የኬንያው ፕሬዝዳንት ተቃውሞ በተደራጀባቸው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ቀርበው ከወጣቶች ጋር ተወያዩ

ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ

የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ያዘጋጁትን የፋይናንስ ሕግ ውድቅ እንዲያደርጉ ያስገደዳቸው የወጣቶች ተቃውሞ የተደራጀበት ማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ላይ ለውይይት በመቅረብ ታሪክ ሠሩ።

ፕሬዝዳንት ሩቶ አርብ ከሰዓት በኋላ በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ ኤክስ ላይ በመቅረብ ከሕዝብ የሚቀርቡላቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ እና ማብራሪያ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸው ያልተጠበቀ በመሆኑ ኬንያ ውስጥ ከፍተኛ ትኩረትን አግኝቶ ነበር።

ከተቃዋሚዎቻቸው ጋር በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተካሄደው ውይይት የተፋጠጡት ፕሬዝዳንቱ ቀጥተኛ እና መሸፋፈን ያልታየባቸው ጠንካራ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ነበር።

በመድረኩ ላይ የመናገር ዕድል ያገኙት ተሳታፊዎች ፕሬዝዳንት ሩቶ እና መንግሥታቸው እስካሁን ያስመዘገቡትን እና ባህሪያቸውን በተመለከተ አንስተው አብጠልጥለዋቸዋል።

በጽህፈት ቤታቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ አስተናጋጅነት ሊካሄድ የነበረው ውይይት በገጠመው እክል ምክንያት ከፕሬዝዳንቱ ተቃዋሚዎች አንዱ በሆነው ኦሳማ ኦቴሮ ገጽ በኩል ነበር የተካሄደው።

የማኅበራዊ መድረክ ውይይቱ መሪ ኦቴሮም በርካታ ተቃዋሚዎች በፖሊስ በጭካኔ መገደላቸውን ለማመልከት “በሽብርተኛ አገር ውስጥ ነው እንዴ ያለነው?” በማለት ያቀረበው ጥያቄ የውይይቱን መስመር የቀየሰ ነበር።

በተቃውሞ ሰልፎቹ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውን በመግለጽ የመንግሥትን ይፋዊ የሟቾች ቁጥር ጥያቄ ውስጥ ከትቶ ነበር። ነገር ግን ፕሬዝዳንት ሩቶ ተገድለዋል የተባሉትን እና አስከሬናቸው የተደበቀባቸውን ቤተሰቦች እንዲያቀርብ ተናጋሪውን ጠይቀዋል።

“የመረጥናችሁ ሰዎች እንደመሆናችን መጠን ስለ እኛ ግድ አላችሁ” በማለት ፕሬዝዳንቱን የወቀሰው ደግሞ አንድ ተቃዋሚ ከፓርላማ ውጭ በጥይት ሲገደል አይቻለሁ ያለው ሚለር የተባለ የካሜራ ባለሙያ ነው። ቁጣው በግልፅ ድምጹ ላይ የሚሰማው ሚለር “በጣም ተናድጃለሁ። ጓዶች፣ መለስ ብላችሁ አስቡበት” ብሏል።

ሌላኛው ተሳታፊ ከዩኒቨርስቲ ተመርቆ ሥራ አጥ የሆነው ማርቪን ማቦንጋ ደግሞ “በካቢኔዎት ውስጥ ብቃት የሌላቸው በርካታ ባለሥልጣናት አሉ” ሲል ለፕሬዝዳንቱ ተናግሯል።

የውይይቱ መሪ ጉዳዩን ባለፈው ሳምንት ወደሞቱት ሰዎች በመመለስ ፕሬዝዳንቱ “የተገደሉትን ወይም የተጎዱትን ሰዎች ቤተሰቦች ለማነጋገር ሞክረዋል ወይ?” ሲል ጠየቀ።

ፕሬዝዳንቱ ከናይሮቢ ከተማ ወጣ ብሎ በተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ ወቅት በጥይት የተገደለውን የ12 ዓመት ህፃን እናት ማነጋገራቸውን በመግለጽ ምላሽ ሰጥተዋል።

የማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር መድረኮች በኬንያ ውስጥ የሚካሄደውን የውይይት ገጽታ ቀይረውታል።

እናም ዜጎችን ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር በማቀራረብ ብዙ ቁጥጥር ያልተደረገበት መድረክ በማዘጋጀት ከበድ ያሉ ጥያቄዎችን እንዲጠይቁ ማድረጉ ታሪካዊ ክስትት ሆኗል።

ከዚህ በፊት አንድ ፕሬዝዳንት ይህን ያህል በይፋ ወጥቶ እራሱን በማጋለጥ ከሕዝቡ በቀጥታ ለሚቀርቡለት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠበት ጊዜ የለም።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ “የኬንያ የበይነ መረብ ሠራዊት” እየተባለ ከሚጠራው ቡድን የሚቀርብባቸውን ትችት ተከትሎ የኤክስ አካውታቸውን ከሥራ ውጪ አድርገውታል።

በኬንያ ውስጥ በበይነ መረብ ላይ የሚካሄድ ዘመቻ አዲስ አይደለም። እራሳቸውን “በትዊተር ላይ ያሉ ኬንያውያን” ብለው የሚጠሩ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ኮርፖሬሽኖችን ይቅርታ እንዲጠይቁ አስገድደዋል።

