ሕዝባዊ እምቢተኝነትን ያቀጣጠለው የኬንያ አዲሱ ትውልድ

 የኬንያ ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ኬንያውያን የፋይናንስ ሕግ ረቂቅ መነሻ በማድረግ የአገሪቱን ፓርላማ ጭምር ጥሶ የገባውን ባለፈው ዓመት የተካሄደውን ፀረ መንግሥት ተቃውሞ አንደኛ ዓመትን ለመዘከር ዛሬ [ረቡዕ] ሰኔ 18/2017 ዓ.ም. በተለያዩ ከተሞች አደባባይ ወጥተዋል።

የኬንያ ፖሊስ በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎችን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ የተኮሰ ሲሆን፣ ቢያንስ ሁለት ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች መቁሰላቸው ተዘግቧል።

በመዲናዋ ናይሮቢ የሚገኙ የንግድ ቤቶች እና ትምህርት ቤቶች ሁከቶች ይከሰታሉ በሚል ተዘግተው ውለዋል።

የአገሪቱን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ባሸበረው ባለፈው ዓመት በተካሄደው ሕዝባዊ የተቃውሞ ማዕበል ከ60 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

ሕዝባዊው ተቃውሞ በተቀሰቀሰበት ወቅት ቢቢሲ የአዲሱን ትውልድ እምቢተኝነት በተመለከተ የሚከተለውን ዘገባ አጠናቅሮ ነበር።

ኬንያውያን ወጣቶች መንግሥታቸውን ለመቃወም አደባባይ ወጥተዋል።

መነሻው መንግሥት ሊያጸድቀው ጫፍ የደረሰው አዳዲስ ቀረጦች እና ግብር ቢሆንም በርካቶችን ያጎሳቆለው የኑሮ ውድነት፣ ሥራ አጥነት፣ ድህነት እና ሙስና መከራችን እያሳየን ነው እያሉ ነው።

መንግሥት ገቢውን ለመጨመር ዳቦን ጨምሮ በምግብ ዘይት፣ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ፣ የሞባይል ስልኮች፣ ኮምፒውተሮች፣ ተሽከርካሪዎች እና በሌሎች ምርቶች እና አገልግሎቶች ቀረጥ ላይ ጭማሪ ያካተተ ረቂቅ የፋይናንስ ሕግ አውጥቶ ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ተደጋጋሚ ግብሮችን በመጨመር ያሰላቹት የኬንያ ሕዝብ፣ በተለይ ወጣቶች ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተዋል።

"መሪዎቹ እየመሩ አይደለም። በድህነት እና በሥራ አጥነት እየማቀቀ ያለውን ወጣት ጀርባውን እያጎበጡት ነው" ይላሉ።

ኬንያ ከዚህ ቀደም በርካታ ሕዝባዊ ተቃውሞዎችን ብታይም ያለፈው ዓመት ግን ለየት ያለ ነበር።

ከዚያ ቀደም የነበሩትን የአደባባይ ተቃውሞዎችን ያደራጁ የነበሩት ተፎካካሪ ፖለቲከኞች ነበሩ።

የአሁኑ ግን ወጣቱ ማንም ሳይቀሰቀሰው ነው ለተቃውሞ ወደ አደባባይ የተመመው።

የአንበሳውን ድርሻ የያዙትም ጄንዚ (ጄኔሬሽን ዙመርስ) የሚሰኙት በሃያዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው ትውልድ አካል ናቸው።

በፍርሃት የተሸበቡ አይደሉም።

ደፋር ናቸው። ሥልጣን አያሳስባቸውም። ይጋተራሉ። በቴክኖሎጂ የተካኑ ናቸው።

የዲጂታል ዘመን ልጆች ናቸው። ለጥያቄ የሰሉ ጭምር።

አሻፈረኝ ባይነታቸው እና እምቢተኝነታቸውም የጸና ነው።

ቤተሰቦቻቸው በድህነት እየማቀቁ መዘዞችን ፈርተው ዝም ማለታቸውን ልጆቹ አልተቀበሉትም።

“መጻኢ ተስፋችንን አትነጥቁም” እያሉ ነበር ፖለቲከኞቻቸውን።

ለሁሉም ክብር ይገባል የሚለውን አያምኑም።

በአምላክ የተመረጥን ነን ለሚሉት የኬንያ ፖለቲከኞች “አምላክ የተመዘገበ መራጭ አይደለም። ሕዝብ ነው የመረጣችሁ” ብለዋቸዋል።

ሙሰኛ የሚሏቸውን ፖለቲከኞች ለማዋረድ ወደ ኋላ አይሉም።

“ከሥልጣን ልቀቁ” ሲሉም ተሰምተዋል።

ፕሬዝዳንት ሩቶን ጨምሮ የኬንያን ፖለቲከኞችን ምሥል ከአንገታቸው በላይ በአሳማ ፊት በመቀየር ፎቶዎች ይዘው ወጥተዋል።

“ዘራፊዎችን ነው የመረጥነው፤ መሪዎች አይደሉም” ፤ “ድህነት ሰው ሰራሽ ነው” የሚሉ መፈክሮችን በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች አደባባዮች ላይ አስተጋብተዋል።

