ዶናልድ ትራምፕ በፍርድ ቤት የተጣለባቸው 500 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት ውድቅ ተደረገ

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ዓመት በኒው ዮርክ ፍትሐ ብሔር የማጭበርበር ችሎት እንዲከፍሉ የታዘዙት 500 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ቅጣት በይግባኝ ፍርድ ቤት ውድቅ ተደረገ።

በትራምፕ ላይ የተመሰረተውን ክስ የተመለከቱት ዳኛ አርተር ኤንጎሮን፤ ፕሬዝዳንቱ ከፍ ያለ ብድር ለማግኘት በማሰብ የድርጅታቸውን ንብረቶች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ አሳድገዋል በሚል የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍሉ ትእዛዝ ሰጥተው ነበር።

የኒውዮርክ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ሐሙስ ዕለት ባወጣው ረዘም ያለ የውሳኔ ሰነድ፤ ትራምፕ በማጭበርበር ወንጀል ተጠያቂ የመሆናቸውን ጉዳይ አልቀለበሰውም።

ነገር ግን የተጣለባቸው ግማሽ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የገንዘብ ቅጣት ከልክ በላይ እንደሆነ እንዲሁም ሰዎች ከባድ ቅጣት እንዳይጣልባቸው ከለላ የሚሰጠውን ህገ መንግሥታዊ ድንጋጌ የጣሰ ሊሆን እንደሚችል ገልጿል።

የባለፈውን ዓመት ውሳኔ ያስተላለፉት ዳኛ ኤንጎሮን፤ ትራምፕ 355 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍሉ ትዕዛዝ ሰጥተው የነበረ ሲሆን ይህ የገንዘብ ቅጣት ከወለድ ጋር ሲደመር ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል።

የአዲሱን ውሳኔ ካስተላለፉት ዳኞች አንዱ የሆኑት ፒተር ሞልተን በበኩላቸው፤ "በእርግጥ ጉዳት የተከሰተ ቢሆንም [የተፈጸመው ጥፋት] ግማሽ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋው ገንዘብ ለመንግሥት እንዲወሰን የሚያስችል አውዳሚ ጉዳት አይደለም" ሲሉ በመዝገቡ ላይ ጽፈዋል።

ትራምፕ፤ ትሩዝ ሶሻል በተባለው የማህበራዊ ሚዲያ ድረ ገፃቸው ባሰፈሩት መልእክት፤ ውሳኔውን "ሙሉ ድል" ሲሉ ጠርተውታል።

"ፍርድ ቤቱ በኒው ዮርክ ግዛት ውስጥ የንግድ ሥራን የሚጎዳውን ይህን ህገ ወጥ እና አሳፋሪ ውሳኔ ውድቅ ለማድረግ ድፍረትን ማግኘቱን በጣም አከብራለሁ" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"በንግድ ስራ ረገድ ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ የፖለቲካዊ ወንጀል ምርመራ ነበር" ሲሉም አክለዋል።

ትራምፕ ላይ ክስ የመሰረተው የኒው ዮርክ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ቢሮም በበኩሉ፤ የይግባኝ ፍርድ ቤቱ ትራምፕ በማጭበርበር ወንጀል ተጠያቂ መሆናቸውን ማጽናቱን እንዲሁም ዳኞቹ ፋይናንስ ነክ ያልሆኑ ሌሎች ቅጣቶችን ውድቅ አለማድረጋቸውን በማንሳት በውሳኔው ራሱን በአሸናፊነት አቅርቧል።

ይሁን እንጂ ቢሮው የቅጣት ውሳኔውን በመቃወም በሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ለማለት አቅዷል።

የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ቢሮ ባወጣው መግለጫ፤ ዳኞቹ "ዶናልድ ትራምፕ፣ ኩባንያው እና ሁለት ልጆቹ በማጭበርበር ተጠያቂ ናቸው የሚለውን የመጀመሪያው ፍርድ ቤት በአግባቡ [በመረጃ] የተደገፈ ድምዳሜ አረጋግጠዋል" ብሏል።

"ይህ ከታሪክ መዝገብ ሊጠፋ አይገባም፤ ሌላ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቱ ህግን መጣሳቸውን እና ክሳችን አግባብነት ያለው መሆኑን ወስኗል" ሲል ውሳኔውን ድል አድርጎ አቅርቧል።

ባለፈው ዓመት በትራምፕ፣ በሁለት ልጆቹ እና በድርጅታቸው ላይ የተመሰረተውን ክስ የተመለከቱት ዳኛ ኢንጎሮን፤ ትራምፕ የኩባንያው ዳይሬክተር ሆነው እንዳያገለግሉ ወይም ለሶስት ዓመት ከግዛቱ ባንኮች ብድር እንዳይወስዱም አግደው ነበር።

የሐሙስ ዕለት የተላለፈው አዲሱ ውሳኔ ይህንን እና ሌሎች በዳኛ ኤንጎሮን የተጣሉ ገንዘብ ነክ ያልሆኑ ቅጣቶች እንዲቀጥሉ አድርጓል።

323 ገጾችን ያሉት እና ሶስት ረዥም አስተያየቶችን የተካተቱበት የውሳኔ መዝገብ፤ ችሎቱ ውስጥ በተሰየሙ አምስት ዳኞች መካከል አለመግባባት መኖሩን አሳይቷል።

ዳኞቹን የከፋፈለው ዋነኛ ጉዳይ በአቃቤ ህጓ ሌቲሺያ ጄምስ አማካኝነት በትራምፕ እና በልጆቻቸው ላይ የቀረበው "ቋሚ እና ተደጋጋሚ ማጭበርበር" ክስ አግባብነት ነው።

ብዙዎቹ ዳኞች አቃቤ ህጓ "ይህንን ክስ የማቅረብ ህጋዊ ስልጣን እንዳላት" አቋም የያዙ ሲሆን አንድ ሌላ ዳኛ ደግሞ ክሱ ውድቅ መደረግ አለበት የሚል እምነት አላቸው።

ቀሪዎቹ ሁለት ዳኞች በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ የሚካሄድ አዲስ የፍርድ ሂደት ሊኖር ይገባል ብለዋል።