“ኃይል የሕዝብ ነው” ያሉት ኬንያውያን ወጣቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
“በትግሉ ከሞትኩኝ፣ ለእናቴ ንገሯት የቻልኩትን ሁሉ አድርጌያለሁ” ይህ ጽሁፍ የሰፈረበትን ካናቴራ የለበሰው ኬንያዊ ወጣት በናይሮቢ ፓርላማ አካባቢ ነበር የታየው።
የኬንያ መንግሥት ገቢውን ለመጨመር በሚል ሰኔ 19/ 2016 ዓ.ም ያጸደቀውን የፋይናንስ ረቂቅ ሕግ ለመቃወም ከወጡ በመቶ ሺዎች ከሚቆጠሩት መካከል አንዱ ነው።
ሞትንም ቢሆን ለመጋፈጥ እንደቆረጠ የገለጸውን ወጣት ጨምሮ በርካቶች የአገሪቱን ፓርላማ እንደ ትግል ማዕከል ነበር ያዩት።
ሕግ ሆኖ ለመውጣት የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ ፊርማ ብቻ የሚጠብቀው የፋይናንስ ረቂቅ በርካታ የአፍሪካ አገራትን በተለይም ድሃውን ሕዝብ በድህነት አዙሪት ውስጥ በመዘፈቅ የሚወቀሰው ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ተግባራዊ እንዲደረግ የሰጠው ማሻሻያ ነው።
ተቃውሞውም በመንግሥት ላይ ብቻ ሳይሆን ኬንያን በእጅ አዙር እየጠመዘዟት ነው ባሏቸው እንደ አይኤምኤፍ ባሉ ተቋማትም ላይ ነው።
በመላ አገሪቷ ከተከሰተው እና የበርካቶችን ሕይወት ከቀጠፈው ተቃውሞ በኋላ ረቂቁ በፓርላማው ቢጸድቅም ፕሬዚዳንቱ ሕግ ሆኖ እንዲያልፍ የመጨረሻ ፊርማዬን አላስቀምጥም ብለዋል።
“ኬንያውያን በሕጉ ዙሪያ ያሰሙትን ተቃውሞ በደንብ ተከታትያለሁ፤ ስለዚህም ሕጉን እንደማይፈልጉት በግልጽ ተናግረዋል፤ ይህንንም ተቀብዬ በሕጉ ላይ አልፈርምም፣ ስለዚህም ቀሪ ይሆናል። ሕዝቡ ፍላጎቱን አሳውቋል” ሲሉ ለኬንያውያን አሳውቀዋል።
መንግሥት በእነዚህ የቀረጥ ጭማሪዎች 2.7 ቢሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ እና አገሪቷ ያለባትን የዕዳ ጫና ለማቃለል ይውላል ሲል እየተሟገተ ቆይቷል።
ኬንያ በአሁኑ ጊዜ ያለባትን 80 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ብሔራዊ ዕዳን ለመቀነስ የተለያዩ ግብሮችን መጣል አንዱ እርምጃ ነው ይላል መንግሥት።
በሥራ አጥነት፣ የኑሮ ውድነት፣ ተደራራቢ ግብር በቃን እንዲሁም ከሰሞኑ በተነሳው ተቃውሞ ሰልፈኞች በፖሊስ መገደላቸው ከፍተኛ ቁጣ የፈጠረበት ኬንያውያን የተቃውሞ መልካቸውን ቀይረው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ከሥልጣን እንዲወርዱ እየጠየቁ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የመንግሥትን ውሳኔ ያስቀለበሰው ተቃውሞ
