በታንዛኒያ ተቃውሞ የተፈጸሙ ግድያዎች እንደሚመረመሩ ፕሬዝዳንቷ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሐሰን ምርጫውን ተከትሎ የተነሳው ተቃውሞ እና የተፈጸሙ ግድያዎች ላይ ይፋዊ ምርመራ እንደሚካሄድ አስታወቁ።
መንግሥት ተቃዋሚዎች ላይ የኃይል እርምጃ ወስዷል የሚሉ ክሶች መበራከታቸውን ተከትሎ ፕሬዝዳንቷ ምርመራ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
ሳሚያ በ98% ድምጽ ምርጫውን አሸንፈው በፕሬዝዳንትነት ቀጥለዋል። በምርጫው ማግሥት ከተነሳው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ቢያንስ 240 ሰዎች በአገር ክህደት ተከሰዋል።
ዐቃቤ ሕግ ከተቃውሞ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር ለዋሉ ሰዎች "ርሕራሔ እንዲያሳይ" ፕሬዝዳንቷ ጠይቀዋል።
"የሚያደርጉትን አያውቁምና፤ አባት ሆይ ይቅር በላቸው" በማለት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል አጣቅሰዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ቱክ፤ ከተቃውሞ ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ ግድያዎች እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በግልጽ እንዲመረመሩ አሳስበዋል።
ፕሬዝዳንት ሳሚያ ምርመራ እንደሚደረግ የገለጹት ከኮሚሽነሩ ማሳሰቢያ በኋላ ነው።
ከምርጫው ጋር በተያያዘ በተነሳው ተቃውሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሞቱ ተቃዋሚዎች ገልጸዋል። መንግሥት የሟቾችን ቁጥር ገና ይፋ አላደረገም።
ላለፉት ስድስት አሥርት ዓመታት የተረጋጋች በነበረችው ታንዛኒያ የተነሳው ተቃውሞ በርካቶችን አስደንግጧል።
ፕሬዝዳንቷ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ ድርጊታቸው ምን እንደሚያመጣ ባለመገንዘብ ተቃውሞውን የተቀላቀሉ ሰዎች ላይ ዐቃቤ ሕግ እንዳይጨክን ተማጽነዋል።
"ብዙ ወጣቶች ታስረው በአገር ክህደት ተከስሰዋል። ምን እያደረጉ እንደነበር አላወቁም። እናት እንዲሁም የዚህ አገር ጠባቂ እንደመሆኔ ርሕራሔ እንድታሳዩዋቸው እጠይቃለሁ" ብለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች አገሪቱን ሳይጎዱ እንዴት በፖለቲካ መሳተፍ እንዳለባቸው እንዲመካከሩም ጥሪ አቅርበዋል።
አዲስ ሕገ መንግሥት ለማርቀቅ ሒደት እንደሚጀመርም ፕሬዝዳንቷ ቃል ገብተዋል።
በወጣቶች የተመራው ተቃውሞ ዜጎች በአገሪቱ አስተዳደር መማረራቸውን በአደባባይ አሳይቷል።
በታንዛኒያ የተጠበቀው ለውጥ ባለመምጣቱ እና የወጣቶች ቁጣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመምጣቱ ምክንያት ተቃውሞው መቀጣጠሉን ተንታኞች ገልጸዋል።
የአገሪቱ መንግሥት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ላይ እያደረሰ ያለው አፈና እና እንግልትም በርካቶችን አስቆጥቷል።
ምርጫው እየተቃረበ ሲሄድ ገዢው ፓርቲ ሲሲኤም በስልታዊ መንገድ ተቃዋሚዎችን ከምርጫ ፉክክር ውጭ አድርጓል።
የፕሬዝዳንት ሳሚያ የማሸነፍ ዕድል እንዲሰፋ የታንዛኒያ ዋነኛ ተቃዋሚ ሲታሰሩ ሌላኛው ተቃዋሚ ከምርጫው ታግደዋል።
ምርጫው የተካሄደው ዋነኛው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ቱንዱ ሊሱ ታስረው በአገር ክህደት ከተከሰሱ በኋላ ሲሆን፣ ፖለቲከኛው ግን ክሱን አስተባብለዋል።
ፕሬዝዳንት ሳሚያ በአውሮፓውያኑ 2021 የመጀመሪያዋ ሴት የአገሪቱ መሪ ሆነው ሲሾሙ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እንደሚያመጡ ተስፋ ተጥሎባቸው ነበር።
ሥልጣን የያዙ ሰሞን ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን በመጋበዝ አሳታፊነትን ለማረጋገጥ ሞክረዋል። ሆኖም ግን ሳሚያ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተቃዋሚዎች ላይ የሚያደርሱት ጫና እየበረታ መጥቷል።
ታንዛኒያ ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣች ወዲህ ገዢው ፓርቲ ሲሲኤም የአገሪቱን ፖለቲካ እና መንበረ ሥልጣን ተቆናጦ ቆይቷል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣው ሪፖርት፤ የዘፈቀደ ዕገታ፣ ስወራ፣ ስቅይት እና ግድያ መፈጸሙን ያሳያል።















