ኤሎን መስክ በትዊተር የይዘት ቁጥጥር ፖሊሲ ላይ ለውጥ አይደረግም አሉ

ኤሎን መስክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቅርቡ የትዊተርን ግዢ በ44 ቢሊዮን ዶላር ፈጽመው የማኅበራዊ ትስስር ገጹን የተረከቡት ቢሊየነሩ ኤሎን መስክ አሁን ላይ በትዊተር የይዘት ቁጥጥር ላይ ለውጥ እንደማይደረግ ተናገሩ።

መስክ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ “ፍጹም ግልጽ ለመሆን እስካሁን በትዊተር የይዘት ቁጥጥር ፖሊስ ላይ ያደረግነው ለውጥ የለም” ብለዋል።

ባለሃብቱ ይህንን ከማለታቸው ቀደም ብለው በትዊተር የሚጋሩ ይዘቶችን የሚቆጣጠር አዲስ ምክር ቤት መቋቋሙን ይፋ አድርገው ነበር።

መስክ በሌላ የትዊተር መልዕክታቸው ደግሞ “በጥቃቅን ወይም አሻሚ በሆነ ምክንያት ከትዊተር የታገደ ማንኛውም ሰው ከትዊተር እስር ቤት ነጻ ወጥቷል” ብለዋል።

ጨምረውም “ኮሜዲ አሁን በትዊተር ሕጋዊ ሆኗል” ሲሉ አስፍረዋል።

ረጅም ጊዜ የፈጀው የትዊተር ግዢ አልቆ መስክ የማኅበራዊ ትስስር ገጹን ከተረከቡ በኋላ ረጅም ጊዜ ያገለገሉ ባለሙያዎች ትዊተርን ለቀው እየወጡ ነው።

የመስክ የትዊተር ዕቅድ ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን በተመለከተ በርካቶች ጥያቄ እያነሱ ነው።

በባለሃብቱ ሊደረጉ የሚችሉ ለውጦች ተቆጣጣሪዎች እና የትዊተር ተጠቃሚዎችን በተለያየ ጎራ አሰልፏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አንዳንዶቹ ቢሊየነሩ የጥላቻ እና የሐሰት ንግግሮችን የሚመለከቱ ደንቦችን ሊያስቀሩ ይችላሉ የሚል ስጋት ያላቸው ሲሆን ሌሎች ደግሞ የቀደመው የትዊተር አስተዳደር ጥሎት የነበረውን እና የመናገር ነጻነትን የሚገድቡ ሕጎችን ሊያስቀር ይችላል የሚል ተስፋ አላቸው።

ኤሎን መስክ ትዊተር “የተለያዩ አመለካከት ያላቸውን በስፋት የሚያካትት” ምክር ቤት ይኖረዋል ብለዋል።

ከትዊተር ታግዶ የነበረው ዕውቁ አሜሪካዊ ካንዬ ዌስት ዕገዳው መነሳቱን ያረጋገጡት ባለሃብቱ “ምክር ቤቱ እስከሚሰበሰብ ድረስ ይዘትን የተመለከተ መሠረታዊ ለውጥ አይደረግም። የታገዱ አካውንቶችም አይመለሱም” ብለዋል።

ዬ በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀው የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኙ ካንዬ ዌስት አይሁድ ጠል አስተያየት ሰጥቷል በሚል ነበር ከማኅበራዊ መድረኩ የታገደው።

የመስክ ትዊተርን መረከብን ተከትሎ ኩባንያውን ለቀው ከወጡ ከፍተኛ አመራሮች መካከል የፋይናንስ ኃላፊው ኔድ ሴጋል እና የቦርድ ሊቀመንበሩ ብሬት ታይለር ይገኙበታል።

የመስክ የትችት ዋነኛ ኢላማ የነበሩት የትዊተር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፓራግ አግራዋል ከተባረሩት መካከል ቢሆኑም የትዊተር አካውንታቸው ላይ እስካሁን የገጹ ሥራ አስፈጻሚ መሆናቸው የሚጠቅሰው ጽሑፍ አልተነሳም።

የኤሎን መስክ ቴስላ መኪና አምራች ኩባንያ ተቀናቃኝ የሆነው እና በአሜሪካ ትልቁ መኪና አምራች ጄነራል ሞተርስ፣ ትዊተር ላይ የሚያስነግረውን ማስታወቂያ ለጊዜው አግዷል።

ኩባንያው በአዲሱ የማኅበራዊ መድረክ ባለቤት ሥር ትዊተር የሚኖረውን አቅጣጫ እየቃኘ እንደሚገኝ ጠቁሟል።

ባለፈው ሐሙስ ትዊተር ላይ የሚነገሩ ማስታወቂያዎችን በተመለከተ መስክ ባሰፈሩት ጽሑፍ ትዊተር ችግር ላለባቸው ምርቶች ሁሉ ክፍት እንዲሆን እንደማይፈልጉ ተናግረዋል።

ቢሊየነሩ መስክ በትዊተር መጠነ ሰፊ ለውጥ እንደሚፈልጉ የተናገሩ ሲሆን የመናገር ነጻነት የሚከበርበት እና ሕዝባዊ የክርክር መድረክ እንዲሆንም ይሻሉ። በተጨማሪም እንደ ዶናልድ ትራምፕ ያሉ አወዛጋቢ እና ከትዊተር የታገዱ ሰዎችም እንዲመለሱ ፍቃደኛ ነኝ ብለዋል።

የቀደሞው የኩባንያው የፋይናንስ ኃላፊ በትዊተር መልካም ጊዜ እንደነበራቸው ገልጸው፣ያለፉት ስድስት ወራት በትዊተር ግዢ የነበሩት መጠራጠሮች ጫና እንደፈጠሩባቸው ተናግረዋል።

የኤሎን መስክ የትዊተር ግዢ ረጅም መንገድ የተጓዘ ነው።

ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር መስክ ትዊተርን ለመግዛት ያቀረቡት 44 ቢሊዮን ዶላር ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል።ይህም ጥያቄያቸው በትዊተር ወዲያውኑ ነበር ተቀባይነትን ያገኘው።

በወቅቱ ቢሊየነሩ ትዊተርን መግዛት የፈለጉበትን ምክንያት ሲያስረዱ “ሥልጣኔ የጋራ የሆነ ዲጂታል አደባባይ” ይፈልጋል ብለው ሐሰተኛ አካውንቶችን በማስወገድ ማኅበራዊ መድረኩ የመናገር ነጻነት ማዕከል ይሆናል ሲሉ ቃል ገብተዋል።

ሆኖም ከጥቂት ወራት በኋላ በትዊተር ያለው ሐሰተኛ አካውንት ብዛት ኩባንያው ከተናገረው ከፍ ያለ ነው በሚል ማኅበራዊ መድረኩን የመግዛት ሃሳባቸውን መሰረዛቸውን ተናግረው ነበር።

ይህንንም ተከትሎ መስክ ባቀረቡት ዋጋ ምክንያት ሃሳባቸውን እንደቀየሩ የሚያምኑት የትዊተር የሥራ ኃላፊዎች ጉዳዩን ወደ ሕግ ወስደውታል።

ከአወዛጋቢው ሂደት በኋላ ባለፈው ሐሙስ ባለቤትነቱ የመስክ የሆነ ድርጅት ለእያንዳንዱ የትዊተር ባለድርሻ 54 ሚሊዮን ዶላር በመክፍል ግዢውን ፈጽሟል።