የመንግሥት ገቢውን ለማሳደግ ዳቦን ጨምሮ በምግብ ዘይት፣ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ፣ የሞባይል ስልኮች፣ ኮምፒውተሮች፣ ተሽከርካሪዎች እና በሌሎች ምርቶች እና አገልግሎቶች ቀረጥ ላይ ጭማሪ ያካተተ ረቂቅ የፋይናንስ ሕግ ተቃውሞ ከቀረበበት ሳምንታትን አስቆጠረ።
በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች የነበረውን ተቃውሞ የመረጥናቸው ተወካዮች ሕዝቡ እየሰሙ ያሉ አይደለም ያሉ ወጣቶች ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ሰኔ 11/ 2016 ለተቃውሞ ሲወጡም አላማቸው የአገሪቱ ፖሊሲዎች የሚወሰኑበትን ፓርላማ ለመቆጣጠር ነበር።
ባለፈው ሳምንት በነበረው የሁለት ቀን ተቃውሞ ‘ኦኩፓይ ዘ ፓርላመንት’ በሚል የተካሄደው የአደባባይ አገር አቀፍ የተቃውሞ ሰልፍ ፓሊሶች አስለቃሽ ጋዝ እና ውሃ በመርጨቱ ምክር ቤቱን አልተቆጣጠሩም ነበር።
ለሳምንታት ያህል ከፍተኛ ተቃውሞ ሲቀርብበት እና ሲያወዛግብ የነበረው ይህ ረቂቅ ሕግ በሚጸድቅበት ዕለትም ነው ወደ ፓርላማ ያመሩት።
የምክር ቤቱ አባላት በቀጥታ በስልኮቻቸው ይህንን ረቂቅ ሕግ ውድቅ እንዲያደርጉ በሺዎች የሚቆጠሩ መልዕክቶች ደርሷቸዋል።
በትዊተር፣ በኢሜይልም የመረጣቸው ሕዝብ ተማጽኗቸዋል።
እንዲሁም ረቂቁን ውድቅ ላደረጉ የምክር ቤት አባላት አበባ በመላክ እንዲሁም ድጋፍ ለሰጡም የአስከሬን ሳጥን በቤቶቻቸው አድራሻ ተልኮላቸዋል።
“አገሪቷ የነሱ ብቻ አይደለችም። የሁላችንም ናት። ሥልጣን የህዝብ ነው። ፓርላማውን ተቆጣጥረን የሕዝብ ተወካዮች የኬንያ ሕዝብ የሚለውን እንዲሰሙ እናደርጋቸዋለን” በሚል በተደጋጋሚ መንግሥትን በድፍረት በመቃወም የሚታወቀው ቦኒፈስ ምዋንጊ ለሰልፍ ከመውጣቱ በፊት ተናግሮ ነበር።
“ዊልያም ሩቶ ኬንያውንን በአንድነት እንዲቆሙ አድርገዋል። ሁሉንም ወደ ማኡ ማኡ ታጋዮች እየቀየረን ነው” የሚል ጽሁፍ የያዙ ህንዳውያን በተቃውሞው ላይ ታይተዋል።
የማኡ ማኡ ታጋዮች በአርባዎቹ እና አምሳዎቹ ጨቋኙን የብሪታንያ ቅዢ ገኝን ለመገርሰስ በጽኑነት የተደረገ ትግልም በማስታወስ ቀጣዩም ትውልድ ይህንን ያደርጋል አሉ።
የማክሰኞውም ተቃውሞ የፋይናንስ ህግ ይቅር ብቻ ሳይሆን ሩቶ ከስልጣን ይልቀቁ የሚል የተሰማበትም ነው።
የኬንያ ሰንደቅ ዓላማ እና የተለያዩ መፈክሮችን ይዘው የወጡ ተቃዋሚዎች እየዘፈኑ፣ እየጨፈሩ ነበር ወደ ፓርላማው ያመሩት።
ተቃውሟቸው ረቂቅ ህጉን ከመጽደቅ አላስቀረውም።
ረቂቅ ህጉን የፓርላማውን ከፍተኛ ወንበር የተቆጣጠረው የፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ ፓርቲ የምክር ቤት አባላት 195 ድጋፋቸውን ሰጥተው እንዲሁም በ106 ተቃውሞ አለፈ።
ረቂቅ ህጉ ሲጸድቅ ወጣቱ ከውጭ ሆኖ ተቃውሞውን እያሰማ ነው የነበረው።
ባለፈው ሳምንት ሰላማዊ የነበረው ተቃውሞም በሁከት ተሞላ።
