ኢሰመኮ በጋምቤላ በሠራተኞቼ ላይ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ደረሰ አለ

የፎቶው ባለመብት, Gambela region
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጋምቤላ ጽህፈት ቤቱ በሚገኙ ሠራተኞቹ ላይ ዛቻ እና ማስፈራሪያ መፈጸሙን ገለጸ።
ኮሚሽኑ ሐሙስ መስከረም 26/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ መስከረም 25 በቡድን ሆነው ወደ ጽ/ቤቱ የመጡ ሰዎች በኢሰመኮ ባልደረቦች ላይ ዛቻ፣ ማስፈራሪያ እና የተለያዩ የጥፋት ድርጊቶችን መፈጸማቸውን ገልጿል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የኮሚሽኑ ሠራተኞች በአዋጅ የልዩ ጥበቃ መብት የሚደረግላቸው እንደሆነ እና የተፈጸመው ድርጊት ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጸዋል።
“ኮሚሽኑ የክትትል እና የምርመራ ሥራውን በሚያከናውንበት ወቅት የተለያዩ ተግዳሮቶች የሚገጥሙት ቢሆንም፤ . . . በሠራተኞች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በክልሉ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ምልክታ የሚጥል በመሆኑ የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥት ተባብረው በአፋጣኝ እንዲያስቆሙ ኮሚሽኑ በጥብቅ ያሳስባል” ብለዋል።
ኮሚሽኑ ይህንን ማስፈራሪያ እና የጥፋት ድርጊት ያላቸውን ተግባራት እነማን እንደፈጸሙ ያለው ነገር ባይኖርም፣ በጋምቤላ ያጋጠመውን ክስተት ተከትሎ ሪፖርት ካወጣ በኋላ የጋምቤላ ክልል መንግሥት ሪፖርቱ ሚዛናዊነት የጎደለው በመሆኑ እንደማይቀበለው እና እንደሚያወግዘው መግለጹ ይታወሳል።
ኢሰመኮ ሰኔ 07/2014 ዓ.ም. በጋምቤላ ከተማ እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን እና የጋምቤላ ነጻነት ግንባር ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ኮሚሽኑ በጋምቤላ ክልል የፀጥታ ኃይሎች እና በታጣቂ ቡድኖቹ ተፈጽሟል ያላቸውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት አስመልክቶ ያከናወነውን የምርመራ ሪፖርት መስከረም 18/2015 ዓ.ም. አውጥቶ ነበር።
በኮሚሽኑ ሪፖርት ታጣቂ ቡድኖቹ ጥቃት ካደረሱ በኋላ ባሉት ሁለት ተከታታይ ቀናት ውስጥ የክልሉ ልዩ ኃይሎች በከተማው በሲቪል ሰዎች ላይ ጥቃት እንዳደረሱ አመልክቷል።
ኢሰመኮ እንዳለው የዚህን ሪፖርት መውጣት ተከትሎ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች እና በመገናኛ ብዙኃን ላይ የተሳሳተ እና ዛቻን ያዘሉ መረጃዎች ሲሰራጩ፤ እንዲሁም በኢሰመኮ ባልደረቦች ላይ ያነጣጠሩ የጥላቻ መልዕክቶች ሲዘዋወሩ ቆይተዋል።
የጋምቤላ ክልል የኢሰመኮን ሪፖርት በተመለከተ መስከረም 22/2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የኮሚሽኑ ሪፖርት ግኝት እጅግ የተጋነነ እና በወቅቱ የነበረውን ሐቅ ያላገናዘበ፣ መረጃ የተሰበሰበው ከታጣቂ ቡድኑ፣ ከህወሓት ደጋፊዎች እና በወንጀሎች ሲጠረጠሩ ከነበሩ ግለሰቦች የተወሰደ ነው ብሏል።
በዚህ እና በሌሎች ምክንያቶች የክልሉ መንግሥት ሪፖርቱ ኃላፊነት የጎደለው በመሆኑ እንደማይቀበለው ገልጾ ነበር።
ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ የኦሮሞ ነጻነት ግንባርና የጋምቤላ ሕዝብ ነጻነት ግንባር የተባሉት ታጣቂ ቡድኖች በጋምቤላ ክልል ዋና ከተማ ላይ ጥቃት ሰንዝረው እንደነበር ይታወሳል።
አማጺያኑ ለተወሰነ ሰዓት ከፊል የከተማዋን ክፍል ተቆጣጥረው የነበረ ሲሆን፣ የፌደራል እና የክልሉ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ ታጣቂዎቹን ከከተማዋ ለማስወጣት ችለዋል።
ይህንንም ተከትሎ በአማጺያኑ እና በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች መካከል ተከስተው በነበሩ ግጭቶች ከሃምሳ በላይ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ተዘግቧል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንም ጥቃቱን ተከትሎ በጋምቤላ ከተማ ስላጋጠሙ ክስተቶች ከወራት በኋላ፣ ባለፈው ሳምንት ባወጣው ሪፖርት ላይ የፀጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጪ እርምጃ ወስደዋል ሲል ወቅሷል።












