የታንዛኒያዋን ፕሬዚዳንት ፎቶ ያቃጠለው አርቲስት እስር ተፈረደበት

ፕሬዚዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሃሰን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የታኒዛንያን ፕሬዚዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሐሰንን ፎቶ አቃጥሏል የተባለው አርቲስት ሁለት ዓመት እስር ወይም የሁለት ሺህ ዶላር ቅጣት እንዲከፍል ተበየነበት።

አርቲስቱ በአገሪቱ የሳይበር (የመረጃ መረብ) ወንጀሎች ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ነው ይህ ብይን የተላለፈበት።

ሻድራክ ቻውላ ፕሬዚዳንቷን እየተሳደበ የፕሬዚዳንቷን ምስል ሲያቃጥል የሚያሳይ ቪዲዮ ቀርጿል በሚል ክስ ነበር በቁጥጥር የዋለው።

የ24 ዓመቱ ሠዓሊ ወንጀሉን መፈጸሙን አምኖ ድርጊቱንም በችሎቱ ሂደት ወቅት መከላከል አልቻለም።

የአርቲስቱ መታሰር ሕጋዊ ውዝግብ ያስነሳ ሲሆን፣ አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎችም የፕሬዚዳንቷን ምሥል በማቃጠል የተጣሰ ምንም ዓይነት ሕግ የለም ሲሉ ተከራክረዋል።

አንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች አርቲስቱ የተጣለበትን የገንዘብ ቅጣት በመክፈል ከእስር ለማስፈታት ገንዘብ ማሰባሰብ ጀምረዋል።

ታንዛኒያ ተቺዎች ሃሳብን የመግለጽ ነጻነትን ይጋፋል ያሉትን የሐሰተኛ መረጃዎችን ሥርጭት ለመግታት ጠንከር ያሉ ሕጎችን ከጥቂት ዓመታት በፊት አውጥታለች።

አርቲስቱ በቲክቶክ ላይ በለጠፈው ቪዲዮው ፕሬዚዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሐሰንን የዘለፋቸው “ጠንካራ ቃላትን” በመጠቀም እንደሆነ ፓሊስ አስታውቋል።

የአካባቢው ፖሊስ ኃላፊ ቤንጃሚን ኩዛጋ ማክሰኞ ዕለት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ አርቲስቱ የፕሬዚዳንቷን ምሥል በማቃጠል እና አጸያፊ ይዘቶችን በኢንተርኔት በማጋራት ጥፋት ፈጽሟል ብለዋል።

“የአገራችንን መሪዎች መሳደብ የምቤያ ማኅበረሰብ ባህል አይደለም” ሲሉም ኃላፊው አክለዋል።

የታንዛኒያን ፕሬዚዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሐሰንን ፎቶ አቃጥሏል የተባለው አርቲስት አርቲስት

የፎቶው ባለመብት, MWANANCHI

የምስሉ መግለጫ, የታንዛኒያን ፕሬዚዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሐሰንን ፎቶ አቃጥሏል የተባለው አርቲስት

ሆኖም የፕሬዚዳንቷን ምሥል ማቃጠል ወንጀል የሚያደርግ ሕግ የለም በማለት አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች ክርክራቸውን እንደቀጠሉ ነው።

“ፎቶው የተነሳው በመንግሥት የፎቶግራፍ ባለሙያ ነው? በአደባባይ ወጥተው ለሕዝቡ እና ለአገሪቱ የሠሩትን ያስረዱ። ፎቶ ማቃጠል ወንጀል መሆኑን ሕጉን ጠቅሶ የሚያሳየን ማን ነው?” ሲሉም ጠበቃ ፊሊፕ ሙዋኪሊማ “ሙዋንቺ” ለተሰኘ ጋዜጣ ተናግረዋል።

ሕጋዊ ይሁንም አይሁን ነገር ግን በታንዛኒያ ሥነ ምግባር የጎደለው ነው በሚል የተፈረጀው ይህ ድርጊት ቁጣን ቀስቅሷል።

አርቲስቱ የአገሪቱን የሳይበር ሕጎች ተላልፎ ሐሰተኛ መረጃዎችን የያዙ ቪዲዮዎች በማሠራጨት ጥፋተኛ የተባለ ሲሆን፣ ቻውላ ክሱን እንዲከላከል ዕድል ሲሰጠው በዝምታ ማለፉን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ቅጣቱ ከበድ ያለ እና መንግሥት በተቃዋሚዎች ላይ ላይ እያወሰደ ያለውን የአፈና እርምጃ የሚያሳይ ነው ሲሉ ተቺዎች ወቅሰዋል።

ከሦስት ዓመታት በፊት ወደ ሥልጣን የመጡት ፕሬዚዳንት ሳሚያ የአገሪቱን የፖለቲካ እና የሲቪክ ምኅዳር ያሰፉ ማሻሻያዎች እንዳመጡ ይነገርላቸዋል።

ነገር ግን ተቃዋሚዎች እና የመብት ተሟጋቾች አገሪቱን ወዳለፈው ጨቋኝ ሁኔታ የሚመልሳት ፖሊሲዎች እየተመለሰች ነው ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።