በታንዛኒያ የተደረገውን አገራዊ ምርጫ ተከትሎ ሁከት እና ብጥብጥ ተስፋፍቷል

በታንዛኒያ ምርጫ በተካሄደበት ዕለት በዋና ከተማዋ ተቃዋሚዎች እና ፖሊስ ተጋጭተዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በታንዛኒያ ምርጫ በተካሄደበት ዕለት በዋና ከተማዋ ተቃዋሚዎች እና ፖሊስ ተጋጭተዋል

በታንዛኒያ በሚገኙ ትላልቅ ከተሞች የተቃዋሚ ደጋፊዎች ረቡዕ ዕለት የተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ እና የፓርላማ ምርጫን በመቃወም አደባባይ ወጥተዋል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች ወደ ኬንያ ግዛት ተሻግረው መንገዶችን በመዝጋት፣ ጎማ በማቃጠል በመንገድ ላይ ያገኟቸውን የፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን ፖስተሮችን በመቀዳደድ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

የኬንያ ፖሊስ ከታንዛኒያ ፖሊስ ሲሸሹ የነበሩ ሁለት ሰዎች መሞታቸውን አስታውቋል።

የዋናው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ በእስር ላይ በመሆናቸው እና ሌላኛው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ከምርጫው እንዲሰረዙ በመደረጉ መንግሥት ፕሬዚዳንት ሳሚያ የማሸነፍ ዕድላቸውን እንዲሰፋ ሲል ዲሞክራሲን ዝቅ እያደረገ ነው በማለት ተቃዋሚዎች ይከስሳሉ።

ሐሙስ ዕለት የምርጫ ኮሚሽኑ ውጤቱን ይፋ ማድረግ ከጀመረ በኋላ የተቃዋሚዎች ቁጣ የጨመረ ሲሆን ሳሚያ በደቡብ ምዕራብ ምቤአ ግዛት 95 በመቶ የሚሆነውን ድምጽ አግኝተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዚዳንቷ በታንዛኒያ እና በዛንዚባር በሚገኙ በርካታ የምርጫ ክልሎች አብላጫውን ድምጽ በማግኘት እየመሩ ነው።

የአውሮፓ ኅብረት ሕግ አውጪዎች ምርጫውን "ለወራት ሲካሄድ የቆየ ማጭበርበር" ሲሉ ጠርተውታል።

የምርጫው ቀን በተቃዋሚ ደጋፊዎች እና በፖሊስ መካከል ግጭት ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከምርጫው አንድ ቀን በኋላ የታንዛኒያ ወታደራዊ አዛዥ ጄኔራል ጃኮብ ማኩንዳ በምርጫው ወቅት ለ"ንብረት እና ሰው ሕይወት መጥፋት"፤ ለታንዛኒያ "ክፉ የሚመኙ ያልተገባ ባህሪያት" አሏቸው ያሏቸውን ግለሰቦች ተጠያቂ አድርገዋል።

በሰሜናዊቷ ምዋንዛ ከተማ የተኩስ ድምፅ የተሰማ ሲሆን በዶዶማ እና በዋና ከተማዋ ዳሬሰላም ግጭት ተቀስቅሶ ዋና ዋና መንገዶች ተዘግተዋል።

ኬንያ ዜጎቿ በናማንጋ የድንበር ከተማ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ እንዳይሳተፉ አስጠንቅቃለች።

የታንዛኒያ ፖሊስ ቀኑን ሙሉ ከፖሊስ ጋር ሲጋጩ የነበሩትን ተቃዋሚዎች ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ተኩሷል።

በታንዛኒያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ወደ ዳሬሰላም ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሚወስደው መንገድ ሐሙስ ዕለት ተዘግቶ ከቆዩት በርካታ ዋና መንገዶች መካከል አንዱ መሆኑን አስታውቋል።

አንድ የዓይን እማኝ ለቢቢሲ በቪክቶሪያ ሐይቅ ዳርቻ ላይ በምትገኘው እና ከዳሬሰላም ቀጥሎ ከፍተኛውን የሕዝብ ቁጥር የያዘችው ምዋንዛ ከተማ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች አደባባይ ወጥተው ማየታቸውን ተናግሯል።

"ከ10 ደቂቃ በኋላ የተኩስ ድምጽ እና የአስለቃሽ ጭስ ፍንዳታ መስማት ጀመርን" ብሏል።

"አንዳንድ የተጎዱ ሰዎች ወደ እኛ መንገድ ሲወሰዱ ተመልክተናል" ሲል አክሏል።

መንግሥት ውጥረቱ እየተባባሰ በመምጣቱ ሠራተኞች ከቤታቸው እስከ አርብ ድረስ እንዲሰሩ መወሰኑን ይፋ አድርጓል።

የመብት ተሟጋች የሆነው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ረቡዕ በተፈጠረ ግጭት አንድ ሰላማዊ ዜጋ እና አንድ የፖሊስ አባል መገደላቸውን የሚገልጸው ዘገባ "እጅግ አሳሳቢ ነው" ብሏል።

በዳሬሰላም የምሽት ሰዓት እላፊ የተጣለ ሲሆን፣ ምንጮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት በከተማው የሚገኘው ሙሂምቢሊ ሆስፒታል በቆሰሉ ሰዎች ተሞልቶ ታይቷል።

የኢንተርኔት ግንኙነት በመላ አገሪቱ የተቋረጠ ሲሆን አምነስቲ ሁኔታውን የበለጠ ሊያቀጣጥል ይችላል ሲል አስጠንቅቋል።

ፕሬዚደንት ሳሚያ የተቃዋሚ ፓርቲ እጩዎች ከምርጫ ከተገለሉ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ አገሪቱን ለማስተዳደር የሚያስችላቸውን ድምጽ ያገኛሉ ተብሎ ተገምቷል።

ሳሚያ እአአ በ2021 ወደ ሥልጣን የመጡት የፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ ሞትን ተከትሎ ነው።