በታንዛኒያ ምርጫ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሲያሸንፉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በታንዛኒያ ምርጫ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሲያሸንፉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ።
ላለፉት ሦስት ቀናት በታንዛኒያ የቀጠለውን ተቃውሞ ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ አስታውቋል።
ተቃውሞው ቢቀጥልም ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱልሁ ሐሰን 98% ድምጽ በማግኘት ምርጫውን እንዳሸነፉ ተገልጿል።
የኢንተርኔት አገልግሎት ስለተቋረጠ የተገደሉ ሰዎችን ቁጥጥር በትክክል ለማወቅ አልተቻለም።
የተቃዋሚ ፓርቲው ቻዳማ ቃል አቀባይ ለኤኤፍፒ እንደገለጹት፤ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በተነሳው ግጭት "ወደ 700 ሰዎች ገደማ" ተገድለዋል። የቢቢሲ ዲፕሎማቲክ ምንጮች ደግሞ "ቢያንስ 500 ሰዎች" መገደላቸውን ገልጸዋል።
የታንዛኒያ መንግሥት የተነሳው ሁከት እምብዛም ሰፊ እንዳልሆነ ገልጿል። የተጣለው የሰዓት ዕላፊ ገደብ እንዲራዘም ተወስኗል።
ምርጫው ፍትሐዊ አይደለም በሚል ተቃውሟቸውን ለማሰማት አደባባይ ከወጡት አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው።
ዋነኛ ተቃዋሚዎችን ከምርጫው በማገድ መንግሥት ዴሞክራሲዊ ሥርዓትን አፍኗል ሲሉ ድምጻቸውን አሰምተዋል።
የፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱልሁ ሐሰን የማሸነፍ ዕድል እንዲሰፋ የታንዛኒያ ዋነኛ ተቃዋሚ ሲታሰሩ ሌላኛው ተቃዋሚ ከምርጫው ታግደዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የታንዛኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሐሙድ ኮምቦ "ተቃውሞው በውስን ቦታዎች ብቻ ነው። ንብረት ወድሟል። የፀጥታ ኃይሎች በአፋጣኝ እርምጃ ወስደዋል" ብለዋል።
ኢንተርኔት የተቋረጠው "ዝርፊያን ለመከላከል" እንደሆነ ሚኒስትሩ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ጋዜጠኞች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ትክክለኛ የሟቾችን ቁጥር ለማወቅ ተቸግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አብዛኞቹ ሆስፒታሎች መረጃ ለመስጠት ባይፈቅዱም፤ በዳሬ ሰላም የሚገኝ ሆስፒታል ካለፈው ሐሙስ አንስቶ በተጎጂዎች እንደተሞላ እና የተገደሉ ሰዎች ቁጥርም ከፍተኛ እንደሆነ የቢቢሲ ምንጮች ጠቁመዋል።
የቻዴማ ፓርቲ አባል "ምስክር በሌለበት ሌሊት ላይ ግድያዎች እየተፈጸሙ ስለሆነ ለሕይወቴ እሰጋለሁ" ብለዋል።
የቻዴማ የውጭ ጉዳዮች ኃላፊ ጆን ኪቶካ "የፀጥታ ኃይሎች መሪዎቻችን ላይ አነጣጥረዋል። ከአገር የሸሹም አሉ። ያለ ተጠያቂነት ግድያ መፈጸማቸውን ቀጥለዋል" ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ከምርጫው በፊት ተቃዋሚዎች፣ ጋዜጠኞች እና የሲቪል ማኅበራት ሠራተኞች ዕገታ፣ ድብደባ እና ዛቻ ሲደርስባቸው እንደነበር ፖለቲከኛው ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የታንዛኒያ የፀጥታ ኃይሎች "አላስፈላጊ ኃይል እንዳይጠቀሙ" አሳስቧል።
ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ እና ኖርዌይ ባጋራ ባወጡት መግለጫ "የንግግር ነጻነት ይከበር" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከፊል ራስ ገዝ በሆችው ዛንዚባር የሲሲኤም ፓርቲ መሪ የሆኑት ፕሬዝዳንት ሑሴን ውዋይኒ 80% ድምጽ በማግኘት አሸንፈዋል።
ታንዛኒያ ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣች ወዲህ ገዢው ፓርቲ ሲሲኤም የአገሪቱን ፖለቲካ እና መንበረ ሥልጣን ተቆናጦ ቆይቷል።
ፕሬዝዳንት ሳሚያ በአውሮፓውያኑ 2021 የመጀመሪያዋ ሴት የአገሪቱ መሪ ሆነው ሲሾሙ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ያመጣሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎባቸው ነበር።
ከጆን ማጉፉሊ ሞት በኋላ ሥልጣኑን የተረከቡት ሳሚያ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተቃዋሚዎች ላይ የሚያደርሱት ጫና እየበረታ መጥቷል።
ዋነኛው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ቱንዱ ሊሱ ታስረው በአገር ክህደት ተከሰዋል። ፖለቲከኛው ክሱን አስተባብለዋል።
ከታሰሩት ዋነኛ ተቃዋሚ በተጨማሪ የፕሬዝዳንቷ ግንባር ቀደም ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብሎ የነበረው ሉሀጋ ማፒና "ከሕጋዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘ" ከውድድሩ ውጪ ተደርገዋል።
ከፕሬዝዳንት ሳሚያ ጋር እንዲፎካከሩ የተፈቀዳላቸው እምብዛም ዕውቅና የሌላቸው ስድስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ብቻ ናቸው።
ከምርጫው አስቀድሞ የመብት ተሟጋቾች እየተባባሰ የመጣውን የመንግሥት አፈና ኮንነዋል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣው ሪፖርት፤ የዘፈቀደ ዕገታ፣ ስወራ፣ ስቅይት እና ግድያ እየተፈጸመ መሆኑን ያሳያል።