ፖሊስ በአስለቃሽ ጋዝ እና ውሃ መርጨት ብቻ ሳይሆን ጥይትም መተኮስ ጀመረ።
ፖሊስ ሊቆጣጠረው ባልቻለም ሁኔታ ወጣቱ ጥብቅ ቁጥጥር ያለበትን ፓርላማ በሮች ገነጣጥለው ገቡ። ። መስኮቶች ተሰባበሩ። የፓርላማው ህንጻም እሳት ተለኮሰበት።
ፓርላማውን ጥሰው የተቆጡ ወጣቶች ሲገቡ የፋይናንስ ህጉን ያጸደቁትን የፓርላማ አባላት ለማስወጣት ሄሊኮፕተር ከምክር ቤቱ ላይ ተንዣበበች።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ኬንያ በጎርፍ በተጥለቀለቀች ወቅት መውጫ አጥተው የነበሩ ነዋሪዎችን ለማዳን ሄሊኮፕተር አለማሰማራቱን በኋላ ላይ የጠቀቁ አልጠፉም።
በተለያዩ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያዎች በቀጥታ የተላለፈው ይህ ሁነት በርካቶችን አስደነገጠ።
ፓሊስም ምላሹ ጥይት ነበር። በርካታ አስከሬኖችም ጎዳናዎች ላይ ታዩ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከኬንያ ፓርላማ ፊት ለፊት ያልታጠቁ ወጣቶች ላይ ጥይት ተኩሶ ሲገድል የተመለከተው የሲኤንኤን ጋዜጠኛ ላሪ ማዶዎ “ውሃ ይዘው፣ ብሄራዊ መዝሙር እየዘመሩ፣ መፈክር እያሰሙ የነበሩ ናቸው” ብሏል።
ፖሊስ ተቃዋሚዎችን ብቻ ሳይሆን የህክምና ባለሙያዎችን በቁጥጥር ስር ሲያውል፣ እንዲሁም ሲደበድብ ሲኤንኤን አሳይቷል።
የኬንያው ዋነኛ ተቃዋሚ እና የአዚሚዮ ጥምረትን የሚመሩት ራይላ ኦዲንጋ መንግሥት “በአገራችን ልጆች ላይ ጭካኔ የተሞላበት የኃይል በትሩን እየሰነዘረ ነው” ሲሉ ተችተውታል።
ያልተጠበቁ ግድያዎችን ተከትሎ በኬንያ የኤክስ ገጽ ለሰዓታት ተቋረጠ፣ ኢንተርኔት ተስተጓጎለ፣ ዩቲዪብ ቀጥ አለ።
ኢንተርኔት ከመዘጋቱ በተጨማሪ የግል ንብረት የሆነው ኬቲኤን ቴሌቪዥን ጣቢያ በተቃውሞ ዘገባ ምክንያት ከመንግሥት እዘጋችኋለሁ ማስፈራሪያ ደርሶናል አሉ።
ባላት ጠንካራ የሲቪል ማህበረሰብ ንቅናቄ የምስራቅ አፍሪካ የዲሞክራሲ ማዕከል ተደርጋ በምትታየው ኬንያ የተከሰተው ደም መቃባት ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡን አስደነገጠ።
አሜሪካ ሁኔታው እንዲረጋጋ የጠየቀች ሲሆን ካናዳ፣ ጀርመን፣ እንደ ዩናይትድ ኪንግደም ያሉ ከ10 በላይ ምዕራባውያን አገራት “በተለይም ከፓርላማ ውጭ የነበሩ ትዕይንቶች አስንደግጠውናል” ብለዋል።
ተቃውሞ በመዲናዋ ብቻ ሳይሆን የሩቶ የትውልድ ስፍራ ጊሹ ግዛትን ጨምሮ፣ በኪሱሙ፣ ሞምባሳ አገሪቷ ካሏት 47 ግዛቶች ውስጥ በ35ቱ ተካሂዷል።
በኬንያ የፓርላማውን በር ጥሰው በገቡ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ከተሞችም ግድያዎች የተፈጸሙ ሲሆን አንዳንድ ሰብዓዊ የመብት ተሟጋቾች የሟቾችን ቁጥር ከ20 በላይ አድርሰውታል።
የኬንያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሊቀመንበር “በኬንያ በአንድ ቀን ይህን ያህል ሰው የተገደለበት ተቃውሞ ገጥሞን አያውቅም” ማለታቸው በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲሽከረከር ነበር።
ከናይሮቢ ውጭ በተለይም ጊቱራይ በተሰኘችው ከተማ በርካታ ግድያ እንደነበር ተነገረ።
“በጊቱራይ በተሰኘችው ከተማ የተፈጸመው ግድያ፣ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተተኮሰው ጥይት፣ ኢንተርኔት መዝጋት፣ አፈና፣ ሙስና፣ ውሸት፣ ዝርዝሩ ማብቂያ የለውም” ሲሉ ኬንያውን ቁጣቸውን በማህበራዊ ሚዲያ አሰፈሩ።
“ወጣት ወንድሜ ለተሻለች ኬንያ በመቆም ህይወታቸውን ካጡ ብዙ ጀግኖች መካከል አንዱ ነበር። የምንፈልገው የተሻለች አገር ብቻ ነው” በሚል አንደኛዋ ትዊተር ላይ መልዕክቷን አሰፈረች
ከሰልፎቹም በፊት የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎችን አፍኖ በመውሰድ ያስፈራራው የሩቶ አስተዳደር ከተቃውሞውም በኋላ ማስጠንቂያዎችን አስተላለፈ።
ቢያንስ 12 የሚሆኑት ከተቃውሞ በፊት በሌሊት በኬንያ ደህንነት አባላት ታፍነው መወሰዳቸውን አምነስቲ አስታውቋል።
ሩቶ በዚያው ዕለት ማምሻውን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ መንግሥታቸው “ሁከት እና ስርዓት አልበኝነት” ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠነቀቁ።
ወጣት ተቃዋሚዎቹን “ወንጀለኞች” ሲሉ ጠሩ እንዲሁም “አገር ክደዋል” ሲሉ ወረፏቸው።
ሩቶ ከማስፈራራት ይልቅ “ብልህ መሪ ቢሆኑ ነገሮችን አረጋግተው ሰምተናችኋል። የሂደቱ አካል እንድትሆኑ እንፈልጋለን ይሉ ነበር” ሲሉም አንዳንዶች በትዊተር መልዕክታቸውን ገለጹ
ከሰዓታት በኋላ የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር አደን ባሬ ዱዋሌ የአገሪቱ ሰራዊት እንዲሰማሩ ትዕዛዝ ሰጡ።
“በግብር በተሰላቸ፣ በኑሮ ውድነት እና በስራ አጥነት በተጎሳቆለ ወጣት ላይ ጦሩን ማሰማራት የማይጠበቅ ነው” በማህበራዊ ሚዲያ ከተሰጡ አስተያየቶች አንዱ ነበር።
የፋይናንስ ህጉ ድሃውን ለመቅጣት የተጣለ ነው ሲሉ በርካቶች ይተቹታል። በተለይም መጀመሪያ የረቂቁ አካል ተደርገው በኋላ እንዲወገዱ የተደረጉት ዳቦ.፣ የምግብ ዘይት፣ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ እና የህጻናት ዳይፐር ላይ ግብር እና ቀረጥ ከሚጥሉ የባለስልጣናቱን ወጪ ለምን አይቀንሱም ተባለ።
