ባይደን ማሪዋና ይዘው በመገኘታቸው ለታሰሩ ይቅርታ አደረጉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አነስተኛ መጠን ያለው ማሪዋና በመያዝ በፌዴራል ደረጃ የተከሰሱ አሜሪካውያንን በሙሉ ይቅርታ የሚያደርግ ትዕዛዝ አወጡ።
በአብዛኛዎቹ ጥፋተኞች ጉዳያቸው በግዛት ደረጃ ስለሚታይ ውሳኔው አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ብቻ ይመለከታል ተብሏል።
ፕሬዝዳንቱ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት አደንዛዥ እጽን ህጋዊ ለማድረግ የገቡትን ቃል ከመፈጸም ግን ተቆጥበዋል።
በቅርቡ በተደረገ የህዝብ አስተያየት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አሜሪካዊያን አደንዛዥ እጽ ህጋዊ እንዲሆን ይደግፋሉ።
“ብዙ ግዛቶች የማይከለክሉት ቢሆንም ማሪዋና መያዝ ሰዎችን ወደ ማረሚያ ቤት እያጎረ ይገኛል” ብለዋል ባይደን በመግለጫቸው።
ከካናቢስ ጋር በተያያዘ ለእስር ከሚዳረጉት መካከል አብዛኛዎቹ አነስተኛ ቁጥር ካላቸው ማኅበረሰብ አባላት የመጡ መሆናቸውንም አክለዋል።
ባይደን በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት እአአ በ1994 አደንዛዥ እጽ በያዙ ሰዎች ላይ ቅጣት የሚያጠናክር ህግ እንዲጸድቅ ሃሳብ በማቅረባቸው ተተችተዋል።
“በፌደራል ማረሚያ ቤት አነስተኛ ማሪዋና በመያዝ በፌደራል ማረሚያ ቤት የሚገኝ ግለሰብ የለም” ሲሉ አንድ የኋይት ሃውስ ባለስልጣን ተናግረዋል።
ባይደን አክለውም ይቅርታው ከክስ መዝገብ ላይ በመፋቅ ግለሰቦች “ለሥራ ዕድል፣ ቤት እና ትምህርት ተጠቃሚነት አላስፈላጊ እንቅፋት መሆኑን” ያስቀራል ብለዋል።
እንደባለስልጣናት ከሆነ 6500 የሚሆኑና አነስተኛ ማሪዋና በመያዝ በፌደራል ማረሚያ ቤት የሚገኙ ሰዎች ከይቅርታው ተጠቃሚ ይሆናሉ።
ሁሉም ግዘቶችም ተመሳሳይ ውሳኔ እንዲያስተላልፉ ጥሪ እንደሚያቀርቡም ተናግረዋል።
ካናነቢስ በፌደራል ህግ ውስጥ እንዴት መታየት እንዳለበት ለመወሰን ፍትህ እና የጤና ሚንስትሮች ጉዳዩን እንዲመረምሩ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
“ማሪዋናን ከሄሮይን እኩል እናስቀምጠዋለን። ቦታው ከፌንታኒልም በላይ ነው። ይህ ተገቢ አይደለም” ብለዋል።
ለመዝናኛነት ጥቅም ላይ የሚውል ማሪዋና በዋሽንግተን ዲሲ እና በ19 ግዛቶች ህጋዊ ነው። ለህክምና እንዲውል ደግሞ 37 ግዛቶች እና ሦስት የአሜሪካ አካባቢዎች ፈቅደዋል።
በፌደራል ደረጃ ግን ህጋዊ አልሆነም።
ውሳኔውን ተከትሎ ገበያው በ200% ማደጉን አንድ የአደንዛዥ እጽ መሸጫ አስታውቋል።
ዶናልድ ትራምፕ በመጨረሻ ቀን የስልጣን ዘመናቸው 12 ማሪዋና ተከሳሾችን በይቅርታ ለቅቀዋል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በባይደን በቀረበው ህግ መሠረት ሦስት ጊዜ ማሪዋና ይዘው በመገኘታቸው ዕድሜ ልክ የተፈረደባቸው ናቸው።












