የተሰናባቹ 2013 ዓመት ዓበይት ምጣኔ ኃብታዊ ክስተቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images/BBC
ኢትዮጵያ 2013ን ተሰናብታ አዲሱን ዓመት ልትቀበል የቀራት ጥቂት ቀናት ናቸው። ተሰናባቹን ዓመት ዘወር ብለን በምናይበት ወቅት አገሪቷ በጦርነት ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿ የተቀጠፉበት፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቤት አልባ ሆነው በችግር ውስጥ የሚገኙበት፣ ከፍተኛ የዋጋ ንረት የብዙዎችን ናላ እያዞረ ባለበት ነው ያሳለፉት።
ፈታኝ በሚባል የታሪክ ሂደት ውስጥ ያለችው አገሪቷ በምትሸኘውም ዓመት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጸጥታ ምክር ቤት ዋነኛ ርዕሰ ጉዳይ፣ የኃያላኑ መንግሥታት መነጋገሪያ፣ በባለስልጣናቷ ላይ የጉዞ ዕቀባ የተጣለባትና ከጫፍ ጫፍ ያሉ የዓለም ሚዲያዎች ዋና ርዕስም ሆናለች።
አገሪቷ ከትግራይ ጦርነት ጋር ተያይዞም በረሃብና በመብት ጥሰቶች ስሟ በተደጋጋሚ የሚጠቀስ ሆኗል። ከጦርነት በተጨማሪ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አገሪቷ ላይ ጫና ያሳደረ ከመሆኑ አንፃር በርካታ ጋሬጣዎች የተደቀኑበት ዓመት ሆኖ ማለፉ አሌ አይባልም።
ተሰናባቹ ዓመት ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት የታየበት፣ ከምጣኔ ሀብት ቀውሰ ጋር በተያያዘ ኤምባሲዎች የተዘጉበት፣ አገሪቷ የመገበያያ ገንዘብ ኖት የቀየረችበት፣ አዲስ የቴሌኮም ፈቃድ የተሰጠበት ወቅት ነው።
ከዚህም በተጨማሪ በርካታ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱ መመሪያዎች የወጡበት እንዲሁም ኢትዮጵያ ለአስርት ዓመታት ሲጠበቅ የነበረው የንግድ ሕጓን ያሻሻለችው በተሰናባቹ ዓመት ነው።
ለመሆኑ የተሰናባቹ ዓመት ዓበይት የምጣኔ ሀብት ክስተቶች ምን ነበሩ? እንዲህ ቃኝተናቸዋል።
የብር ኖቶች ቅያሪ
ኢትዮጵያ የ2012 ዓ.ምን የምጣኔ ሀብት ማሻሻያዋን የጀመረችው ከሁለት አስር ዓመታት በላይ ስትገለገልባቸው የነበሩ የ10፣ የ50፣ እና የ100 ብር የገንዘብ ዓይነቶችን በመቀየርና አዲስ ብር ኖቶችን ይፋ በማድረግ ነው።
በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የባለ ሁለት መቶ ብር ኖትም አሳትማለች። አገሪቷ ነባሮቹን የብር ኖቶች ለመቀየር ሌላ ወጪ ሳይጨምር ለህትመት ብቻ 3.7 ቢሊዮን ብር ማውጣቷን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ አስታውቀዋል።
አገሪቱ በዋነኝነት ወደ ቅያሪ የገባችው ባንኮች የገጠማቸውን የገንዘብ ችግር ለመቅረፍና ቁጠባቸውን እንዲያሳድግ፣ ሕጋዊ ያልሆነ የገንዘብ ዝውውርን ከኢኮኖሚው እንቅስቃሴ እንዲወገድ፣ የዋጋ መረጋጋት እንዲኖር፣ የመንግሥት ገቢ እንዲያድግ ያስችላል በሚል ነው።
በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ከባንክ ውጪ በመኖሩ ከፍተኛ የሆነ የጥሬ ገንዘብ እጥረት (ሊኩዊዲቲ) ከማጋጠሙ ጋር ከመሆኑ ተያይዞም ቅያሪው ይህንንም እንደሚቀርፍ ታምኗል። ከቅያሪው ጋር ተያይዞ ከወጡ መመመሪያዎች ጋር በተያያዘ አንዳንድ ለውጦችም ታይተዋል።