 የኬንያ ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የወጣቱ ተቃውሞ የበረታበት መንግሥትም በረቂቅ የፋይናንስ ሕጉ የተካተቱ የተወሰኑ ቀረጦችን ለማንሳት ተገዷል።

እንዲቀሩ ከተደረጉት መካከል በዳቦ ላይ ሊጣል የነበረው 16 በመቶ ቀረጥ፣ የምግብ ዘይት፣ የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት እና በተሽከርካሪዎች ላይ ሊጣሉ የነበሩ ቀረጦች ይገኙበታል።

ይህ አወዛጋቢ ረቂቅ በቲክቶክ መነጋገሪያነት ጀምሮ ወደ ከፍተኛ የሕዝባዊ ተቃውሞ ተቀይሯል።

የፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ መንግሥት የበርካታ ትውልድ ፖለቲከኞች ያላደረጉትን ከዘር እና ከፓርቲ ባለፈ በርካታ ኬንያውን በአንድነት እንዲቆሙ እና እንዲቃወሙ አድርጓቸዋል።

በርካታ ግብሮችን በመጫን የሚታወቁት ሩቶ ወጣቱ በአንድነት እንዲነሳባቸው ምክንያት ሆነዋል።

ተቃውሞው በጀመረበት ሰኔ 11/2016 ዓ.ም. በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ‘ታውን’ ተብሎ በሚጠራው የመዲናዋ የናይሮቢን የንግድ ማዕከልን በመቆጣጠር እያንዳንዷ እንቅስቃሴ ቀጥ እንዲል አድርገው ነበር።

ፖሊሶች በአስለቃሽ ጭስ፣ በውሃ ሊበትኗቸው ቢሞክሩም በጄ አላሉም። ፖሊሶች የሚያደርጓቸውን መተናኮሶች እና ድብደባዎችም በሞባይል ስልኮቻቸው በቀጥታ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲያሰራጩ ነበር።

ለሕዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት የነበረውን ረቂቅ ሕግ የሚመለከተውን እና የሚያጸድቀውን የአገሪቱን ምክር ቤት “ፓርላማውን እንቆጣጠር” (ኦኩፓይ ፓርላመንት) በሚል መርኅ ነበር የወረሩት።

ከዚህ ቀደም ፖለቲከኞች እና ስፖንሰር አድራጊዎች ከሚያደራጇቸው ተቃውሞዎች በተለየ መልኩ ይህ የወጣቶች እንቅስቃሴ መሰባሰቡ እና መደራጀቱ የተካሄደው በማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት ነው።

የተቃውሞው አደራጆች ጥቁር ልብስ እንዲለበስ ቢጠይቁም አንዳንዶች የተቀደዱ ጂንሶች ለብሰው መጥተዋል። የፀጉርም ሆነ የልብስ ፋሽኑም የተለየ ነበር።

 የኬንያ ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, AFP

“እኛ ጄን ዚ ነን። ራሳችንን ማሰባሰብ እና ማደራጀት ችለናል። ወጣቶች ለተቃውሞ እንዲመጡ ብቻ ሳይሆን ለምን እንደምንቃወምም ለማስተማር ቲክቶክን እንደ መድረክ እንጠቀምበታለን” ሲል አንደኛው ተቃዋሚ ዛሃ ኢንዲሙሊ ለጋዜጠኞች ተናግሯል።

አብዛኞቹ ለተቃውሞ ሲወጡ ወጣቶች ለመጀመሪያ ጊዜያቸው ነው። “ሩቶ መልቀቅ አለበት” የሚሉ ድምጾችም በርከት ብለው ተሰምተዋል።

“እኔ ለምወዳት አገሬ እገዛላታለሁ። ወላጆቼ ደክመዋል፤ አሁን ይህንን ማድረግ አይችሉም። የእኔ ተራ ነው” ሲል የ24 ዓመቱ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ኬን ማኪሊሊያ ተናግሯል።

የኬንያ የፓርላማ አባላት ረቂቁን እንዳያጸድቁት ጫና ለማሳረፍ እና ተቃዋሚዎችን ለማሳባሰብ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ "#OccupyParliament" እና "#RejectFinance Bill2024" የሚሉ ሃሽታጎችን ተጠቅመዋል።

