በታንዛኒያ ከተነሳው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ቢያንስ 240 ሰዎች በአገር ክህደት ተከሰሱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር ታንዛኒያ ከምርጫ ጋር በተያያዘ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ቢያንስ 240 ሰዎች በአገር ክህደት ተከሰሱ።
ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሁሉ ሐሰን በ98% ድምጽ ምርጫውን ማሸነፋቸው ተገልጿል። በምርጫው እንዲሳተፉ ያልተፈቀደላቸው ፓርቲዎች ግን ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።
በአደባባይ ድምጻቸውን ለማሰማት የወጡ ተቃዋሚዎች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር እንደተጋጩና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደተገደሉ የተለያዩ ምንጮች ጠቁመዋል።
የታንዛኒያ መንግሥት የተነሳውን የተቃውሞ መጠን አሳንሶ፤ ምርጫው ነጻ እና ፍትሐዊ ነው ብሏል።
በዳሬ ሰላም ፍርድ ቤት የቀረቡ በርካታ ሰዎች በአገር ክህደት ተከሰዋል። ቢቢሲ የተመለከተው የክስ ሰነድ እንደሚያሳየው፤ ተከሳሾቹ ምርጫውን ለማሰናከል በሚል ተቃውሞ በማነሳሳት ክስ ቀርቦባቸዋል።
ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ሞት ሊፈረድባቸው ቢችልም በታንዛኒያ የሞት ፍርድን ወደ ዕድሜ ልክ እስራት መለወጥ የተለመደ ነው።
በታንዛኒያ ለመጨረሻ ጊዜ የሞት ፍርድ ተፈጻሚ የተደረገው እአአ በ1990ዎቹ ነበር።
በአገር ክህደት ከተሰሰሱት መካከል ታዋቂዋ ነጋዴ ጄኔፈር ጆቪን ይገኙበታል።
ለተቃውሞ አደባባይ የሚወጡ ሰዎች በአስለቃሽ ጭስ እንዳይጎዱ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲገዙ ስታበረታታ ነበር በሚል ተከሰዋል።
የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችም ከተከሳሾቹ መካከል ናቸው።
ፕሬዝዳንት ሳሚያ ቃለ መሐላ ሲፈጽሙ የተነሳውን ተቃውሞ ኮንነው የውጭ አገራት ዜጎች ጣልቃ ገብነት አለበት ብለዋል።
በታንዛኒያ የሚኖሩ ኬንያውያን የጥቃት ዒላማ በመደረጋቸው መስጋታቸውን ገልጸዋል። የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሙሳይላ ሙዳቬዲ ኬንያውያን ከለላ እንዲሰጣቸው አሳስበዋል።
ወደ 250,000 የሚጠጉ ኬንያውያን በታንዛንያ ይኖራሉ።
የታንዛኒያ ፖሊስ ቃል አቀባይ "አንዳንድ የውጭ አገራት ዜጎች ወንጀል ለመፈጸም እና ሁከት ለማነሳሳት በማቀድ በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር ተሻግረዋል" ብለዋል።
የተወሰኑ ኬንያውያን መገደላቸው፣ መደብደባቸው እና መታፈናቸው ከተሰማ በኋላ በርካታ ኬንያውያን ቤተሰቦች ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በዳሬ ሰላም መምህር የነበረው ኬንያዊ ጆን ኦጉቱ ምግብ ለመግዛት ሲወጣ በታንዛኒያ ፖሊሶች መገደሉን ታላቅ እህቱ ለቢቢሲ ተናግራለች።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንዳሉት የመምህሩን አስከሬን ለማግኘት አልተቻለም።
በሙሂምቢሊ ሆስፒታል የሚሠሩ ዶክተር ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ በተቃውሞ ወቅት የተገደሉ ሰዎችን አስከሬን የከተማው ማዘጋጃ ቤት ሰብስቧል።
የኬንያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቤተሰቦቻቸው ያሉበት ሁኔታ ያሰጋቸው ሰዎች የስም ዝርዝር እና ስልክ ቁጥር እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
በተለይም በግል ትምህርት ቤቶች ያስተምሩ የነበሩ ኬንያውያን መምህራን አገሪቱን ጥለው እየሸሹ ነው።
የምርጫ ታዛቢዎች ሒደቱ ዴሞክራሲያዊ መንገድን የተከተለ አይደለም ሲሉ ተችተዋል። መንግሥት ግን ይህን አስተባብሏል።
ፕሬዝዳንት ሳሚያ ዋነኛ የአገሪቱ ተቃዋሚዎች በምርጫው እንዲሳተፉ አልፈቀዱም።
በዓለ ሲመታቸው የተካሄደው በዶዶማ በሚገኝ ወታደራዊ መቀመጫ ነው።
ከወራት በፊት በአገር ክህደት የተከሰሱት ተቃዋሚው ቱንዱ ሊሱን የፍርድ ቤት ሒደት ለመከታተል ዳሬ ሰላም የተገኙ ኬንያውያን ላይ የደረሰውን ስቅይት ተከትሎ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ሻክሯል።
ታዋቂው ኬንያዊ የመብት ተሟጋች ቦኒፌስ ምዋንጊ እና ኡጋንዳዊቷ የመብት ተሟጋች አጋታር አቱሀሬ ለቀናት ታፍነው ወሲባዊ ጥቃት እና ስቅይት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል።
ታንዛኒያ ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣች ወዲህ ገዢው ፓርቲ ሲሲኤም የአገሪቱን ፖለቲካ እና መንበረ ሥልጣን ተቆናጥጦ ቆይቷል።
ፕሬዝዳንት ሳሚያ በአውሮፓውያኑ 2021 የመጀመሪያዋ ሴት የአገሪቱ መሪ ሆነው ሲሾሙ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ያመጣሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎባቸው ነበር።
ከጆን ማጉፉሊ ሞት በኋላ ሥልጣኑን የተረከቡት ሳሚያ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተቃዋሚዎች ላይ የሚያደርሱት ጫና እየበረታ መጥቷል።