በአንድ ሰው እጅ ሊቀመጥ የሚችለው የገንዘብ መጠን በ1.5 ሚሊዮን ብር መወሰኑ፣ ግለሰቦች ከባንክ በቀን ማውጣት የሚችሉት ከፍተኛ የገንዘብ መጠን 200 ሺህ ብር፣ እንዲሁም ኩባንያዎች በጥሬ ገንዘብ ማውጣት የሚችሉት 300 ሺህ ብር ገደብ መመሪያዎች ጥያቄ ያጫሩ ሆነው አልፈዋል።
ብሔራዊ ባንክ በወቅቱ እንዳስታወቀው የታተመው ብር በኢኮኖሚው ውስጥ ከሚዘዋወረው በበለጠ እንዲሆንና ለመጠባበቂያም እንዲሆን 262 ቢሊዮን ብር ታትሟል።
በ1983 ዓ.ም የታተመው የብር መጠን ስምንት ሚሊዮን ብር ብቻ የነበረ ሲሆን የዘንድሮው በአገሪቱ የብር ቅያሪ ታሪክ ከፍተኛ ተብሎ ተመዝግቧል።
የትግራይ ጦርነት ያስከተለው ቀውስ
በጥቅምት መጨረሻ አካባቢ በትግራይ ክልል የተከሰተው ደም አፋሳሽ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከመግደሉ በተጨማሪ ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊና የምጣኔ ሀብት ቀውስ አስከትሏል።
ጦርነቱ እስካሁን ድረስ አገሪቷን ምን ያህል እንዳስወጣት ይፋዊ መረጃ ባይኖርም፣ በትሬዲንግ ኢኮኖሚክስ ትንበያ መሰረት ወታደራዊ ወጪዋ በመጪው ታኅሣሥ ወር መጨረሻ ላይ ወደ 502 ሚሊዮን ዶላር ሊደርስ ይችላል ተብሏል። ባለፈው ዓመት ወጪዋ 460 ሚሊዮን ዶላር ነበር።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝም ጦርነቱ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር ከአገሪቱ ግምጃ ቤት አስወጥቷል ብለዋል። አገሪቱ ለጦርነቱ መዋዕለ ንዋይዋን ከማፍሰሷ በተጨማሪ ከትግራይ ክልል ታገኝ የነበረውን ገቢም አጥታለች።
ጦርነቱ በተጀመረ በወራት ውስጥ ከትግራይ ክልል በሦስት ወራት ውስጥ መሰብሰብ የነበረበት ሁለት ቢሊዮን ብር አለመገኘቱን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጥር ወር መጨረሻ ላይ የስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃጸሙን ለሐዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው መረጃ መሰረት በበጀት ዓመቱ ለመሰብብሰብ ከታቀደው 290 ቢሊዮን ብር ውስጥ በትግራይ ክልል ለማግኘት የታሰበው 7.8 ቢሊዮን ብር እንደነበር አስረድቷል። ከጦርነቱ በፊት በነበሩት ሦስት ወራት 1.8 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሰብስቧል።
የትግራይ ክልል ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ውስጥ የምትጠቀስ ስትሆን ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ በየዓመቱ ወጪ ንግድ ከምታደርጋቸው ምርቶች ውስጥ ዘጠኝ በመቶ የክልሉ ድርሻ ነው።
