የኬንያ ሕዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ ለፓርላማ አባላቱ ሊደረግ የነበረው የደመወዝ ጭማሪ ታገደ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የበርካታ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈውን የኬንያ ሕዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ ለአገሪቱ የፓርላማ አባላት ታቅዶ የነበረው የደመወዝ ጭማሪ እንዲታገድ ተደረገ።
ሕዝባዊውን ተቃውሞ ተከትሎ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ዕቅዶቹ እንዲከለሱ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ተከትሎም ይህ እርምጃ የተወሰደው።
የተለያዩ የግብር ጭማሪዎችን የያዘው የፋይናንስ ረቂቅ ሕግ በአገሪቱ የተነሳው ተቃውሞ ፕሬዚዳንት ሩቶን እንዲሰርዙት ካስገደዳቸው ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው ይህ ውሳኔ የተላለፈው።
የደመወዝ እና የጥቅማጥቅም ኮሚሽን ሊቀመንበር ሊይን ሜንጊች ለመንግሥት ባለሥልጣናት ሊደረግ የነበረውን የደመወዝ ጭማሪን “በአሁኑ ጊዜ ባሉ የምጣኔ ሀብት እውነታዎች ምክንያት” እንዲቆም ተደርጓል ሲሉ ረቡዕ ዕለት ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ መጀመሪያ ለፌደራል ባለሥልጣናት 2 በመቶ ጭማሪ እና እንዲሁም ለዳኞች እና የክልል ባለሥልጣናት 5 በመቶ ጭማሪ እንዲደረግ አስቀምጦ ነበር።
አገሪቱ የፋይናንስ ቀውስ ላይ ናት እየተባለ ባለችበት ወቅት ለባለሥልጣናት እንዴት ደመወዝ ይጨመራል የሚሉ ጥያቄዎችም እየተነሱ ነበር።
ኮሚሽነሯ እንዳሉት እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው ከብሔራዊ ግምጃ ቤት ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ የደመወዝ ጭማሪው ከዚህ ወር መጀመሪያ ጀምሮ ተፈጻሚ እንዲሆኑ የሚያደርግ ማስታወቂያ ባለፈው ዓመት አውጥቶ ነበር።
በግብር መደራረቦች እና ከፍተኛ የኑሮ ውድነት እየታገለ ያለው የኬንያ ሕዝብ ተጨማሪ ግብር አንከፍልም የሚል ተቃውሞ ካሰማ በኋላም ነው የፕሬዚዳንት ሩቶ መንግሥት የፋይናንስ ሕጉን የሰረዙት።
በርካቶች መንግሥት በመጀመሪያ ወጪውን መቀነስ አለበት ሲሉ የተቹ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንት ሩቶም ይህንን እንደሚያከናውኑ ቃል ገብተዋል።
የገዢው ፓርቲ ጥምረት ሴናተር የሆኑት አሮን ቼሩየትን ጨምሮ በርካታ የፓርላማ አባላት የደመወዝ ጭማሪው ውድቅ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
የገዢው ፓርቲ አጋር የሆኑት የተቃዋሚ ፓርቲ ፓርላማ ተወካይ የሆኑት አዳን ኬይናን ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተው የታሰበው ጭማሪ “የሕዝቡን ድምጽ መስማት የተሳነው” ሲሉ ተችተውታል።
ማክሰኞ ዕለት የብሔራዊ ምክር ቤቱ ፀሐፊ ሳሙኤን ንጆሮጌ የደመወዝ ጭማሪው የክልል መንግሥት ሠራተኞችንም ስለሚነካ ውድቅ ሊደረግ አይቻልም ሲሉ ለፒፕል ዴይሊ ጋዜጣ ተናግረው ነበር።
ሆኖም ፕሬዚዳንት ሩቶ የአገሪቱ ግምጃ ቤት ይህንን እንዲገመግም ትዕዛዝ ከሰጡ በኋላ ነው ዕቅዱ የተሻረው።
ሥራ አጥነት፣ የኑሮ ውድነት፣ ተደራራቢ ግብር እንዲሁም ከሰሞኑ በተነሳው ተቃውሞ ሰልፈኞች በፖሊስ መገደላቸው ከፍተኛ ቁጣ የፈጠረው የኬንያውያን የተቃውሞ መልኩን ቀይሮ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ከሥልጣን እንዲወርዱ እየጠየቁ ነው።
ሩቶ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በተነሳው ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ 39 ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገልጿል።
በዚህ ሳምንት ማክሰኞ በቀጠለው ተቃውሞ ሱቆች እና የተለያዩ መደብሮች ሲዘረፉ የታዩ ሲሆን፣ ፖሊስ በሕገወጥነት የተሳተፉ ናቸው ያላቸውን የ38 ሰዎችን ፎቶግራፍ ይፋ አድርጓል።
ተቃውሞውን እያዘጋጁ ያሉ ወጣቶች “የተቀጠሩ ወንጀለኞች” በእነዚህ ሰላማዊ ተቃውሞዎች መካከል ሰርገው እየገቡ እንደሆነ ገልጸው፣ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ስትራቴጂያቸውን እየገመገሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።