ሩቶ ስልጣን ከመጡ በኋላ ወደ 38 አገራት ያደረጓቸው ጉብኝቶች፣ ባለፈው ወደ አሜሪካ ሲሄዱ ለግል አውሮፕላን ያወጡት 1.5 ሚሊዮን ዶላር የፈጀ ጉብኝት፣ ምክትላቸው ሪጋቲ ጋቻውጋ ቢሯቸውን ለማደስ ይወጣል የተባለው 2.6 ቢሊዮን ሺልንግ የኬንያውንን ቁጣ ያቀጣጠሉ ናቸው።
እንዲሁም የሩቶን ቤተመንግሥት (ስቴት ሃውስ) ለማደስ የተመደበው 11.5 ቢሊዮን ሺልንግ በከፍተኛ የዋጋ ግሽበት በተመታችው አገር የሚዲያዎች መነጋገሪያ ሆነው ነበር።
የፓርላማ አባላቱ አዳዲስ መኪና ሞዴሎች፣ የተቀናጡ ቤቶች እና ሃብታቸውን በቲክቶክ እና በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ሲያሳዩ “አምላክ ሰጥቶናል” እያሉ በመሆኑ በርካታ ወጣቶች መሳለቅ መሆኑም ተሰምቷቸዋል።
ተቃውሞው በአብዛኛው ጄንዚ የተሰኘውን በ20ዎቹ ዕድሜ ላይ ያሉትን ትውልድ ያካተተ ቢሆንም ከብሔር፣ ከመደብ እና ከፖለቲካ ድጋፍ አውጥቶ በአንድነት ያቆመ ነው።
ከኬንያም አልፎ ህዝብ ሲነሳ አልበገሬ መሆኑን ያሳየው ይህ ተቃውሞ በተለያዩ አገራት ወጣቶች እንዲሁም ታዋቂ ሰዎች ድጋፍ ተሰጥቶታል።
የኡጋንዳው ፖለቲከኛ ቦቢዋይን፣ በደቡብ አፍሪካ ስር ነቀል ለማምጣት የሚታገለው ጁሊየስ ማሌማ ከናንተ ጋር ነን ብሏል።
እንዲሁም በርካታ የመብት እንቅስቃሴዎችን በመደገፍ የሚታወቀው አለም አቀፉ የመረጃ ጠላፊ ቡድን ለፕሬዚዳንት ሩቶ እና ለምክር ቤቱ አባላት የኬንያን ህዝብ የማያዳምጡ ከሆነ መዘዙ ከፍ ያለ የሳይበር ጥቃት እናደርሳለን ሲል አስጠንቅቋል።
የአስተዳደሩ እብሪተኝነት፣ ሙስና እና በአዲሱ የፋይናንስ ቀረጥ እንደታየው ለረዥም ጊዜ የቀጠለው ጆሮ ዳባ መልበስ አዲሱ ትውልድ ለትግል እንዲነሳ አድርጎታል ይላል በኒው ሂማኒታሪያን ከፍተኛ አዘጋጅ የሆነው ፓትሪክ ጋታራ ‘ ኢን ኬንያ ቱሞሮው ኢዝ ሂር’ በሚለው የአልጀዚራ ጽሁፉ።
ከሁለት ዓመታት በፊት በነበረው ምርጫ በአገሪቱ ፖለቲካ ፍላጎት የላቸውም ተብለው የተወቀሱት ወጣቶች ናቸው ትግሉን ያቀጣጠሉት።
"ቤተሰቦቻቸው የመረጧቸው ፖለቲከኞች አገሪቷን ወደ ቁልቁለት እየሰደዷት ነው፤ቃል የገቡትን ማክበር አልቻሉም እጃችንን አጣጥፈን ልንመለከታቸው አይገባም" ማለታቸው አዲስ ነገር አይደለም ይላል ፓትሪክ።
በ80ዎቹ እና በ90ዎቹ ወጣቶች የነበሩት ወላጆቻቸው ከቅኝ ግዛት ያላቀቃቸውን የነጻነት ትውልድ ከዲሞክራሲያዊ ነጻነት እና ግላዊ መብቶች በላይ ልማት ፣ አንድነት እና ሰላም ይቅደም ሲሉ ያስቀመጡት ፖለቲካዊ ተሳትፎ ውድቅ አድርገዋል።
ያ ትውልድ ጨቋኝ አገዛዝ እንዴት እንደሚገረሰስ፣ የፖለቲካ ስርዓት እንዴት እንደሚሻሻል ፣ ህዝባዊ ቅሬታን የሚያስተናገግድ ከመንግሥት ውጭ ያሉ ተቋማትን በመገንባት ትርጉም ያላቸው ለውጦችን ማምጣት እንደቻለ ይጠቀሳል።
ባደረጓቸውም ትግሎች የአገሪቱን ፖለቲካ በመቀየር፣ ጤናማ ለሆነ የስልጣን ፉክክር እንዲሁም ነጻነት እና ምጣኔ ኃብቱ እንዲንሰራራ አድርገዋል።