የኢትዮጵያ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ባለፈው ዓመት በ2020 ከነበረበት 6 በመቶ በዚህ የአውሮፓውያን ዓመት በ2021 ሁለት በመቶ ብቻ እንደሚያድግ ተገምቷል። ይህም በሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ ከታየው በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ የአይኤምኤፍ መረጃ ያሳያል።
ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት
በኢትዮጵያ ውስጥ እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት የበርካታ ከተሜን ህይወት እየፈተነና የማይወጡት ተራራ ሆኖባቸዋል። የኑሮ ውድነት አመላካች የሆነው የዋጋ ግሽበት በነሐሴ ወር ወደ 30.4 በመቶ አሻቅቧል።
የኢትዮጵያ ስታስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያሳየው በነሐሴ ወር የምግብ ዋጋ ግሽበት ከ32 በመቶ አገሪቷ በአስርት ዓመታት አይታው ወደማታውቀው 37.6 በመቶ ደርሷል።
ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦችን የዋጋ ግሸበት በምናይበት ወቅት ከ19 በመቶ ወደ 20.8 በመቶ አሻቅቧል።
የዋጋ ግሽበቱ ጦርነት በሚካሄድባቸውና ምንም ዓይነት የመሠረታዊ አገልግልቶች በሌለባቸው እያሻቀበ ሲሆን የመሠረታዊ ሸቀጦች መመናመኑን ከስፍራው የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።
ለምሳሌ ያህል ጥር መጨረሻ ላይ በነበረው መረጃ መሰረት የምግብ ዋጋ ግሽበቱ በትግራይ ከ36 በመቶ በላይ ነበር።
የአገሪቷ የዋጋ ግሽበት ከሦስት አስርት አሃዝ በላይ መሆኑ መሠረታዊ በሚባሉ ሸቀጦችም ዋጋ እያናረው ሲሆን በዜጎች ላይም ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጫና እያሳደረ ነው።
ኢትዮጵያ ለዓመታት የነበራት የተዛባ የንግድ ሥርዓት በተለይም የወጪና የገቢ ንግድ አለመመጣጠን፣ ጦርነትና አለመረጋጋት፣ የብር መዳከም የፈጠረው ግሽበት፣ የወጪ ንግድ መቀዛቀዝ፣ የውጪ ምንዛሪ እጥረት ተደራርበው ለዋጋ ንረቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረጉ ይገኛሉ።
ከዚህም በተጨማሪ በመላው ዓለም የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በምጣኔ ሀብቱ ቀውስ ላይ ጫና እያሳደረ ይገኛል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሪቱ የሚታየውን የዋጋ ግሽበት ወደ አንድ ነጠላ አሀዝ አውርዶ የዋጋ መረጋጋት ለማምጣት እየጣረ የሚገኝ ሲሆን ከሰሞኑም የተወሰኑ መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦችን ላልተወሰነ ጊዜ ከቀረጥና ታክስ ነጻ ማድረጉን አስታውቋል።
ከነሐሴ መጨረሻም ጀምሮ የምግብ ዘይት፣ ስኳርና ሩዝ ከውጭ ሲገቡም ሆነ በአገር ውስጥ ግብይት ሲፈጸምባቸው ከቀረጥና ታክስ ሙሉ በሙሉ ነፃ ሲሆኑ ስንዴ ከውጭ ሲገባ ከቀረጥና ታክስ ነፃ እንዲሆን ተወስኗል።
ፓስታ እና ማኮሮኒ ከውጭ ሲገቡም ሆነ በአገር ውስጥ ግብይት ሲፈጸም ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ እንዲሆኑ፣ እንዲሁም የዶሮ እንቁላል ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነጻ እንዲሆን ተወስኗል።