“ይሄ የመጀመሪያ ሰልፌ ነው። የመጨረሻዬ እንደሚሆን ተስፋ አድርጋለሁ። ከዚህ በኋላ ነገሮች እንደሚለወጡ ተስፋ አደርጋለሁ” ስትል ናሴሪያና ካሱራ የተሰኘች ተቃዋሚ ተናግራለች።

ሰልፈኞቹ ወደ አገሪቱ ፓርላማ ደርሰው ለመክበብ ያደረጉት ጥረት በፖሊስ ውሃ መርጨት ቢደናቀፍም መንፈሳቸው እንደተጠናከረ ነበር።

በዚያች ዕለት ከ200 በላይ ወጣቶች የታሰሩ ሲሆን፣ ጠበቆች በፖሊስ ጣቢያዎች ተገኝተው የተወሰኑትን አስፈትተዋል። አንዳንዶቹም በፖሊስ መኪኖች አንሳፈርም እያሉ ሲያንገራግሩ ታይተዋል።

በአደባባዩ ተቃውሞ ላይ ያልተገኙት ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ መልዕክቶችን፣ ፎቶዎችን፣ ቪዲዮዎችን በማጋራት ለትግሉ አጋርነታቸውን አሳይተዋል።

ተቃውሞው ግልጽ ያለ አመራር ስለሌለው ፖሊስ ዒላማ የሚያደርጋቸውን አካላትን ለመለየት ተቸግሯል። የተቃውሞ ሰልፉን አንዳንድ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን አላሟላም በሚል ፖሊስ ቢያግደውም ተቃዋሚዎቹ በዚህ አይስማሙም።

ከዚህ ቀደም ከነበሩት ፀረ መንግሥት ተቃውሞዎች በተለየ መልኩ ዘረፋ፣ ንብረት ማውደምም ሆነ ድንጋይ መወርወር አልታየበትም። ፍጹም ጨዋነት የተሞላ ነበር። ወጣቶቹ አገር አቀፍ በሆነው ተቃውሟቸው መንግሥታቸው ላይ ጫና ማድረስ ችለዋል። የተወሰኑት ቀረጦች እንዲሰረዙም አድርገዋል።

“ኬንያውያንን አድምጠናችኋል” ሲሉ የፓርላማው የፋይናንስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኩሪያ ኪማኒ ፕሬዝዳንት ሩቶ እና የምክር ቤት አባላት በተገኙበት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

በፋይናንስ ረቂቁ ላይ የተደረጉ ለውጦች “ኬንያውያንን ከኑሮ ውድነት ጫና ለመጠበቅ የተደረጉ ናቸው” ሲሉም ኩሪያ አክለዋል።

መንግሥት በእነዚህ የቀረጥ ጭማሪዎች 2.7 ቢሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ እና አገሪቷ ያለባትን የዕዳ ጫና ለማቃለል ይውላል ሲል ይሟገታል።

ኬንያ በአሁኑ ጊዜ ያለባትን 80 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ብሔራዊ ዕዳን ለመቀነስ የተለያዩ ግብሮችን መጣል አንዱ እርምጃ ነው ይላል መንግሥት።

በተቃዋሚ ሰልፎቹ ያልተሳተፉ እና ሙሉ በሙሉ ሕጉ እንዲሰረዝ የሚጠይቁ ተቃዋሚዎች በሕዝብ ላይ የተጣለ “ቅጣት” ሲሉ ነው የጠሩት።

ረቂቅ ሕጉን እንዲሰርዙትም ለማድረግ በፕሬዚዳንት ሩቶ ላይ በቀጥታ ያነጣጠረ "#unfollowRuto" የሚል ሃሽታግ በማኅበራዊ ሚዲያዎች እየተጋራ ይገኛል።

በዚህም ተቃዋሚዎች ሕዝቡ ፕሬዚዳንቱን በኤክስ ገጻቸው እንዳይከተሏቸው እየጠየቁ ነው። ረቂቅ ሕጉ ሙሉ በሙሉ ውድቅ እስኪደረግ በመዲናዋ ናይሮቢ እንዲሁም በሌሎች ከተሞች በተቃውሟችን እንቀጥላለን ብለዋል።

 የኬንያ ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ረቂቅ ሕጉን በበርካታ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ከማጋራት በተጨማሪ የፓርላማ አባላት ላይም ጫና ለማድረስ ተሞክሯል።