የ24 ዓመቱን አምባገነናዊ የዳንኤል አራፕ ሞይ የገረሰሰው ይህ ትግላቸው ካመጣው ነጻነት በኋላ ብዙዎቹ የአዲሱ የተመሰረተው አገዛዝ አካል ሆኑ።
በኋላም አራፕ ሞይን ማስወገድ የቻሉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንዲከስሙ ተደረጉ፣ ነጻ ሚዲያዎች ደበዘዙ እንዲሁም ከስርዓቱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አጠነከሩ።
ፓትሪክ እንደሚለው እንደቀድሞዎቹ የነጻነት ትውልዶች ታግለው የጣሉትን የቅኝ ግዛት ስርዓት መልሰው ለመድገም እንደሞከሩት ሁሉ እነዚህኞቹም ሙሰኛ እና ጨቋኝ በሚል የታገሉትን አገዛዝ እንደገና መልሰው ማምጣት ጀመሩ።
የአሁኑ ትውልድም ያደገው ወላጆቻቸው ስኬት ብለው በሚያዩዋቸው እና ታግለን ጥለነዋል በሚሉት አዲስ ስርዓት ነው።
ነገር ግን አዲሱ ትውልድ ያለፈውን አይመለከትም፣ መጪውን ነው የሚያየው። የአዲሱ ትውልድ በኢንተርኔት፣ በዲጂታል መሰልጠን፣ አለመፍራታቸው የሩቶ አስተዳደርን በተደናበረ መልኩ እንዲሄድ አድርጓልም ተብሏል።
በአንድ በኩል ወጣት ተቃዋሚዎችን አበረታትተው ለውይይት ዝግጁ ነኝ ቢሉም በሌላው መልኩ ደግሞ ተቃዋሚዎችን በመግደል፣ በማቁሰል እንዲሁም መሪዎች ናቸው ተብለው የሚታሰቡትን በማፈን ሰውሯል።
ነገር ግን ፓትሪክ በርካታ ስልቶቻቸውን ከሞይ እንደተማሩ የሚናገርላቸው ሩቶ ያንን ማድረግ አይችሉም ይላል።
የትግል እንቅስቃሴው የስልጣን ተዋረድ የሌለው እና የታዋቂ ፖለቲከኞችን ተሳትፎ የማይፈልግ እንዲሁም ከሚታወቀው ፕሬስ ይልቅ ማህበራዊ ሚዲያን የመረጠ በመሆኑ ያንን ማድረግ አይችሉም ይላል።
ባለፈው ሳምንት እሁድ ለሰባት ተከታታይ ሰዓት በተደረገ ስብሰባ 60 ሺህ ሰው ተሳትፏል።
የተቃውሞ ሰልፎቻቸውን ለማካሄድ፣ ለማደራጀት፣ ገንዘብ ለማሰበሳብ እንዲሁም ለተጎዱ ጓዶቻቸው ደም ልገሳ የሚጠየቀው በነዚሁ ነው።
ከዚህ ቀደም የኪቦርድ ተዋጊዎች ሲሉ ያጧጣሏቸው ወጣቶች ባሳዩት የተደራጀ ተቃውሞ ፖለቲከኞች መደናገጣቸው አልቀረም።
ወጣቱ ፖለቲከኞች እንዲሁም ጋዜጠኞች የሚተልሟቸውን ማዕቀፎች አይቀበሉም፤ የራሳቸውን የትግል መስመር አስምረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአይኤምኤፍ ድጋፉን የሰጠው ማሻሻያ
የአገሪቱ መንግሥት ከተቃዋሚዎች ውዝግብ ጋር የገባበት የፋይናንስ ህግ በአይኤምኤፍ እንዲተገበር የተነገረው ፖሊሲ ነው።
ከፍተኛ ዕዳ ካለባቸው አገራት አንዷ የሆነው ኬንያ ያለባት እዳ ለማቃለል በሚል ነበር በአውሮፓውያኑ 2021 ከአለቀም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ ጋር) ስምምነት ላይ የደረሰችው።
መርሃ ግብሩ የአገሪቱን የዕዳ ጫና ለማቃለል መንግሥት ገቢውን ማሳደግ እና ሌሎች የምጣኔ ኃብት ማሻሻያዎች ላይ ያተኮረ ነው።