የውጭ ምንዛሪ ዋጋ መናር
ለዓመታት የአገሪቱ አንገብጋቢ ችግር ሆኖ የዘለቀው የውጭ ምንዛሪ እጥረት በዘንድሮው ዓመትም በከፍተኛ ሁኔታ ተባብሷል።
በዓመታት ከፍተኛ በሚባል ሁኔታ ጭማሪ እያሳየ የመጣው የምንዛሪ ተመን ንሮ ይፋዊ በሆነው የባንክ ግብይት መሰረት አንድ ዶላር በ45.6 ብር እየተመነዘረ ይገኛል።
በትይዩ ወይም በተለምዶ ጥቁር ገበያ በሚባለው ገበያ የምንዛሪ ተመን ደግሞ አንድ ዶላር በ70 ብር አካባቢ እየተመነዘረ ሲሆን ከመደበኛው ገበያ ጋር ያለው ልዩነት ከ20 ብር በላይ መሆኑ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችን ስጋት ላይ የጣለ ክስተት ሆኗል።
በተለይም አገሪቷ የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ ፍላጎት የሚመራ ሥርዓት እንዲዘረጋ ከመወሰኗና ከገበያው ጋር ለማቀረራረብ እየሰራች ባለበት ወቅት ይህንን ያህል ልዩነት መፈጠሩ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ጥያቄ ሆኗል።
የብር የንምዛሪ ተመን ማሽቆልቆል በትግራይ ክልል ከተነሳውና በአማራና አፋር ክልል ከተዛመተው ጦርነት ጋር ተያይዞ አገሪቷ ካጋጠማት አለመረጋጋት በተጨማሪ የብር ተገቢውን ዋጋ መያዝ (ዲቫሉዌት) የማድረግ ጥረትና የንግድ ሚዛን ጉድለት እንደሆነም ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በተለይም የአገሪቷ የተዛባ የንግድ ሥርዓት ጋር በተያያዘ እየታየ ያለው የወጪና የገቢ ንግድ አለመመጣጠን በተጨማሪ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ለዓመታት መንግሥት ብር ከዶላር ጋር ያለው ምንዛሪ ተመን መዳከም እንዳለበት ከመጎትጎታቸው ጋር ተያይዞ ይህ ተግባራዊ መሆኑ ብሩን አዳክሞታል።
አገሪቱ በዓመት ወደ 14 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ እቃዎችን ከውጭ የምታስገባ ሲሆን 3.4 ቢሊዮን ዶላር ብቻ የሚያወጣ ምርቶችን ወደ ውጪ ትልካለች። ምንም እንኳን ይህ አሀዝ ጉድለት ቢታይበትም የአገሪቱ የወጪ ንግድ ገቢ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር ሲሻገር የመጀመሪያው ነው።
አዲስ የቴሌኮም ፈቃድ
ኢትዮጵያ ለ126 ዓመታት ያህል በመንግሥት ልማት ስር የነበረውን የቴሌኮም ኢንዱስትሪ ክፍት በማድረግ የቴሌኮም ፈቃድ የሰጠችው በዘንድሮው ዓመት ነው።
በኢትዮጵያ የቴሌኮም ገበያ ለመሰማራት በተደረገው ዓለም አቀፍ ጨረታ በኬንያው ሳፋሪኮም የሚመራው ጥምረት በ850 ሚሊዮን ዶላር አሸንፏል።
ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ የተሰኘው ይህ ጥምረት በዘርፉ አሉ የሚባሉ ስመ ጥር የቴሌኮም ኩባንያዎችንና ተቋማትን በቅንጅት የያዘ ሲሆን እነዚህም ሳፋሪኮም፣ ቮዳኮም ግሩፕ፣ ቮዳፎን ግሩፕና ሱሚቶሞ ኮርፖሬሽንና ሲዲሲ ግሩፕ የተካተቱበት ነው።
ጥምረቱ በኢትዮጵያ የሚሰጠውን የቴሌኮም አገልግሎት ከመጪው ጥር 2014 ዓ.ም በኋላ ይጀምራል ተብሏል።
