስፈላጊ” መሆኑን ይገልጻል።

የትዊተር ሠራተኞች ድርጅቱ የአሜሪካንን እና የካሊፎርኒያን ግዛት ሕግ በሚጥስ ሁኔታ የሁለት ወራት የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ ከፍተኛ የሠራተኞች ቅነሳ ማድረጉን በመቃወም በፍርድ ቤት ክስ መስርተዋል።

በትዊተር ላይ ማስታወቂያዎችን ለማውጣት ከፍተኛ ገንዘብ የሚከፍሉ ግዙፍ ተቋማት መስክ የማኅበራዊ ሚዲያውን ከገዛው በኋላ ግንኙነታቸውን ለጊዜው እያቋረጡ መሆናቸው ተገልጿል።

ከእነዚህም የመኪና አምራቾቹ ቮልስዋገን፣ ጄነራል ሞተርስ፣ አውዲ እንዲሁም የመድኃኒት አምራቹ ፋይዘር እና ምግብ አምራቹ ጀነራል ሚልስ ይጠቀሳሉ።

በዚህም ሳቢያ መስክ የትዊተርን ወጪ በመቀነስ ገቢውን ለማሳደግ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው። ከእነዚህም መካከል የተረጋገጠ ገጽ ያላቸው ተጠቃሚዎች በወር ስምንት ዶላር እንዲከፍሉ የማድረግ አሰራርን እንደሚጀምር ተገልጿል።