የኬንያ ዕዳ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ውስጥ 68 በመቶ ሲሆን ይህም በአለም ባንክ እና አይኤምኤፍ ከሚመከሩት 55 በመቶው ብልጫ አለው።
አገሪቷ ከበጀቷም ውስጥ ከፍተኛውን ወጪ ብድሯን ለመክፈል ታወጣለች ብሏል።
የኬንያውን ስራ አጥ እና ድሃውን ህይወት ለማሻሻል ቃል የገቡት ሩቶም የአገሪቱን ከብድር ለማውጣት ፊታቸውን ወደ አይኤምኤፍ አድርገዋል።
በዚህ ጥር ወርም ብቻ አገሪቷ ከአይኤምኤፍ 941 ሚሊዮን ተበድራለች። ነገር ግን መንግሥታት እነዚህን ብድሮች ለመቀበል አይኤምኤፍ ገቢያቸውን በተለያየ መልኩ እንዲጨምሩ ወጪያቸውን እንዲቀንሱ ያስገድዳቸዋል።
ኬንያም ከዚህ የተለየ አልነበረም ሩቶ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በበቆሎ ዱቄት እና ነዳጅ ላይ መንግሥት የሚያደርገውን ድጎማ አነሱ።
እንዲሁም ከዚህ በተጨማሪ አይኤምኤፍ ባስቀመጠው መሰረት በነዳጅ ላይ ከ8 በመቶ ወደ 16 በመቶ ቫት ሲጥሉ የነዳጅ ዋጋ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በሊትር ከ200 ሺልንግ በላይ ወጣ።
መንግሥት ባነሳቸው ድጎማዎች እና በተጣለው ቫት ምክንያት ባለፈው ዓመት አገሪቷ በርካታ ሰዎች የተገደሉበት ተከታታይ ተቃውሞ አየች።
በድሃው መራጭ ጫንቃ ወደ ስልጣን የመጡት ዊልያም ሩቶ አገሪቷን ለበለጠ ግሽበት በመዳረግ ተተቹ።
በመጨረሻ የህዝቡ ቁጣ የበረታቸው ሩቶ በነዳጅ ላይ የመንግሥት ድጎማን መለሱ ይህም በአይኤምኤፍ ወቀሳ ደርሶበታል።
አይኤምኤፍ በአገራት ላይ ያስቀመጣቸው እነዚህ ድንጋጌዎች እና መንግሥቶቻቸው እነዚያን ፍላጎቶች ለሟሟሏት የሚወስዷቸው የምጣኔ ኃብት እርምጃዎች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአርጀንቲና፣ ሱሪናም እና ስሪላንካን ጨምሮ በተለያዩ አገራት አለመረጋጋት ፈጥሯል።
እነዚህ የዓለም አቀፍ አበዳሪዎች የምጣኔ ኃብት አስከፊ መዘዞች ከዚህም በፊት የታዩ ናቸው።
በአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ በርካታ የአፍሪካ መሪዎች አይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክ ከፍተኛ ብድር እንዲወስዱ እና ተቋማቱ ያቀረቡትን ጥብቅ የኒዮ ሊበራል ሞዴል ለመከተል ተገደዋል።
እነዚህ ተቋማት ስትራክቸራል አድጀስትመንት ፕሮግራም (መዋቅራዊ የማስተካከያ ፕሮግራሞችን) እንዲተገብሩ አድርገዋቸዋል።
በዚህም በትምህርት፣ የጤና አገልግሎት እና በማህበራዊ ወጪዎች ላይ ያለውን ወጪያቸው እንዲቀንሱ ተደርገው ገቢያቸውን ወደሚጨምር የወጪ ንግድ ላይ አተኩረዋል። ይህም ከፍተኛ ቀውስ መፍጠሩን የምጣኔ ኃብት ባለሙያዎች ይተቻሉ።