ዋነኛው የአገሪቱ አገልግሎት ሰጪ ኢትዮ ቴሌኮም 40 በመቶ ድርሻውን ለውጪ ባለሀብቶች፣ 5 በመቶውን ለኢትዮጵያውያን እና 55 በመቶውን በመንግሥት ይዞታ ይቀጥላል ተብሏል።
ኢትዮጵያ ኢትዮቴሌኮምን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ድርሻ ለመሸጥ የወሰነችው በዋነኝነት ያላትን ከፍተኛ ዕዳ ለመክፈል ሲሆን፤ በተጨማሪነት የቴሌኮምን ተደራሽነት ለመጨመርና አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ እንደሆነም ይጠቀሳል።
ኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድን ለመስጠት ወደ ገበያው መግባት የሚሹ ፍላጎታቸውን እንዲገልጹ ሲጠየቅ 12 የቴሌኮም ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ ውስጥ ለመሳተፍ ፍለጎት እንዳላቸው ገልጸው ነበር።
ከእነዚህ ውስጥም የፈረንሳዩን ኦሬንጅ ጨምሮ ሳዑዲ ቴሌኮም ኩባንያ፣ ሊኩዊድ ቴሌኮም፣ እንዲሁም የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ኢቲሳላትን ጨምሮ ሌሎች ኩባንያዎች አፈግፍገዋል።
ለዚህም አንደኛው ምክንያት ሆኖ የተጠሰው የአገሪቱ ሕግ ለውጭ ተቋማት በሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ለመሰማራት አለመፍቀዱ ጋር ተያይዞ እንደሆነ ተገልጿል።
በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የቴሌኮም ፈቃድ ጨረታም እንደምታወጣ በገለፀችበት ወቅት የአገልግሎት ፈቃድ የሞባይል ገንዘብ መገበያያን እንዲጨምር ተደርጓል።
በተያያዘም ኢትዮ ቴሌኮም በድምፅ፣ በመልዕክት፣ በኢንተርኔት ተወስኖ የነበረውን አገልግሎት በማስፋት የቴሌ ብር የሞባይል አገልግሎት አስጀምሯል።
ተቋሙ ከቻይናው ሑዋዌ ኩባንያ ጋር በመተባበር ተግባራዊ ያደረገው ቴሌ ብር ለአስር ሚሊዮኖች ደንበኞቹ በስልካቸው ገንዘብ ለማስተላለፍና እና ለግብይት አገልግሎትም ይውላል ተብሏል።
ኢትዮ ቴሌኮም በአምስት ዓመት 33 ሚሊዮን ደንበኞችን ለማገልገልና 3.5 ትሪሊየን ብር ለማንቀሳቀስ ማቀዱም ተዘግቧል።
የውጭ አበዳሪዎች ለኢትዮጵያ ብድር መልቀቅ ማቅማትና የናረው ዕዳ
ለኢትዮጵያ ዋነኛ አበዳሪ የሚባሉ የገንዘብ ተቋማት ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተጨማሪ ብድር ለመልቀቅ እያንገራገሩ ነው ተብሏል።
በዋነኝነትም የነዚህ ተቋማት ስጋት ተጨማሪ ብድር ለአገሪቱ መስጠት የበለጠ ጫና ውስጥ ይከታታል እንዲሁም መክፈል አቋሟን የበለጠ ሊያዳክም ይችላል ከሚል ስጋት ጋር የተያያዘ ነው።
የቻይናው ኤክዚም ባንክ ለኢትዮጰያ ለመስጠት ቃል የገባውን 339 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆኑ ተነግሯል።
ከዚህም በተጨማሪ የዓለም ባንክ አንድ አካል የሆነው የዓለም አቀፉ የልማት ትብብር ማኅበር (ኢንተርናሽናል ዴቨሎፕመንት አሶሲየሽን) 3.3 ቢሊዮን ዶላር፣ የዓለም የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) 2.7 ቢሊዮን ዶላር፣ የኢትዮጵያ ዋነኛ አበዳሪ ቻይና 1.4 ቢሊዮን ዶላርና ሌሎችም አበዳሪዎች በያዝነው አመት እስከ መጋቢት ድረስ ይሰጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም እስካሁን አልተለቀቀም የተባለውም በዚህ አመት ነው።
