ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ይፋ አደረገ

በሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የሚመራው ጥምረት ኃላፊዎች

የፎቶው ባለመብት, Safaricom Ethiopia

የኬንያው ግዙፍ የቴሌኮም ኩባንያ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በዛሬው ዕለት መስከረም 26/2015 ዓ.ም. በአገሪቱ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ይፋ አደረገ።

ኩባንያው በነሐሴ ወር ከአዲስ አበባ በ500 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የድሬዳዋ ከተማ ነበር የሙከራ አገልግሎቱን የጀመረው።

በቀጣይ በነበሩ ሳምንታት ደግሞ በአስር ከተሞች ማለትም በሐረር፣ በሐረማያ፣ በአዳማ፣ በባሕር ዳር፣ በቢሾፍቱ፣ በደብረ ብርሃን፣ በጎንደር እና በሌሎች ከተሞች የሙከራ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።

ከእነዚህ ሙከራዎች በኋላ ዛሬ በይፋ አገልግሎቱን በአዲስ አበባ መጀመሩን ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ያስታወቀ ሲሆን፣ በዚህ ሥነ ሥርዓትም ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ ተገኝተዋል።

በቅርቡ የነበረውን የኬንያ ምርጫ ያሸነፉት ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ለመጀመሪያ ጉብኝታቸው አዲስ አበባ ገብተዋል።

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዛሬ በመላው አገሪቱ የኔትወርክ አገልግሎት ከጀመረም በኋላ ለተጨማሪ 14 ከተሞች አገልግሎቱን እንደሚያዳርስም ተገልጿል።

“በሁለገብ የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃዳችን ግዴታዎች መሰረት በከተማ የደንበኞቻችን ሙከራዎቻችን የምንቀጥል ሲሆን፣ ለተጨማሪ ከተሞች እና የተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ኔትወርካችንን እና አገልግሎታችንን ማቅረብ እንቀጥላለን” ሲሉ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አንዋር ሱሳ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለ125 ዓመታት በላይ በመንግሥት የልማት ድርጅት በብቸኝነት ተይዞ የነበረውን የቴሌኮም ዘርፍ ክፍት በማድረግ የቴሌኮም ፈቃድ የሰጠችው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር።

በኢትዮጵያ የቴሌኮም ገበያ ለመሰማራት በተደረገው ዓለም አቀፍ ጨረታ በኬንያው ሳፋሪኮም የሚመራው ጥምረት በ850 ሚሊዮን ዶላር ማሸነፉ ይታወሳል።

ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ የተሰኘው ይህ ጥምረት በዘርፉ አሉ የሚባሉ ስመ ጥር የቴሌኮም ኩባንያዎችን እና ተቋማትን በቅንጅት የያዘ ሲሆን፣ እነዚህም ሳፋሪኮም፣ ቮዳኮም ግሩፕ፣ ቮዳፎን ግሩፕና ሱሚቶሞ ኮርፖሬሽን እንዲሁም ሲዲሲ ግሩፕ የተካተቱበት ነው።

ዋነኛው የአገሪቱ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ኢትዮ ቴሌኮም 40 በመቶ ድርሻውን ለውጭ ባለሀብቶች፣ 5 በመቶውን ለኢትዮጵያውያን እና 55 በመቶውን በመንግሥት ይዞታ ይቀጥላል ተብሎ ነበር። 

ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች አንዱ የሆነው ኢትዮቴሌኮም ገቢው ትርፋማ ከሚባሉ ድርጅቶች አንዱ ቢሆንም ከሌሎች የቀጠናው ኩባንያዎች ጋር ሲወዳዳር ዝቅተኛ ነበር ይላሉ በዘርፉ ያሉ ተንታኞች።

ኢትዮጵያ ኢትዮቴሌኮምን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ድርሻ ለመሸጥ የወሰነችው በዋነኝነት ያላትን ከፍተኛ ዕዳ ለመክፈል እንደሆነ ተንታኞች የሚናገሩ ሲሆን፤ በተጨማሪነት የቴሌኮምን ተደራሽነት ለመጨመርና አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ እንደሆነም ይጠቀሳል።

ከሳፋሪኮም ከሚመራው ጥምረት በተጨማሪ በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ ለመግባት የሚያስችል ሁለተኛ ፈቃድ እንደሚሰጥ መንግሥት መግለጹ ይታወሳል።