የሥራ ቦታችንን የሚያውኩት ምን ዓይነት ሠራተኞች ናቸው?

ሠራተኛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኢሜልም ይሁን በአካል ቢሮ የሚያውኩ ሰዎች በየመሥሪያ ቤቱ አይጠፉም።

ሰው ይሸነቁጣሉ፣ አስተያየታቸው ያማል፣ ሥራም ያደናቅፋሉ።

አንዳንዶች በግልጽ ሳይቆጡ ወይም ሳይሳደቡ፣ በስሱ ወይም ውስጥ ውስጡን ሰው መተናኮል ይችላል።

እንዲህ ዓይነት ባህሪ ያላቸው passive-aggressive ይባላሉ። ስውር ተንኳሽ ብለን እንተርጉመው።

የሥነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚሉት በእነዚህ ሰዎች ምክንያት የሥራ ቦታ ይታወካል።

ካትሪን በአንድ ግዙፍ የአሜሪካ አሳታሚ ድርጅት ስትሠራ የገጠማትን አትረሳውም።

ስውር ተንኳሽ የሥራ ባልደረባዋ በሚሰጠው አስተያየት ካትሪን እና የሥራ ባልደረቦቿ ተደብተው ይውላሉ።

ንግግሮቹን በአጠቃላይ መመዝገብ ስትጀምር ነው ምን ያህል ጎጂ እንደሆኑ የተረዳቸው።

“ንግግሩ በስለት የመወጋት ያህል ያማል። በቢሮው አስጨናቂ ድባብ ይነግሣል። ደካማነት እንዲሰማኝ ያደርገኝም ነበር። ንግግሮቹን መጻፍ ስጀምር ከዚህ ድርጊት ራሴን መከላከል የግድ እንደሆነ ገባኝ” ስትል ታስታውሳለች።

ካትሪን አሁን ደራሲና የአኗኗር ዘዬ አስተማሪ ናት። ሦስት ልጆች አሏት።

ስውር ተንኳሾችን በተመለከተ አንድ 'ፕሪፕለይ' የተባለ የቦስተን ድርጅት ጥናት ሠርቷል።

እአአ በ2022 በተሠራው ጥናት የተሳተፉ 1200 ሰዎች፤ በሕይታቸው ካሉ ሰዎች አብዛኞቹ ይህንን ባህሪይ እንደሚያሳዩ ተናግረዋል።

73 በመቶው እንዲያውም ይህ ባህሪይ ያላቸው ቤተሰቦች እና ጓደኞች እንዳላቸው አምነዋል።

52 በመቶ እነዚህን ሰዎች በየሳምንቱ ያገኟቸዋል።

ስውር ተንኳሾች ጥቃት የሚሰነዝሩት በቀጥታ አለመሆኑ እነሱ አካባቢ መሆንን ፈታኝ ያደርገዋል።

በቀጥታ አለመቆጣታቸው ወይም ተሳዳቢ አለመሆናቸው ነገሩን የበለጠ ያወሳስበዋል።

ከንግግራቸው ጀርባ ያለው ትርጉም ሰዎችን ቢረብሽም፣ ጥቃቱ ቀጥተኛ አለመሆኑ ሌላው ችግር ነው።

የሥራ ቦታን አስጨናቂ የሚያደርጉ ሰዎችን ማሸነፍ ይቻላል? እራስንስ እንዴት መከላከል ይቻላል? የሚለውን እንመልከት።

ስውር ተንኳሾች

የአየርላንድ ደብሊን ትሪኒቲ ቢዝነስ ስኩል የሚያስተምሩት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዋልዲስላው ሪቭኪን እንደሚሉት፣ የተለያዩ ዓይነት ስውር ተንኳሾች አሉ።

አንዳንዶቹ ጎጂ ሰው አይመስሉም። ለምሳሌ ሥራ ካጓተቱ በኋላ እውነታውን አንሻፈው በማቅረብ ለመጓተቱ ሌላን ሰው ተጠያቂ ያደርጋሉ።

የሥራ ባልደረቦቻቸውን በራስ መተማመን ስሜትን የሚቀንስ ንግግር ያሰማሉ ወይም ያጣጥላሉ።

 “ላስቀይምህ ባልፈልግም” ወይም “በክፉ አትውሰጅብኝና” በሚሉ ንግግሮች ይታወቃሉ።

በቀጥታ ተቆጥተው ጸብ ውስጥ ከሚገቡ ሰዎች በተለየ ስውር ተንኳሾች መቆጣጠር እንደሚከብድ ባለሙያው ያስረዳሉ።

የወንድ እና የሴት ጥላ በሥራ ቦታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ስውር ተንኳሽ ባህሪይ የሚፈጠረው እንዴት ነው?