ከዚህም ጋር በተያያዘ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ሊያስተጓጉል እንደሚችል ተሰግቷል።
ከሰሞኑም የኢትዮጵያ መንግሥት ከአገር ውስጥና የውጭ ውዝፍ እዳው እስከ አውሮፓውያኑ ሐምሌ መጨረሻ ድረስ 2.4 ትሪሊዮን ብር ሆኖ መመዝገቡን ሪፖርተር ጋዜጣ የገንዘብ ሚኒስቴርን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
በዘገባው መሰረት ብሔራዊ ባንክ ባለፈው አንድ ዓመት ባደረገው የብር ምንዛሬ ተመን ለውጥ ምክንያት የብር የመግዛት አቅምም በከፍተኛ ደረጃ በመውረዱ አጠቃላይ የአገሪቱ እዳ በ221. 5 ቢሊዮን ብር እንዳሻቀበም ዘገባው አስነብቧል።
የአገሪቱ ብሔራዊ ዕዳ በዚህ ዓመት 60 ቢሊዮን ዶላር ወይም ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) 70 በመቶ ይደርሳል ተብሏል።
ብሔራዊ ባንክና አዳዲስ መመሪያዎቹ
ብሔራዊ ባንክ በዘንድሮው ዓመት ከአምስት ጊዜ በላይ ገንዘብ ከሒሳብ ወደ ሒሳብ ማዘዋወር የሚከለክለው ሰርኩላርን ጨምሮ፣ የባንኮች መመስረቻ ካፒታል አምስት ቢሊዮን ብር እንዲሆን የሚሉና ሌሎች ተጨማሪ አዳዲስ መመሪያዎችን አውጥቷል።
ባንኩ በነሐሴ ወር ከዚህ ቀደም ባንኮች ይሰሩበት የነበረውን ቤት፣ ሕንፃ፣ መሬትና ሌሎችም ንብረቶችን በመያዣነት ተጠቅመው ብድር የሚሰጡበትን አሰራር አግዷል።
ባንኩ ይህንን እርምጃ የወሰደው በኮኖሚው ውስጥ አሻጥር ታይቷል በሚል ሲሆን በማይንቀሳቀሱ ንብረቶች መያዣነት የሚሰጠው ብድር እግድ እስከ መቼ እንደሆነ አልተጠቀሰም።
ከዚህም በተጨማሪ በቅርቡ በከፍተኛ ሁኔታ እያንሰራራ ያለውን የዋጋ ግሽበትን ለመግታት ባንኮች ከሚሰበስቡት የተጣራ ቁጠባ በኢትዮጵያ ብሔራዊ እንዲያስቀምጡት የሚጠበቅባቸውን የመጠባበቂያ የገንዘብ መጠን ወደ አስር በመቶ ከፍ እንዲያደርጉት ተወስኗል።
ከዚህ ቀደም 5 በመቶ የነበረውን የመጠባበቂያ የገንዘብ መጠን ከፍ እንዲል የተደረገው በኢኮኖሚው ውስጥ የሚዘዋወረውን የገንዘብ መጠን ለመቀነስ ቁጥብ የገንዘብ ፖሊስ ለማድረግ ከመወሰኑ ጋር ተያይዞ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ባንኮች ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚበደሩበት ዓመታዊ የወለድ ምጣኔ ከ13 በመቶ ወደ 16 በመቶ ከፍ እንዲል ተወስኗል።
ከዚህም በተጨማሪ የውጭ ምንዛሬንም በተመለከተ አዲስ መመሪያ የተላለፈ ሲሆን ከወጪ ንግድ፣ ከግለሰብ ሃዋላና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሬ ውስጥ 50 በመቶውን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገቢ ማድረግ አለባቸው ተብሏል።
እነዚህ በ2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ላይ ከታዩት ጉልህ ክስተቶች መካከል የተወሰኑት ናቸው።












