ኤሎን መስክ የዶናልድ ትራምፕን የትዊተር አካውንት ሊመልስ እንደሚችል ጠቆመ

ኤሎን መስክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዓለማችን ሃብታሙ ግለሰብ ኤሎን መስክ ትዊተርን ለመግዛት ያቀረበው ጥያቄ ከተሳካ የዶናልድ ትራምፕ የትዊተር አካውንት ላይ የጣለውን እገዳ እንደሚቀለብስ ተናገረ።

ኤሎን ባለፈው ወር ከትዊተር ቦርድ ጋር 44 ቢሊዮን ዶላር በመክፈል ማሕበራዊ ሚዲያውን ለመግዛት ስምምነት ላይ የደረሰ ሲሆን በሚቀጥሉት ሁለት ወይም ሶስት ወራት ውስጥ ሙሉ ሂደቱ እንደሚጠናቀቅ ይፋ ሆኗል።

ትዊተር የቀድሞውን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በቋሚነት ለማገድ የወሰደው ውሳኔ "ከሞራል አንጻር የተሳሳተ እና አይን ያወጣ ድድብና ነው" ሲል መስክ ፋይናሻል ታይምስ በመኪኖች ላይ በሚያዘጋጀው ጉባኤ ላይ ተናግሯል።

እ.ኤ.አ. በጥር 2021 ትዊተር የዶናልድ ትራምፕ የትዊተር አካውንት በይፋ ያገደው የካፒቶሉን ማዕበል ተከትሎ "ለተጨማሪ ሁከት መቀስቀስ ስጋት ስለሚፈጥር" በሚል ነበር።

ነገር ግን የቴስላ ባለቤት መስክ "ቋሚውን እገዳ አነሳለሁ። ነገርግን እስካሁን የትዊተር ባለቤትነት ስለሌለኝ እርግጠኛ ሆኜ መናገር አልችልም'' ሲልም ተናግሯል።

እገዳው ዶናልድ ትራምፕን ዝም ከማሰኘት ይልቅ የራሳቸውን ማህበራዊ ድረ-ገጽ እንዲገነቡ በማድረግ በቀኝ አክራሪዎች ዘንድ ድምጻቸውን የበለጠ ከፍ አድርጎታልም ሲል መስክ ተናግሯል።

መስክ አክሎም ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ቀደም አካውንታቸው ወደነበረበት ቢመለስም ወደ ትዊተር የመመለስ ፍላጎት እንደሌላቸው መናገራቸውን ጠቁሟል።

የትዊተር ኩባንያ በሳን ፍራንሲስኮ የቴክኖሎጂ ማህበረሰብ ውስጥ የተጠነሰሰ በመሆኑ ምክንያት ወደ ግራ ዘመሞች የሚያደላ ጠንካራ አቋም አለው ሲሉም ቢሊየነሩ ወንጅለዋል።

"ድል ማለት የቀኝ አክራሪዎች 10% እና የግራ አክራሪዎች 10% እኩል ከተበሳጩ ነው" ሲልም አክሏል።

ባለፈው ሳምንት የመብት ተሟጋቾች ለትዊተር በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ በኤሎን መስክ አስተዳደር ስር "ትዊተር የተሳሳተ መረጃ የመሰብሰቢያ ገንዳ ሊሆን ይችላል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በዩናይትድ ስቴትስ የዋይት ሀውስ ፕሬስ ፀሐፊ ጄን ፒሳኪ የባደን አስተዳደር የበይነ መረብ መገናኛ ዘዴዎች የንግግር ነፃነትን ያስጠበቁ እንዲሆን ይፈልጋል ብለዋል።

ፒሳኪ ዶናልድ ትራምፕን ወደ ትዊተር እንዲመለሱ መፍቀድ ወይም አለመፍቀድ የኩባንያው ውሳኔ ነውም ብለዋል።