ነገር ግን ይህ አንድ እርምጃ ነው ወደፊት የሄደ ነው።

ስፔስ የተባለው በኤክስ ላይ ያለው መድረክ ዜጎች ከአገራቸው መሪ ጋር አንድ ለአንድ በቀጥታ ለመገናኘት መድረክን ፈጥሯል፤ የኅብረተሰቡ አባላት እውነትን ለባለሥልጣናት በቀጥታ እንዲናገሩም አስችሏቸዋል።

ባለፉት ሳምንታት በኬንያ የተካሄዱት ተቃውሞዎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአገሪቱ ሕጎች እና ታክስ ላይ እንዲወያዩ እና መንግሥትን ተጠያቂ እንዲደርጉ አብቅቷቸዋል።

አንዳንድ ጊዜ፣ እነዚህ ዜጎች ብስጭታቸውን የሚገልጹባቸው መድረኮች ሆነዋል፣ ነገር ግን በሕዝብ መካከል የሚደረገውን ውይይት የበለጠ የዳበረ እንዲሆን አድርጎታል።

የፕሬዝዳንት ሩቶ የኤክስ ውይይት መድረክ 163,000 ተሳታፊዎች ጋር በመድረስ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።

ይህ አሃዝ ከ56 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ሕዝብ ካላት አገር አንጻር ሲታይ ትንሽ ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን የማኅበራዊ ሚዲያ ንግግሮች ወደ አደባባይ ከደረሱ በኋላ የሚደርሱት የሕዝብ ቁጥር ይጨምራል።

ምንም እንኳን ፕሬዝዳንት ሩቶ ሁልጊዜ በሚያስቆጡ እና ጠንከር ያሉ ጉዳዮችን በሚመለከት ክርክር ውስጥ መሳታፋቸው ብዙም የሚያስደንቅ አይደለም።

ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በፖለቲካ ሕይወታቸው ፈታኝ ጥያቄዎችን እና ሁኔታዎችን ከመጋፈጥ ወደ ኋላ ሲሉ ታይተው አይታወቅም።

በመገናኛ ብዙኃን ዘንድ ከቀደምት ፕሬዝዳንቶች በበለጠ በራቸው ክፍት መሆኑ ይነገራል።

አሁን በማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ላይ ቀርበው በቀጥታ ከሕዝብ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን መጋፈጣቸው ወደፊት ለሚመጡት ተተኪዎቻቸው አዲስ ልምድ ይሆናል።

በኤክስ (በቀድሞው ትዊተር) ስፔስ ላይ ፕሬዝዳንቱ በተገኙበት ግልጽ የውይይት መድረክ ላይ ከ150,000 በላይ ሰዎች ታድመው ነበር። አንዳንዶች ሩቶን ውሸታም እና ሐዘኔታ የሌላቸው በሚል ቢከሷቸውም እሳቸው ግን ጠንካራ ምላሽ ሰጥተዋል።

ፕሬዝዳንቱ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ባለሥልጣናትን በሙሉ ለማባረር ቃል ገብተው “አንዳንድ ባለሥልጣኖቻችን አስጸያፊ ድርጊቶችን እንደሚያሳዩ እስማማለሁ እና እራሳቸውን እንዴት እንደሚያስተካክሉ እኔም ጉዳዩን በግሌ አንስቼላቸዋለሁ። ከዚህ የበለጠም አርጋለሁ” ብለዋል።

መንግሥታዊው የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኬንያ ውስጥ ባለፉት ሳምንታት በተካሄዱ ተቃውሞዎች ወቅት ከ40 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ይገምታል፣ አብዛኞቹ የተገደሉት አወዛጋቢው ሕግ በፓርላማ አባላት በጸደቀበት ዕለት ነው።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተካሄደው ውይይት ወቅት ፕሬዝዳንት ሩቶ በተቃውሞው የተገደሉ ሰዎችን አሃዝ በማጋነን አንዳንዶችን “ግድየለሽ” በማለት የከሰሱ ሲሆን፣ ቁጥሩ 25 መሆኑን ተናግረዋል።

የኬንያ መንግሥት ያረቀቀው አዲሱ ሕግ የታክስ ጭማሪ በማድረግ አገሪቱ ካለባት 80 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ላይ ለመቀነስ ያለመ ነበረ።

በፓርላማው የጸደቀውን ሕግ በፕሬዝዳንቱ በሁለት ሳምንት ውስጥ መጽደቅ የሚገባው ቢሆንም፣ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ካለፈ በኋላ ካለ ፕሬዝዳንቱ ፊርማ ተግባራዊ ሊሆን ስለሚችል በርካታ ኬንያውያን ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በውይይቱ ላይ ፕሬዝዳንት ሩቱ ረቂቅ ሕጉን ማንሳታቸውን በማረጋገጥ፣ ነገር ግን ሕጉን በተመለከተ የተሳሳተ ግንዛቤ መፈጠሩን ጠቅሰዋል። አክለውም የሕጉ ዓላማ የኬንያውያንን ንግድ ማጠናከረ ነበር በማለተ የተካተቱትን ዕቅዶች ጠቃሚነት አብራርተዋል።

የታክስ ሕጉን በመቃወም ለሦስት ሳምንታት በዘለቀው ተቃውሞ ምክንያት ፕሬዝዳንቱ ሃሳባቸውን ቀይረው የጸደቀው ሕግ ተግባራዊ እንዳይሆን ቢወስኑም፣ ተቃውሞው ሩቶ ሥልጣን እንዲለቁ እና ተቃዋሚዎችን የገደሉ የፀጥታ ኃይል አባላት ለፍርድ እንዲቀርቡ ወደ መጠየቅ ተሸጋግሯል።