ኢትዮጵያ ግሽበትን ለመግታት የባንኮች የመጠባበቂያ የገንዘብ መጠን በእጥፍ እንዲያድግ ወሰነች

በከፍተኛ ሁኔታ እያንሰራራ ያለውን የዋጋ ግሽበት ለመግታት ባንኮች ከሚሰበስቡት የተጣራ ቁጠባ በኢትዮጵያ ብሔራዊ እንዲያስቀምጡት የሚጠበቅባቸውን የመጠባበቂያ የገንዘብ መጠን ወደ አስር በመቶ ከፍ እንዲያደርጉት ተወስኗል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዳስታወቀው ከዚህ ቀደም 5 በመቶ የነበረውን የመጠባበቂያ የገንዘብ መጠን ከፍ እንዲል የወሰነው በኢኮኖሚው ውስጥ የሚዘዋወረውን የገንዘብ መጠን ለመቀነስ ቁጥብ የገንዘብ ፖሊስ ለማድረግ ከመወሰኑ ጋር ተያይዞ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ባንኮች ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚበደሩበት ዓመታዊ የወለድ ምጣኔ ከ13 በመቶ ወደ 16 በመቶ ከፍ እንዲል መወሰኑም ተገልጿል።
ይህ የባንኮች መጠባበቂያና የብሔራዊ ባንክ የማበደሪያ ወለድ ምጣኔ ከዛሬው ዕለት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆንም ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ያለው ግሸበት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ሲሆን በሐምሌ ወር የነበረው መጠን 26.4 መሆኑን የሮይተርስ ዘገባ አስነብቧል። በዓመቱ ውስጥ የነበረው 20 በመቶ የሆነው የግሽበት መጠን በቅርቡ ከፍተኛ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን መንግሥት ይህንን ለመግታት የተለያዩ ጥረቶችን፣ ማሻሻያዎችንና ፖሊሲዎችን እያወጣ ይገኛል።
በቅርቡም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንደ ህንፃዎች ያሉ ንብረቶችን እንደ መያዣነት የሚጠቀሙ ባንኮች ሁሉንም ብድሮች ለጊዜው እንዲታገድ የሚወስን አዲስ መመሪያ ወጥቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪንም በተመለከተ ባንኮች ሲጠቀሙበት የነበረው አሰራር ላይ ማሻሻያ ተደርጓል።
በዚህም ማሻሻያ መሰረት ባንኮች ከወጪ ንግድ፣ ከግለሰብ ሃዋላና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሬ ውስጥ 50 በመቶውን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገቢ ማድረግ አለባቸው ተብሏል።
ከዚህ ቀደም ባንኮች ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት፣ ከዲያስፖራ ሂሳብና ከሌሎች ምንጮች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ ሰላሳ በመቶውን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገቢ እንዲያደርጉ የሚያዘውን መመሪያም ተሻሽሏል።
ይህ አሰራርም ከዚህ ቀደም በባንኮች በተደጋጋሚ ከሚቀርበው ወቀሳ መካከል ከውጭ ኢንቨስትመንት፣ ከዲያስፖራ ሂሳብና ከውጭ ብድር የሚገኝ የውጭ ምንዛሪ ተቀንሶ ወደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገቢ መደረግ የለበትም ለሚለውም ጥያቄ መልስ እንደሆነም ተገልጿል።
ከባንኮች በተጨማሪ ደንበኞችን በተመለከተ መያዝ የሚችሉትን የውጭ ምንዛሪ መጠንም ማሻሻያ ተደርጓል። በባንኮች የውጭ ምንዛሬ ያስገኙ ደንበኞች በውጭ ምንዛሪ ሂሳባቸው ያለ ጊዜ ገደብ መያዝ የሚችሉት የውጭ ምንዛሬ መጠን ከ31.5 በመቶ ወደ 40 በመቶ ከፍ ብሏል። የገንዘብ ተቋማትና ደንበኞቻቸው ሊኖራቸው ስለሚገባው ግንኙነት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዲስ መመሪያ አውጥቷል።
አገሪቱ እየሰራች ያለችው ወጥ ብሔራዊ መታወቂያ እስኪሰጥ ድረስ የገንዘብ ተቋማት ለደንበኞቻቸው የተለየ የደንበኛ መለያ ቁጥር መስጠት አለባቸው ተብሏል። ደንበኞች ወይም ድርጅቶች ከአንድ በላይ አካውንት ቢኖራቸውም ይህ የመለያ ቁጥር ተግባራዊ ይሆናል።
ደንበኞች ማንኛውንም የባንክ አገልግሎት በሚጠቀሙበት ወቅት ገንዘብ ማውጣት፣ ማስቀመጥም ሆነ ከሂሳብ ወደ ሂሳብ ማዘዋወርና ሌሎች ማንኛውም የባንክ አገልግሎቶችን በተመለከተ የገንዘብ ተቋማት (ባንኮች) ተመሳሳይ ቅፅ (ፎርም) መጠቀም አለባቸው።
በዚህም አሰራር መሰረት በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ማንኛውም ባንኮችም ሆነ የገንዘብ ተቋማት ለየትኛውም የባንክ አገልግሎቶች የሚጠቀሟቸው ወጥና ተመሳሳይ የሆኑ ቅፆችን እንደሆነ መመሪያው አስቀምጧል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ደንበኞች ትክክለኛ ያልሆነ ወይም አጠራጣሪ መረጃ የሚሰጡ ወይንም መመሪያዎችን የማያከብሩ ከሆነ የገንዘብ ተቋማቱ አገልግሎትን የመከልከል ይችላሉ።
ከዚህም በተጨማሪ ባንኮቹ የእነዚህን ደንበኞች መረጃ ለብሔራዊ ባንክና ለፋይናንስ መረጃ ደኅንነት ማዕከል ማስተላለፍ እንዳለባቸው ተጠቅሷል።
የገንዘብ ተቋማቱ (ባንኮች) እነዚህን መመሪያዎች በተገቢው መልክ እንዲሰሩም የደንበኞቻቸውን ታሪክ የሚከታተል አዲስ አደረጃጀት ሊያዋቅሩ ይገባል እንዲሁም ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አሰር መዘርጋት አለባቸው ተብሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለባንኮች ለመድንና ለጡረታ ዋስትና ድርጅቶች ቦንድ መሸጥ እንዲችልም ውሳኔ አስተላልፏል።
በዚህም መሰረት ባንኮች ከዓመታዊ ጠቅላላ የብድር ክምችት አንድ በመቶ የልማት ባንክ ቦንድ፤ የመድን ድርጅቶች ደግሞ ከተጣራ ዓመታዊ ገቢያቸው ከ15 በመቶ ያላነሰ የልማት ባንክ ቦንድ እንዲገዙ ተወስኗል።
ይህ የልማት ባንክ ቦንድ መንግሥት ዋስትና የሚሰጠውና በተነፃፃሪ የተሻለ ወለድ የሚከፈልበት እንደሚሆንም ተገልጿል።