የምክር ቤት አባላቱ ይህንን ሕግ ውድቅ እንዲሆን ድምጻቸውን እንዲሰጡ ለማድረግም “ኤስኤምኤስ ዩርኤምፒ” (ለፓርላማ ተወካዮቻችሁ መልዕክት ላኩ) በሚል ከስልክ ቁጥሮቻቸው ጋር ተጋርቷል።

ስቴፈን ሙሌ የተሰኙት የፓርላማ አባል ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት፣ ረቂቅ ሕጉን ውድቅ እንዲያደርጉት የሚጠይቁ 30 ሺህ መልዕክቶች በስልካቸው ደርሷቸዋል።

ሌሎች የፓርላማ አባላትም በሚደርሷቸው መልዕክቶች መጨናነቅ ምክንያት የስልክ አገልግሎታቸው ተቋርጧል ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

ለዓመታት የፀረ መንግሥት ተቃውሞዎችን ሲመሩ የነበሩት አንጋፋው የተቃዋሚ መሪ ራይላ ኦዲንጋ ከተቃውሞ ሰልፎቹ እንዲርቁ አንዳንዶች አሳስበዋል።

እሳቸውም ይህንኑ አክብረው በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ምላሽ የሰጡ ሲሆን “እኔ ዛሬ በጣም ኩሩ አባት ነኝ። መብቶቻቸውን ለማስከበር በጀግንነት ለቆሙ ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል።

 የኬንያ ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ረቂቅ የፋይናንስ ሕጉ ምን ይዟል?

ረቂቅ ሕጉ የኬንያ የ2024̀/5 በጀት አካል ሲሆን መንግሥት ገቢውን ለመጨመር በተለያዩ ምርቶች እና አገልግሎቶች ላይ ቀረጥ እና ታሪፍ መጨመርን የያዘ ነበር።

ከእነዚህም መካከል በዳቦ ላይ 16 በመቶ ተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) መጣልን ጨምሮ እንዲሁም በሞባይል ገንዘብ የማስተላለፊያ አገልግሎት ላይ ታሪፈ እና በመኪና ላይ 2.5 ቀረጥ ተካትተውበት ነበር።

ረቂቅ ሕጉ ለአካባቢ ጎጂ ናቸው ተብለው በሚታሰቡ እንደ ማሸጊያ፣ ፕላስቲክ እና ጎማ ያሉ ምርቶች ላይ ‘ኢኮ ታክስ’ እንዲጣል ሃሳብ አቅርቧል። በዚህም እንደ ህፃናት ዳይፐር፣ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያዎች፣ ኮምፒውተሮች እና ሞባይል ስልኮች ላይ ቀረጥ ይጥላል ነበር።

በአንዳንድ የፋይናንስ አገልግሎቶች እንዲሁም በውጭ ምንዛሬ ግብይቶች ላይ 16 በመቶ ቫት ለመጣል አቅዶ ነበር።

ከእነዚህም ውስጥ በዳቦ ላይ ሊጣል የነበረው 16 በመቶ ቀረጥ፣ የምግብ ዘይት፣ በፋይናንስ አገልግሎት፣ እና በተሽከርካሪዎች ላይ ሊጣሉ የነበሩ ቀረጦች እንዲሰረዙ ተደርጓል።

በተጨማሪም እንደ ህፃናት ዳይፐር፣ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያዎች፣ ኮምፒውተሮች፣ ሞባይል ስልኮች፣ በመኪና ጎማዎች እና በሞተር ሳይክሎች ላይ ሊጣል የታሰበው ቀረጥ ከረቂቁ እንዲወጣ ተደርጎ ነበር።

ሌላኛው በሞባይል የገንዘብ ማስተላለፉያ አገልግሎት ላይ የክፍያ ጭማሪ እና የኢንተርኔት ዳታ ክፍያዎች ላይ ሊደረግ የታሰበው የግብር ጭማሪ እንዲሰረዝ ሆኗል።

በተደጋጋሚ ግብሮች የተሰላቹት ኬንያውያን ይሄ በቂ አይደለም። አሁንም ቢሆን በረቂቁ የተካተቱ እንደ የመንገድ ጥገና፣ ከውጭ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ ሊጣሉ የታሰቡ ቀረጦችን አንቀበልም ብለዋል። ረቂቁ ሙሉ በሙሉ ውድቅ ይደረግም እያሉ ነው።

የወጣቶቹ ተቃውሞ የበረታባቸው ፕሬዝዳንት ሩቶ በመጨረሻም የፋይናንስ ሕጉን ሙሉ ለሙሉ ውድቅ እንዲሆን ለማድረግ ተገድደዋል። ነገር ግን የተቀሰቀሰባቸው ተቃውሞ እና ቅሬታ ቀጥሏል።