አንዱ መላ ምት፣ ሰዎች የሚፈልጉበት ቦታ ለመድረስ ማጭበርበርን ሲመርጡ ይህ ባህሪይ መፈጠሩ እውን ይሆናል።

ይህ አቋራጭ መንገድን የመጠቀም አዝማሚያ Machiavellianism ይባላል።

ሌላው መላ ምት፣ ስሜታቸውን ጤናማ በሆነ መንገድ መግለጽ በማይችሉ ሰዎች ባህሪው መታየቱ ነው።

የሥራ ቦታ በአግባቡ ሳይመራ ሲቀርም ሰዎች ስውር ተንኳሽ መሆንን ሊመርጡ ይችላሉ።

ነገሮች በተዛባ መንገድ ሲከናወኑ የሚፈጠር ቁጣ ስውር ተንኳሽ የሚያደርጋቸውም አሉ።

ቀድሞ በደንበኞች አገልግሎት ዘርፍ ትሠራ የነበረችው ማሪያ ሥራ የለቀቀችው በስውር ተንኳሽ አለቃዋ ምክንያት እንደሆነ ትናገራለች።

አለቃዋ ቀልድ አስመስሎ ስለ ማሪያ ተክለ ሰውነት፣ ስለ ወሲብ ሕይወቷ እና ሌሎችም ግላዊ ጉዳዮች አስተያየት ይሰነዝር ነበር።

ይህ አለቃ በስብሰባ ወቅት፣ ምሳ ላይ፣ በኢሜል፣ በዋትስአፕም ሠራተኞችን በስውር ከመተንኮስ አይቆጠብም።

“ከዚያ ቦታ የለቀቅኩት ሞራሌ ደቆ ነው። በራስ መተማመኔ መክኖም ነበር” ትላለች።

ስውር ተንኳሽ አለቆች ያሏቸው ሰዎች ጤናቸው እንደሚቃወስ፣ ለጭንቀት እንደሚጋለጡና በሥራቸው እርካታ እንደሚያጡም ጥናት ይጠቁማል።

በእነዚህ አለቆች ሳቢያ የሚፈጠረው አሉታዊ ስሜት ከሠራተኛ ወደ ሠራተኛ ይጋባል። አጠቃላይ ቢሮውን ከማወክ አልፎ የሥራ ጥራትንም ይቀንሳል።

ስውር ትንኮሳን መከላከል ይቻላል?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የስውር ተንኳሾች ንግግር አንደ ቀልድ ሊታለፍ ይችላል። በቀላሉ ንግግሩን መለየትም ይቸግራል።

ኒው ዮርክ የምትኖረው የሙያዊ ሕይወት ባለሙያዋ አማንዳ ኦገስቲን እንደምትለው፣ ስውር ትንኮሳን ቶሎ ለማወቅ ስለሚከብድ መሥሪያ ቤቶች ባህሪውን ለመቆጣጠር ይቸገራሉ።

“ስውር ተንኳሾችን ስትጋፈጧቸው የተናገርኩት ነገር ‘ቀልድ ነበር’ ወይም ‘ለክፉ ብዬ አልነበረም’ ይሏችኋል። እንዲያውም እነሱ ተጎጂ እንጂ አጥቂ እንዳልሆኑ ሊከራከሩም ይችላሉ” ትላለች።

ስውር ተንኳሾች ቀዳሚ ግባቸው የሥራ ባልደረቦቻቸውን ማስቆጣት ነው።

“እናንተ ግን ስሜታችሁን ገትታችሁ በመረጋጋት አሳልፏቸው። ምንም ቢያደርጉ ስሜታዊ ምላሽ አትስጡ” ስትል ኦገስቲን ትመክራለች።

ኦገስቲን የምትመክረው ስክነት ቀላል እንዳልሆነ ትገነዘባች።

ችላ ማለት ውጤት ካላመጣ ነገሩን ወደ በላይ አለቆች መውሰድ ግድ ይሆናል።

ስውር ተንኳሾችን ባህሪያቸው እንደሚረብሽ ነግሮ መጋፈጥ ቢቻልም፣ ነገሩን በድለላ ወይም በሽንገላ ሊያልፉት ይችላሉ።

ጉዳዩን ወደ በላይ አለቆች ሲወስዱ ግን የስውር ተንኳሾችን ንግግር ብቻ ሳይሆን እንዴት አዋኪ እንደሆነም የሚገልጽ ማስረጃ ማቅረብ የግድ ነው።

አለበለዚያ ድርጊታቸውን ለመካድ ይቀላቸዋል።

ንግግሩ የአንድ ጊዜ ሳይሆን ተደጋጋሚ እንደሆነ ለማሳመን ተመሳሳይ ንግግሮችን መዝግበው የጽሑፍ ማስረጃ ማቅረብ ይችላሉ።

ስለ ስውር ትንኮሳ ተቀጣሪዎች ወቀሳ ሳያሰሙ በፊት መሥሪያ ቤቶች ሥልጠና ቢሰጡ ችግሩ እንደሚቀንስ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

እንዴት ባህሪውን መለየት እንደሚቻልና ችግሩ እንዴት እንደሚቀረፍ የቅድመ ጥንቃቄ ሥልጠና መስጠት መልካም ነው።

መሥሪያ ቤቱ ይሄ ባህሪይ ያለባቸውን ሰዎች ለማረቅ ቁርጠኛ መሆን ይጠበቅበታል።

አለበለዚያ ግን ሠራተኞች እራሳቸውን ለመከላከል መጣጣር ግዴታ ይሆንባቸዋል።

መግቢያችን ላይ የጠቀስናት ካትሪን፣ እራሷን ከስውር ተንኳሽ ነጻ ያወጣችው ነገሩን በቀጥታ በመጋፈጥ እንደሆነ ተናግራለች።

ሂደቱ ግን ቀላል አልነበረም። ሥራዋን ከማጣቷ ባሻገር ሥራ ቦታው በፈጠረባት መጥፎ ስሜት ሳቢያ ለዓመታት ተንገላታለች።