የታንዛኒያን ምርጫ ተከትሎ በተነሳው ተቃውሞ ምክንያት የሰዓት እላፊ ታወጀ

በፖሊስ እና በሰላማዊ ሰልፈኞች መካከል የተነሳውን ግጭት ተከትሎ የሰዓት ዕላፊ ታውጇል።
የምስሉ መግለጫ, በፖሊስ እና በሰላማዊ ሰልፈኞች መካከል የተነሳውን ግጭት ተከትሎ የሰዓት ዕላፊ ታውጇል።

በታንዛኒያ ዋና ከተማ ዳሬ ሰላም በፖሊስ እና በሰላማዊ ሰልፈኞች መካከል የተነሳውን ግጭት ተከትሎ የሰዓት እላፊ ገደብ ታወጀ።

ረቡዕ የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ በተነሳው ግጭት ምክንያት ተጎድተው ሆስፒታል የገቡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን በሙሂምቢሊ ሆስፒታል ያሉ የቢቢሲ ምንጮች ገልጸዋል።

ምርጫውን ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉህ እንደሚያሸንፉ ይጠበቃል። ምርጫው የተካሄደው ዋነኛው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ታስረው በአገር ክህደት ከተከሰሱ በኋላ ሲሆን፣ ፖለቲከኛው ግን ክሱን አስተባብለዋል።

ተቃዋሚዎች ነጻ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዲቻል ሲጠይቁ ቆይተዋል። ረቡዕ [ትናንት] በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍም ይሄው ጥያቄ ተስተጋብቷል።

በተቃውሞው ተሽከርካሪዎች ሲቃጠሉ አውራ ጎዳናዎች ላይም ጉዳት ደርሷል።

የታንዛኒያ ፖሊስ ኃላፊ ካሜሊየስ ዋምቡራ፤ የሰዓት እላፊውን ይፋ ካደረጉ በኋላ ነዋሪዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ አሳስበዋል። የሰዓት ዕላፊው መቼ እንደሚነሳ አልገለጹም።

የዳሬ ሰላም ቀጣናዊ አስተዳዳሪ አልፍሬድ ቻላሚላ፤ የከተማውን ሰላም የሚያውኩ ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠንቅቀዋል።

ተቃውሞው ዛሬ ሐሙስም በመቀጠሉ ምክንያት መንግሥት ሠራተኞች ከቤታቸው ሆነው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ አዝዟል።

ምርጫውን ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉህ እንደሚያሸንፉ ይጠበቃል።
የምስሉ መግለጫ, ምርጫውን ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉህ እንደሚያሸንፉ ይጠበቃል።

በደቡብ ምዕራባዊቷ ምቤያ ከተማ እና ድንበር ላይ ባለችው ቱንዳማ ከተማም ተቃውሞዎች ተካሂደዋል።

በሰላማዊ ሰልፉ የተገኘ አንድ ግለሰብ "ታክቶናል፤ ገለልተኛ ምርጫ ተከናውኖ ታንዛኒያውያን መሪያችንን መምረጥ ነው የምንፈልገው" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ተቃውሞውን ተከትሎ በአገሪቱ ኢንተርኔት መቋረጡ ተገልጿል። የደኅንነት ስጋት በመኖሩ በዳሬ ሰላም የድምጽ ሰጪዎች ቁጥር ውስን እንደሆነም ተዘግቧል።

የፖሊስ ቃል አቀባይ የፀጥታ ችግር የለም ብለው ለሕዝቡ ማስተማመኛ ለመስጠት ሞክረዋል።

ከፕሬዝዳንት ሳሚያ ጋር እንዲፎካከሩ የተፈቀዳላቸው እምብዛም ዕውቅና የሌላቸው ስድስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ብቻ ናቸው።

ከታሰሩት ዋነኛ ተቃዋሚ በተጨማሪ የፕሬዝዳንቷ ግንባር ቀደም ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብሎ የነበረው ሉሀጋ ማፒና "ከሕጋዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘ" ከውድድሩ ውጪ ተደርገዋል።

ታንዛኒያ ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣች ወዲህ ገዢው ፓርቲ ሲሲኤም የአገሪቱን ፖለቲካ እና መንበረ ሥልጣን ተቆናጦ ቆይቷል።

ከምርጫው አስቀድሞ የመብት ተሟጋቾች እየተባባሰ የመጣውን የመንግሥት አፈና ኮንነዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው ሪፖርት፤ የዘፈቀደ ዕገታ፣ ስወራ፣ ስቅይት እና ግድያ እየተፈጸመ መሆኑን ያሳያል።

መንግሥት ክሱን አስተባብሎ ምርጫው ነጻ እና ገለልተኛ መሆኑን አስታውቋል።

ፕሬዝዳንት ሳሚያ በአውሮፓውያኑ 2021 የመጀመሪያዋ ሴት የአገሪቱ መሪ ሆነው ሲሾሙ ዴሚክራሲያዊ ለውጥ ያመጣሉ ተስፋ ተጥሎባቸው ነበር።

ከጆን ማጉፉሊ ሞት በኋላ ሥልጣኑን የተረከቡት ሳሚያ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተቃዋሚዎች ላይ የሚያደርሱት ጫና እየበረታ መጥቷል።

የምርጫው ውጤት ከቀናት በኋላ ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።